Saturday, April 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ልማት የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ አይሁን!

ኢትዮጵያን ከተመፅዋችነት መዝገብ ስሟን የሚያሰርዝ የልማት እንቅስቃሴ በስፋት ሲጀመር፣ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአንድነት ሆነው ከዳር የማድረስ ዓላማ ሊሰንቁ የግድ ይላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት እየተነገረለት የሚገኘው የስንዴ ልማት ጅማሮ እንዲሰምር፣ ሀቀኛ ዜጎች በቅንነት መንፈስ ተነሳስተው የድህነት ቀንበር እንዲሰበር መተባበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የስንዴ ልማቱ ከተራ የፖለቲካ ንትርክና አሉባልታ ተላቆ፣ በእውነተኛ የትብብር መንፈስ ከዳር እንዲደርስ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆን አለበት፡፡ የስንዴ ልማቱ በጥናት ላይ ተመሥርቶና ተገቢው የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ከተደረገለት፣ በሔክታር በአማካይ ከ80 ኩንታል በላይ ሊያስገኝ እንደሚችል ይነገራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ተስፋ ባላት አገር ውስጥ የስንዴ ልማቱ መሠረት ሳይዝ፣ በግራና በቀኝ በጽንፈኝነት መንፈስ የሚሰሙ ከንቱ ነገሮች መብዛታቸው ለማንም አይጠቅምም፡፡ የስንዴ ልማቱን ከፖለቲካ ገመድ ጉተታ በማላቀቅ አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች የበለጠ ምርት እንዲያሳፍሱ፣ ኢንቨስተሮች ማበረታቻ አግኝተው በልማቱ በስፋት እንዲሳተፉ፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድሎች በብዛት እንዲፈጠሩ፣ ገበያዎች በስንዴ ምርት እንዲጥለቀለቁና ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ ጥረት ይደረግ፡፡  

መንግሥት በስንዴ ልማቱ የጀመረው አበረታች እንቅስቃሴ በማይረቡ ምክንያቶች መደነቃቀፍ የለበትም፡፡ ኢትዮጵያውያን የረባ ዳቦ ሳይበሉ ዘሎ የኤክስፖርት ወሬ ላይ መጣድ፣ ‹‹ከፈረሱ ጋሪውን ማስቀደም›› ነው፡፡ የአገር ውስጥ ዱቄት ፋብሪካዎች፣ ዳቦ መጋገሪያዎች፣ የፓስታና የማካሮኒ ፋብሪካዎችና የመሳሰሉት አስተማማኝ የስንዴ ምርት አቅርቦት ያግኙ፡፡ በአገር ውስጥ ገበያው እየሰፋ ሲሄድ አምራቾችም እየበዙ ወደ ውጭ ገበያ ማማተር ይቻላል፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ አጥ ወጣቶች በማኅበራት ተደራጅተው የባንክ ብድር ቢመቻችላቸው፣ ፆማቸውን የሚያድሩ በርካታ ሚሊዮን ሔክታር መሬቶች ከአፍሪካ አልፈው ዓለምን መመገብ ይችላሉ፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው በግብርና ኢንቨስትመንት የሚሳተፉ ባለሀብቶች በብዛት ሲገኙ ደግሞ፣ የአገር ውስጥ ባንኮች የስንዴ ልማቱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምርቶች እንዲመረቱ ድጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ የስንዴ ልማቱ ባለድርሻ አካላት ሲበዙበት የባለቤትነት ስሜቱ እየተጠናከረ፣ ኢትዮጵያ የዳቦ ቅርጫት እንድትሆን ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አጉል ትከሻ መለካካትና መጎነታተል ለማንም አይበጅም፡፡ ይልቁንም ልማቱ በተሻሻሉ ዝርያዎች፣ በዘመናዊ የግብርና ማሽኖችና በዕውቀት ላይ በተመሠረተ እንቅስቃሴ እንዲከናወን ዕገዛ ይደረግ፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር ናት፡፡ ልጆቿ መከባበርና መተባበር ከቻሉ ተዓምር መሥራት አያቅታቸውም፡፡ የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መገንባት ይኖርበታል፡፡ በተከፋፈለ ልብ ግን እንኳን አገር ቤተሰብም ፀንቶ መቆም አይችልም፡፡ በዓለም ታሪክ አንፀባራቂና ተምሳሌታዊ ገድል የፈጸሙ ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ያቆሟትን አገር፣ በክብር ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡ መተሳሰብ፣ መተጋገዝ፣ አገርን በጋራ መጠበቅና በልማት ማሳደግ፣ ከልዩነቶች ይልቅ ለጋራ አገራዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት፣ ታማኝነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ጨዋነትና ሰብዓዊነት ለኢትዮጵያ ያስፈልጋሉ፡፡ ይህች ታላቅ አገር በተለያዩ ጊዜያት በገጠሟት ፈተናዎች ምክንያት የረሃብ፣ የግጭት፣ የኋላቀርነትና የመከራ ተምሳሌት መሆኗ ያሳዝናል፡፡ ሕዝቧም በተለያዩ ጊዜያት በተነሱ ገዥዎች አበሳውን ማየቱም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን ካለፉት ስህተቶች ተምሮ አገርን ማልማትና ማሳደግ የግድ መሆን አለበት፡፡ ወደ ዴሞክራሲ፣ ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ልማትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ግንባታ በፍጥነት መግባት የሚቻለው ከንትርክ ይልቅ ለልማት ቅድሚያ ሲሰጥ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ መከባበርና መተባበር መለመድ አለበት፡፡ የስንዴ ልማቱ በዚህ መንፈስ ይታይ፡፡

ምክንያት እየፈለጉ በነገር ከመቋሰልና አገርን የበለጠ ቀውስ ውስጥ ለመክተት ሴራ ከመጎንጎን፣ ካለፉት ዘመናት የተሻሉ ልምዶችን በመቅሰምና ጥሩ ያልነበሩትን ወደ ጎን በመተው የሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ መንግሥትም ሆነ በዙሪያው ያሉ፣ እንዲሁም በሌላ ጎራ የተሠለፉ የስንዴ ልማቱን የልዩነት ማንፀባረቂያ ማድረግ የባቸውም፡፡ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት ማዋቀር ላይ መተባበርና አብሮ መሥራት የግድ ይሆናል፡፡ የማይረባ ዓላማ ይዞ አገር ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ አዲስ ሐሳብ ሲቀርብ በንቀት ማንኳሰስ፣  በቂም በቀል ተሞልቶ መጪውን ብሩህ ተስፋ ማደብዘዝ፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ የማይመጥኑ ኋላቀር ድርጊቶችን መፈጸም፣ ጽንፈኝነትና ስግብግብነት ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ የላቸውም፡፡ አንድን ነገር በተደጋጋሚ ሞክሮ ካልተሳካ ሌላ ዘዴ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ስህተትን እየደጋገሙ የተሻለ ውጤት መጠበቅም አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተደጋጋሚ የተገኙ መልካም አጋጣሚዎች የመከኑት፣ ከታሪክ ለመማር ባለመቻሉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተደጋጋሚ ስህተትን በስህተት ለማረም የተነሱም እንዳይሆኑ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከድህነት ሊያላቅቅ የሚችል ፕሮጀክት ሲዘረጋ፣ የእኔስ ድርሻ ምን መሆን አለበት ብሎ አስተዋጽኦ ለማበርከት መነሳት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ ከበፊቱ የተሻለች አገር ሆና ስሟ ታድሶ ወደ ታላቅነት መገስገስ የምትችለው፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በመከባበርና በመተባበር ስሜት በጋራ ሲሠሩ ነው፡፡ ጥላቻ፣ ንቀትና ክፋት የተጠናወተው ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ወገኖችም ከምንም ነገር በላይ የአገር ልማት አሳስቧቸው የባህሪ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የባዕዳንን ዓይንና ግንባር እያዩ ፖለቲካው ውስጥ የተዘፈቁ ወገኖችም፣ ከባዕዳኑ ይልቅ ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ቢተባበሩ ይበጃቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ልማቷን እያቀላጠፈች ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋታል፡፡ ከአንድ የንትርክ አጀንዳ ወደ ሌላው የሚደረገው የማያቋርጥ ቅራኔ አገርን ከማደህየት ውጪ ያመጣው ለውጥ የለም፡፡ በአፍሪካ ግዙፍ የሚባል ወጣት የሥራ ኃይል፣ ክረምት ከበጋ ሊታረስ የሚችል እጅግ በጣም ብዙ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የውኃ ሀብትና ተስማሚ የአየር ንብረቶች ያሏት ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በልማት ድህነትን ታሪክ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በመከባበርና በመተባበር ጠቃሚ ሐሳቦችን በመለዋወጥ በስንዴ ልማቱ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች አዝርዕቶችም ሆነ ምርቶች አመርቂ ውጤት እንዲገኝ መትጋት ተገቢ ነው፡፡

በዚህ ዘመን የመከባበርና የመተባበር ውጤት የሆነውን ጨዋነት ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ከንቱ ንትርክ ሳይሆን ዘለቄታዊ ልማት ነው፡፡ ከሸፍጥ፣ ከሴራ፣ ከቂም በቀል፣ ከክፋት፣ ከሌብነትና ከመሳሰሉት አውዳሚ ድርጊቶች መታቀብ ይበጃል፡፡ ለሁከት፣ ለግጭትና በአጠቃላይ ለሰላም መደፍረስ መንስዔ ከሚሆኑ ድርጊቶች አገር አታተርፍም፡፡ ሕዝብም ከሥቃይ በስተቀር ደስታን አያገኝም፡፡ ሕዝብንና አገርን የሚጎዱ ድርጊቶች ከቀውስ ውጪ ዕድገት አያመጡም፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም ሲባል፣ ልዩነትን ይዞ ለአገር በአንድነት መሥራት ይቻላል ማለት ነው፡፡ ነጋ ጠባ ምክንያት እየፈለጉ መጎነታተል ከጽንፈኝነት ውጪ ምንም ስያሜ አይሰጠውም፡፡ ሁልጊዜም የጋራ አማካይ እንዳለ መገንዘብ ይገባል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በመሳሰሉት ልዩነትን ለማስፋት የሚታገሉ ግለሰቦችና ስብስቦች ከታሪክ ቢማሩ ይጠቅማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጓት ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ናቸው፡፡ ሕዝቧም ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት ይፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጋራ ራዕይ መኖር አለበት፡፡ የጋራ ራዕይ ሲኖር ልማቱም የጋራ ጥረት ይፈልጋል፡፡ የአገር ልማት የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ አይሁን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...