Thursday, May 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድር በጅግጅጋ ከተማ በይፋ ሊጀመር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሕግ ማዕቀፎ ሦስት ዓመት የሆነውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥን ብድር፣ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በይፋ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

የብድር ዓይነቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በይፋ የሚጀመርበት ሶማሌ ክልል፣ በምሥራቅ ክላስተር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ብሔራዊ ባንክ አገልግሎቱን ለማስፋፋት ያቀደው የአገሪቱን አካባቢዎች በአራት ክላስተሮች ከፍሎ መሆኑን የባንኩ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት አገር አቀፉን የማስጀመሪያ ፕሮግራም በጅግጂጋ ከተማ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ ይፋ የሚደረግበት ትክክለኛ ቀን ግን ገና እንዳልተቆረጠ ምክትል ገዥው ገልጸዋል፡፡

ኦሮሚያ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱ የሚጀመርባቸው ተከታይ ክልሎች መሆናቸውን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ አካል የሆነው በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድር፣ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ሰብሳቢነት በሚመራው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ምክር ቤት አቅጣጫ የሚሰጥበት ነው፡፡ ምክር ቤቱ አገልግሎቱን በዚህ ዓመት ለማስጀመርና ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለማስፋፋት አቅጣጫ ማሳለፉን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ አርብቶ አደሮች በብዛት በሚገኙበት የሶማሌ ክልል አገልግሎቱን ለማስጀመር ያቀደው፣ በእንስሳት ማስያዣነት በሚሰጥ የብድር አገልግሎት ነው፡፡ አገልግሎቱ ወደ ሌሎች ክልሎች እየተስፋፋ ሲሄድ በሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የሚሰጥ ብድር እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

ብሔራዊ ባንክ 2012 ዓ.ም. በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድርን አስመልክቶ ባወጣው መመርያ ላይ፣ የእርሻ ሰብል፣ እንስሳት፣ የአዕምሮአዊ ንብረት ባለቤትነትንና የመሬት ተጠቃሚነት መብት ምዝገባ ተደርጎባቸው ለማስያዣነት እንደሚቀርቡ ዘርዝሯል፡፡ እንደ ቦንድና የአክሲዮን ድርሻ ያሉ ገንዘብ ነክ ሰነዶችም ለብድር ማስያዣነት መቅረብ ይችላሉ፡፡

በ2011 ዓ.ም. የወጣው በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሠረት የዋስትና ንብረት መብት አዋጅም ሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ በተከታዩ ዓመት ያወጣቸው ሁለት መመርያዎች በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት ለሚሰጥ ብድር የሕግ ማዕቀፍ ቢዘረጉም፣ ለንብረቶቹ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት ሥራ ባለመጀመሩ እስካሁን አገልግሎቱ ሳይጀመር ቆይቷል፡፡

የምዝገባ ሥርዓቱ በማስያዣነት ለሚቀርቡ ብድሮች የመለያ ቁጥር የሚሰጥ ሲሆን፣ ባንኮች ብድር ከመስጠታቸው በፊት ተንቀሳቃሽ ንብረቱ በሌላ ብድር መያዝና አለመያዙን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ንብረት የሚገዙም ሆነ ሌሎች መረጃ ፈላጊ ግለሰቦችም ስለንብረቱ መረጃና ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡

ይህንን ሥርዓት የመዘርጋትና በሚሊዮን የሚቆጠሩ መረጃዎችን የሚይዝ ዳታ ቤት ገዝቶ ሙከራ የማድረግ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ እስካሁን ከ60 ሺሕ በላይ ንብረቶች ምዝገባ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ተደራሽነትን በማስፋት የተገለሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በማቀድ የተዘረጋው ይህ ሥርዓት፣ አገር አቀፍ ደረጃ ይፋዊ ሥርዓቱን ለሶማሌ ክልል ለማድረግ ያቀደው አርብቶ አደሩ በተጠቃሚነት “የተገለለ” መሆኑ ስለታመነበት መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

‹‹አርሶ አደሮች በማዳበሪያና ምርጥ ዘር ከመንግሥት ድጋፍ ያገኛሉ፣ አርብቶ አደሮች ግን እንደዚህ ዓይነት ድጋፍ የሚያገኙበት መንገድ የለም፤›› ሲሉ ሐሳቡን አብራርተዋል፡፡ እንስሳቶቻቸውን በማበደር የሚያገኙት ብድር ተጓዳኝ ገቢ የሚያስገኙ ሥራዎች ላይ እንዲሠማሩ እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

በዚህም መሠረት አገልግሎቱ ይፋ ሲደረግ በክልሉ የሚገኙ አርብቶ አደሮች እንደ ቀንድ ከብት፣ ግመል፣ ፍየል፣ በግና አህያ ያሉ እንስሳቶቻቸውን በማስያዝ ከባንክና ማይክሮ ፋይናንሶች ብድር ማግኘት ይችላሉ፡፡ ለብድር ማስያዣነት የሚቀርቡ እንስሳት ከተመዘገቡ በኋላ የሚሰጣቸው መለያ ቁጥር የያዘ ቢጫ የፕላስቲክ ተለጣፊ ጆሯቸው ላይ ይቀመጣል፡፡ ይህንን ሥራ የሚያከናውነው የግብርና ሚኒስቴር እንደሆነ ብሔራዊ ባንክ በ2012 ዓ.ም. ያወጣው መመርያ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ለብድር ማስያዣነት የሚቀርቡ እንስሳት ያላቸውን ዋጋ ለማወቅ እንዲቻል፣ በየወሩ የእንስሳትን መሸጫ ዋጋ በድረ ገጹ ላይ የማስቀመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይሁንና አበዳሪው ባንክ በማስያዣነት የቀረበውን እንስሳ ዋጋ ለመወሰን፣ ከግብርና ሚኒስቴር ውጪ ሌሎች ታማኝ የመረጃ ምንጮችን የመጠቀም መብት አለው፡፡

እንስሳቱ በማስያዣነት የሰጠ ተበዳሪ ካለ አበዳሪው ፈቃድ መሸጥ መለወጥም ሆነ የማስተላለፍ፣ እንዲሁም በእንስሳቱ ላይ የተደረገውን መለያ የመንቀል ፈቃድ አይኖረውም፡፡

ብሔራዊ ባንክ አገልግሎቱን በጅግጅጋ ከተማ በይፋ በሚያስጀምርበት ሥነ ሥርዓት ላይ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድና የብሔራዊ ባንክ ገዥን ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ጨምሮ፣ ከፍተኛ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እነዚህ ኃላፊዎች በአሁኑ ጊዜ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ ጉባዔ ለመሳተፍ በአሜሪካ ይገኛሉ፡፡ በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድር በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በይፋ የሚጀመርበት ቀን የሚወሰነው፣ ባለሥልጣናቱ ወደ አገር ውስጥ ከመጡ በኋላ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች