Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የአምስት ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የአምስት ሰዎችን ሕይወት ቀጠፈ

ቀን:

ወረርሽኙን እየተቆጣጠረው መሆኑን የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል

በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በሦስት ወረዳዎችና በሶማሌ ክልል ሊበን ዞን በአንድ ወረዳ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የአምስት ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ቢሆንም፣ እየተቆጣጠረው መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ከመስከረም ወር አጋማሽ አንስቶ በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በርበሬ፣ ደሎ መና፣ እንዲሁም ሃረና ቡሉቅ ወረዳዎች የተከሰተው ወረርሽኝ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በሶማሌ ክልል ቀርሳ ዱላ ወረዳም ተከስቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በሁለቱ ክልሎች 215 ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውን ለሪፖርተር የተናገሩት የኢንስቲትዩቱ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን፣ በሶማሌ ክልል ውስጥ የተያዙት 17 ሰዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጀምሮ አምስት ሰዎች ሕይወታቸው እንዳለፈ፣ የአራቱ ሰዎች ሕልፈት ያጋጠመው በኦሮሚያ ክልል ሦስቱ ወረዳዎች ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ባለፉት ቀናት ውስጥ የወረርሽኙ ሥርጭት እየቀነሰ ነው፡፡ በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ካለው የሥርጭት መጠን በስተቀር፣ በቀሪዎቹ የዞኑ ሁለት ወረዳዎች አዲስ የሚያዙ ሰዎች ብዛት ዝቅተኛ እንደሆነና በሶማሌ ክልል ቀርሳ ዱላ ወረዳም ለተከታታይ ቀናት በኮሌራ የተያዘ አዲስ ሰው አለመኖሩን አስረድተዋል፡፡

‹‹ኮሌራ በወረርሽኝ መልክ የሚከሰት ስለሆነ፣ በአንድ ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ ይያዛሉ፡፡ አሁን ቁጥሩ አነስተኛ የሆነው ከዚህ በፊት ክትባት ስለሰጠን ነው፤›› በማለት፣ በአንድ ወር ገደማ ውስጥ የተያዙት ሰዎች ብዛት ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወረርሽኙ የታየባቸው አካባቢዎች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ኮሌራ የሚከሰትባቸው መሆናቸውን የሚገልጹት አቶ መስፍን፣ አስቀድሞ የኮሌራ ክትባት መሰጠቱ በሽታው እንዳይስፋፋ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

የተመረዘ ውኃን መጠቀም በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ወረርሽኙ ለመከሰቱ በምክንያትነት የተጠቀሰ ሲሆን፣ የውኃና የንፅህና አገልግሎት አቅርቦት ውስንነትና የንፅህና አጠባበቅ ጉድለት በወረርሽኙ በአረና ቡሉቅ ተነስቶ ወደ ሌሎቹ ወረዳዎች ለመስፋፋቱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ተመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሐሙስ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ሪፖርት፣ በየቀኑ አዳዲስ ሰዎች እየተያዙ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በወረርሽኙ ከሚያዙት ሰዎች ውስጥ 71 በመቶ የሚሆኑት ሕመምተኞች ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ድርቀት ምልክት እንደሚታይባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በተለይ በበርበሬና በደሎ መና ላሉ የኮሌራ ሕክምና ማዕከላት በቂ የውኃ መኪኖች ባለመኖራቸው፣ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚሰጠው ምላሽ በሚፈለገው ሁኔታ እየሄደ አይደለም፡፡ የመመርመሪያ ኪት ውስንነት፣ የኮሌራ ቁጥጥር ቴክኒካዊ ዕውቀት በቂ አለመሆን፣ በማዕከላቱ ውስጥ ለታማሚዎችና ለተንከባካቢዎቻቸው የምግብ አቅርቦት እጥረትና ሌሎችም ውስንነቶች እንቅፋት እንደሆኑ በሪፖርቱ ላይ አሥፍሯል፡፡አንዳንድ ለኮሌራ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎችም ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ አነስተኛ በመሆኑም፣ ወሳኝ የሆኑ አቅርቦቶችን በፍጥነት ለማድረስ በሚደረገው ጥረትና የሕክምና ቡድኖች ተደራሽነት ላይ ተፅዕኖ ማድረሱን አስታውቋል፡፡ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ምክንያት ወረርሽኙ ወደ ደቡብና ምሥራቅ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ እንዲሁም ወደ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ ዞኖች ሊዛመት ይችላል የሚለውን ሥጋቱን ገልጿል፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን፣ ወረርሽኙ ወደ ሌሎች ክልሎች ሊዛመት ይችላል በሚለው ሐሳብ አይስማሙም፡፡

‹‹ወረርሽኙን እየተከታተለና ለጽሕፈት ቤቱ መረጃ እየሰጠ ያለው ኢንስቲትዩቱ ነው፡፡ በእኛ በኩል ያለው ግምገማ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚስፋፋ አያሳይም፡፡ ባለፉት ተከታታይ ቀናት የተመዘገበ አዲስ ኬዝም የለም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...