ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ለተደረገባቸው 38 ምርቶች፣ ባንኮች ከነገ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ሌተር ኦፍ ክሬዲት›› መክፈት እንደማይችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየናረ የመጣውን የጥቁር ገበያ ለመቆጣጠር ተሽከርካሪን ጨምሮ 38 ምርቶች እንዳይገቡ በመወሰኑ፣ ባንኮችም በዚህ ውሳኔ መሠረት ለእነዚህ ምርቶች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቅዱ መመርያ ደርሷቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ደግፌ በሰጡት መግለጫ፣ በመንግሥት በተሰጠው ውሳኔ መሠረት 38ቱ ምርቶች ወደ አገር እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለው ከጥቅምት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡
በዚህ መሠረት ለእነዚህ ምርቶች ማንኛውም ባንክ ኤልሲ መክፈት የማይችል መሆኑ የተገለጸለት ሲሆን፣ ይህንን መመርያ ጥሰው ኤልሲ የሚከፍቱ ባንኮች ካሉ ሕግ በመተላለፍ ተጠያቂ የሚሆኑና የሚቀጡ መሆኑንም ምክትል ገዥው አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት 38ቱ ምርቶች እንዳይገቡ ያደረገበትን ምክንያት በተመለከተ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደግሞ፣ ዕርምጃው የዋጋ ንረት በኅብረተሰቡ ላይ ሊያደርስ የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ታስቦ ጭምር የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡
በኅብረተሰብ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ሲባል መንግሥት የተለያዩ የፊስካል ገንዘብና ሌሎች ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ያስታወቀው ገንዘብ ሚኒስቴር፣ ይህን ውጤታማ ለማድረግ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች መውሰዱ አግባብ መሆኑ ታምኖበት የሚተገበር መሆኑን አመልክቷል፡፡ ምክትል ገዥውም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የማይገባቸው ምርቶች ላይ ክልከላ መጣሉ ኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያሳርፍ መሆኑን ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ባስታወቀው መሠረት፣ ሕገወጥነትን ለመከላልና እየናረ የመጣውን የጥቁር ገበያ ለመቆጣጠር ተጨማሪ አጋዥ ዕርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑንም ምክትል ገዥው ገልጸዋል፡፡
የማክሮ ኮሚቴው ጥናት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቀድላቸው የተዘረዘሩ ምርቶች ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው በግል የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ እንደ አቶ ፈቃዱ ገለጻ፣ ‹‹በግል ወደ ኢትዮጵያ ከሚገቡ ምርቶች ተሽከርካሪዎች በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑ፣ ለእነዚህ ተሽከርካሪዎች ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለሌሎች መሠረታዊ ለሚባሉ፣ በተለይ የፋብሪካ ጥሬ ዕቃዎችን ማስመጫ ለማዋል ያስችላል፤›› ብለዋል፡፡
ከተሽከርካሪዎች ሌላ ክልከላ ከተደረገባቸው ምርቶች ውስጥ እንደ ከረሜላ፣ ማስቲካና ጣፋጭ ምግቦች ተጠቅሰዋል፡፡ የተለያዩ የፍራፍሬ ጭማቂዎች፣ ሲጋራ፣ ውስኪ፣ ወይንና ሌሎች የአልኮል መጠጦች በዚህ መመርያ መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ የማይገቡ ይሆናሉ፡፡
ሽቶ፣ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች፣ በኤሌክትሪክ ከሚሠሩ ውጪ ያሉ የሞተር ሳይክሎችና ሳይክሎችም ገደብ ከተጣለባቸው ምርቶች ውስጥ ይገኙበታል፡፡ እንደ ሒውማን ሄርና መሰል ጌጣጌጦችም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቅዱላቸው ተወስኗል፡፡ ከምግብ ነክ ምርቶች የገበታ ጨው፣ ቼኮሌቶችና ሌሎች የታሸጉ ምርቶች ይገኙበታል፡፡ ከሕፃናት አልሚ ምግቦችና የዱቄት ወተቶች በስተቀር ያሉ የተለያዩ የታሸጉ ምርቶች ክልከላው የሚመለከታቸው ናቸው፡፡
ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆየው ክልከላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ያስረዱት አቶ ፈቃዱ፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢራ እየተመረተ ከውጭ እንዲገባ መፈቀዱ አግባብ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቢራን ከማስገባት ለቢራ ማምረቻ የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡
እነዚህ ምርቶች በዓመት ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ያስወጡ ነበር? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፈቃዱ፣ አሁን ባለው ደረጃ ምን ያህል እንደሚሆን መግለጽ ባይችሉም፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይወጣባቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በተለይ ተሽከርካሪ አሁን ከሚገባው አንፃር ግማሽ ያህሉ እንኳን በዚህ ክልከላ ውስጥ የሚወድቅ ከሆነ፣ ከሌሎች ዕገዳ ከተደረገባቸው ምርቶች ጋር ተደምሮ በዓመት ቢያንስ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ የሚወጣባቸው ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ይህንን የውጭ ምንዛሪ ለተመረጡ ዘርፎች ማስተላለፍ ቢቻል፣ ኢኮኖሚውን ምን ያህል ሊያነቃቃ እንደሚችል መገመት ይቻላል፤›› ያሉት ምክትል ገዥው፣ ከተሽከርካሪዎች አንፃር የውጭ ምንዛሪ እንዳይፈቀድላቸው የተከለከሉት ሁሉም ተሽከርካሪዎች እንዳልሆኑም ጠቁመዋል፡፡ የሥራ ተሽከርካሪዎች ይህ መመርያ እንደማይመለከታቸውና ለግል አገልግሎ የሚውሉ ትንንሽ ተሽከርካሪዎች በዚህ መመርያ ውስጥ በዋናነት የተካተቱ ናቸው፡፡ ‹‹በትንሽ ኤልሲ እየተከፈተ ከረሚታንስ በተጠለፈ ዶላር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች እንዳይገቡ የሚደረግ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እየወሰዳቸው ያሉ ዕርምጃዎችን የሚደግፍ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሪ ኢኮኖሚያዊ በሆነ መንገድም ሆነ ባልሆነ መንገድ በጣም እየሰፋ ስለመጣ ይህንን ለማረጋጋት የተወሰደ ጠቃሚ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡
ላልተወሰነ ጊዜ ወደ አገር እንዳይገቡና ምንም ዓይነት ኤልሲ እንዳይከፈትላቸው የተደረጉት እነዚህ ምርቶች፣ በአብዛኛው ከፍተኛ ታክስ የሚከፈልባቸው ከመሆኑ አንፃር፣ መንግሥት ሊያገኝ የሚገባውን ታክስ እንዳያገኝ ሊያደርጉ የሚችሉ ናቸው፡፡ አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ግን ክልከላው የተሻለ በመሆኑ ውሳኔው ሊሰጥ መቻሉም ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያለው ክልከላ ኢኮኖሚውን ላለመጉዳቱ ምን ያህል ታሰቢ ተደርጎ የተወሰነ ነው የሚል ጥያቄ ለምክትል ገዥው ቀርቦ ነበር፡፡ ወደ አገር እንዳይገቡ የተከለከሉ ምርቶች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ አይችሉም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ፈቃዱ፣ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ተፅዕኖዎች የሚጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ተፅዕኖ የሌለው ፖሊሲ እንደሌለ በማመልከት፣ ዋናው ጉዳይ የትኛው ይሻላል? የሚለው ተብሎ የተሻለው ይመረጣል እንጂ፣ ተፅዕኖ መኖሩ እንደማይቀር አስረድተዋል፡፡ ‹‹በእኛ እምነት ከእነዚህ ከተከለከሉ ምርቶች የተሻለ ጠቀሜታ ያላቸው ምርቶች መግባት ስላለባቸው የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡ ጥሬ ዕቃ በማስገባት ፋብሪካዎች ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎች በርካታ ጠቀሚታ ያለው ነው የሚሉት ምክትል ገዥው፣ የተከለከሉ ምርቶችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ ጭምር ዕድል የሚሰጥ መሆኑ አንዱ ጠቀሜታ ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ጠቀሜታ አለው ብለው የጠቀሱት በውጭ ሐዋላ ጠልፎ ዕቃ ማስመጣት የሚያስቀር በመሆኑ በሕጋዊ መንገድ በባንክ የሚመጣውን የውጭ ገንዘብ ያሳድገዋል፡፡ ይህም በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መጠን ስለሚያጠብ በውጭ ምንዛሪ የሚልኩ ሰዎች ወደ ባንክ እንዲመለሱ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጥቁር ገበያውን ለመቆጣጠር ሰሞኑን ዕርምጃዎች ከመወሰዳቸው በፊት በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር ዋጋ ከ100 ብር በላይ ደርሶ እንደነበር ያስታወሱት ገዥው፣ ከዕርምጃው በኋላ በጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋ ከ80 ብር በታች ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህ አሁን የሚተገበረው መመርያ ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በመደበኛውና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ስለሚያጠብ ይህም አንድ ጠቃሚ ጎን ይኖረዋል፡፡ ይህ መመርያ ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ በመሆኑ፣ መሀል ላይ እየታየ ማስተካከያዎች ሊወሰዱ የሚችሉ መሆኑንም ከገለጻቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ የውጭ ምንዛሪ የማይፈቀድላቸው 38 የምርት ዓይነቶ ዝርዝር የሚከተሉት ናቸው፡፡
Based on Import Data of 2014 Ethiopian Budget year (1USD = 50Br) |
||||
No |
Tariff Code |
Product Description |
|
|
1 |
1704 |
Chewing Gum and Sugar Confectionary |
ከረሜላዎች፣ ማስቲካዎችና ሌሎች ጣፋጭ ዝግጅቶች |
|
2 |
1806 except 18062010 |
Chocolate |
ቸኮሌት |
|
3 |
1905 |
Sweet Biscuits and Waffies |
ብስኩቶችና ዋፈሮች |
|
4 |
2009 |
Fruit Juices & canned fruits |
የፍራፍሬ ጭማቂና የታሸጉ ፍራፍሬዎች |
|
5 |
|
Jam, vimto, potato chips, tomato paste |
ከፍራፍሬ የተዘጋጁ ጃሞች፣ የድንች ጥብሶች፣ |
|
6 |
22021000 |
Water including mineral water, soft drinks and other non-alcoholic drinks |
የታሸጉ ውኃዎች፣ ለስላሳ መጠጦችና አልኮል የሌላቸው መጠጦች |
|
7 |
Chapter 22 |
Wihisky, wind, Beer and all other alcoholic drinks |
ውስኪ፣ ወይን፣ ቢራና ሌሎች አልኮል መጠጦች በሙሉ |
|
8 |
2402,2403,2404 |
Cigarettes and substitutes |
ሲጋራ |
|
9 |
3303 |
Pertumes and toilet waters |
ሽቶዎችና ቶይሌት ዋተርስ |
|
10 |
33041000,33042000,33043000 |
Make up preparations |
የውበት ወይም የመኳኳያ ዝግጅቶች |
|
11 |
3401 |
Soaps |
ሳሙናዎች |
|
12 |
3604 |
Fireworks |
ርችቶች |
|
13 |
4202 |
Bags and waliets |
ቦርሳና ዋሌቶች |
|
14 |
4909 |
Post cards and similar cards |
የታተሙ ሥዕላዊ መግለጫ ያላቸው ካርቶች |
|
15 |
4910 |
Calendars |
የቀን መቁጠሪያ ካሌንደሮች |
|
16 |
49119190 |
Pictures including wall picture |
ሥዕሎች የግድግዳ ሥዕሎችን ጨምሮ |
|
17 |
6504 & 6505 |
Hats and headgears |
ባርኔጣዎችና ኮፍያዎች |
|
18 |
6702 |
Artificial flowers |
አርቲፊሻል አበባዎች |
|
19 |
6704 |
Human and artificial hairs |
የሰውና አርቲፊሻል ፀጉሮች |
|
20 |
Chapter 71except Legal Tender Coins |
Artificial jewelers |
አርቲፊሻል ጌጣጌጦች |
|
21 |
8703 |
Complete build up /CBU/ Automobiles and three wheelers /except electric motor vehicles/ |
የተገጣጠሙ የቤት አውቶሞቢልና ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች /በኤሌክትሪክ ሞተር የሚሠሩትን ሳይጨምር/ |
|
22 |
8711 |
Complete build up /CBU/ motorcycles /except electric motor vehicles/ |
የተገጣጠሙ ሞተር ሳይክሎች /በኤሌክትሪክ ሞተር የሚሠሩትን ሳይጨምር/ |
|
23 |
8712 |
Bicycles |
ሳይክሎች |
|
Based on Import Data of 2014 Ethiopian Budget year (1USD = 50Br) |
||||
24 |
9401 & 9403 |
Household and office Furniture’s except specially designed chairs |
በታሪፍ ቁጥር 9401 እስከ 9403 የሚመደቡ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች |
|
25 |
25.01 |
Table salts |
የገበታ ጨው |
|
26 |
Chapter 95 |
Different games |
የተለያዩ መጫወቻ ዕቃዎች |
|
27 |
Chapter 91 |
Hand watches, table and wall clocks |
የእጅ፣ የጠረጴዛና የግድግዳ ሰዓቶች |
|
28 |
66 01 & 6602 |
Umbrella |
ዣንጥላዎች |
|
29 |
Chapter 57 |
Carpets |
ምንጣፎች |
|
30 |
1601 |
Pork luncheon meat |
የዓሳማ ሥጋዎች |
|
31 |
1602 |
Chicken luncheon meat |
የዶሮ ሥጋዎች |
|
32 |
1604 |
Tuna, sardins and other sea foods |
ቱናዎች፣ ሰርዲኖችና ሌሎች የዓሳ ምርቶች |
|
33 |
Chapter 19 & 21 |
Packed foods preparation except milk and preparation for infant or young children |
ከሕፃናት አልሚ ምግቦችና ወተቶች በስተቀር የተለያዩ የታሸጉ ምግቦች |
|
34 |
6911-6914 |
Ceramics and porlin kitchen wares |
ከሴራሚክስና ፖርስሊን የተዘጋጁ የቤት ዕቃዎች |
|
35 |
9613 |
Gas lighter |
ጋዝ ላይተር |
|
36 |
9615 |
Hair pin, clip, grips, roller, bow, band, pony tall, tiyara |
የተለያዩ የፀጉር ጌጣጌጦች |
|
37 |
96180000 |
Mannequin |
ልብስ ማሳያ አሻንጉሊቶች |
|
38 |
7013 |
Glass beer mug, wine, alcohol, ash tray, base, frame |
ከብርጭቆ የተዘጋጁ የመጠጥ መጠጫ ዕቃዎች፣ የሲጋራ መተርኮሻዎች፣ የአበባ መያዣና ተመሳሳይ ዕቃዎች |
|