Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሕገወጥ ትዕዛዝ መወረሱ ተረጋግጦ ለባለቤቶቹ የተመለሰው ኦሜድላ ሆቴል እንደገና ተወረሰ

በሕገወጥ ትዕዛዝ መወረሱ ተረጋግጦ ለባለቤቶቹ የተመለሰው ኦሜድላ ሆቴል እንደገና ተወረሰ

ቀን:

  • ፍርድ ቤቶችና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ፍትሕ የማግኘት መብትን አሳጥተዋል ተብሏል
  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ዓይተው መፍትሔ እንዲሰጡ አቤቱታ ቀርቦላቸዋል

ከ47 ዓመታት በፊት በ1968 ዓ.ም. በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ኮሎኔል አጥናፉ አባተ በተጻፈ ቀላጤ በሕገወጥ ትዕዛዝ ተወርሶ ከቆየ 23 ዓመታት በኋላ፣ ውርሱ ሕገወጥ መሆኑ ተረገግጦ በ1991 ዓ.ም. ለባለቤቶቹ ተመልሶ የነበረው ኦሜድላ ሆቴል እንደገና በሕገወጥ መንገድ መወረሱ ተገለጸ፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 05/06/07 ጎተራ አካባቢ የሚገኘው ኦሜድላ ሆቴል ከአዋጅ ቁጥር 47/67 ድንጋጌ ውጪ በቀላጤ መወረሱን፣ ባለቤቶቹ ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ተረጋግጦ በ1991 ዓ.ም. የተመለሰላቸው ቢሆንም፣ ለሰባት ዓመታት የራሳቸው አድርገው እየሠሩበት ከቆዩ በኋላ፣ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጋር በተያያዘ እንደተወሰደባቸው ባለቤቶቹ ከፍርድ ቤት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ ያቀረቧቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ደርግ ሥልጣን እንደያዘ በወቅቱ በነበሩ ባለሀብቶች (ከበርቴዎች) የተያዙ የንግድ ተቋማትንና መኖሪያ ቤቶችን በሁለት መንገዶች ማለትም፣ በአዋጅና በቀላጤ (ደብዳቤ) መውረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ፣ በቀላጤ የተወረሱ ቤቶችና የንግድ ተቋማትን እውነተኛነት እያረጋገጠ ለባለቤቶቹ ሲመልስ፣ ኦሜድላ ሆቴልም በወቅቱ በሕይወት ለነበሩ ባለቤቶቹ፣ ለአቶ በላይ አባተና ለአቶ አባተ ወልዴ ወራሾች መመለሱን ሰነዶች ይመሰክራሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኦሜድላ ሆቴል ባለቤቶች በ1991 ዓ.ም. ሆቴሉ ተመልሶላቸው እስከ 1998 ዓ.ም. ድረስ ሲሠሩበት ቢቆዩም፣ የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ በላይ አባተ የ1997 ምርጫ ውጤትን አስመልክተው፣ ‹‹ሥልጣን ለመራጩ ሕዝብ›› የሚል ንግግር አድርገዋል በሚል ‹‹ቂም››፣ ሆቴሉ ለባለቤቶቹ የተመለሰው በተሳሳተ ማስረጃ እንደሆነ በማስመሰል፣ ከሐምሌ 14 ቀን 1998 ዓ.ም. ጀምሮ በድጋሚ መወረሱ ታውቋል፡፡

ሆቴሉ በድጋሚ እንዲወሰድ ቀጭን ትዕዛዝ ያስተላለፉት በወቅቱ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት በሚኒስትር ደኤታ ማዕረግ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ወ/ሮ እንወይ ገብረ መድኅን ሲሆኑ፣ ሰኔ 30 ቀን 1998 ዓ.ም. ለፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርቶች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በጻፉት ደብዳቤ፣ ኦሜድላ ሆቴል በትርፍነት በአዋጅ ቁጥር 47/67 የተወረሰ መሆኑንና በወቅቱ የተወረሰበት ሰነድ ማቅረብ ስላልተቻለ እንደተመለሰላቸው፣ ነገር ግን የተወረሰበት ሰነድ ስለተገኘና በአዋጅ የተወረሰ መሆኑን መረዳት በመቻሉ፣ እንዲሁም 250 ብር አበል ለባለቤቶቹ ሲከፈላቸው መቆየታቸውን በመዘርዘር፣ ሆቴሉ በድጋሚ እንዲወሰድ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ሪፖርተር ያገኛቸው ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከዳይሬክተሯ የደረሰውን ደብዳቤ መሠረት አድርጎ፣ ሆቴሉ ለባለቤቶቹ ከተመለሰ ከሰባት ዓመታት በኋላ፣ እንደገና እንዲወረስ ትዕዛዝ ማስተላለፉን በአሁኑ ጊዜ የኦሜድላ ሆቴል ወራሾች ወኪል የሆኑት አቶ መሀሪ በላይ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሌሎች የመንግሥት ባለሥልጣናት የጻፏቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ኤጀንሲው ሆቴሉን እንደገና ከወሰደ በኋላ ተወካዩ ‹‹ለምን?›› የሚል ጥያቄ ቢያነሱም ከኤጀንሲው ምላሽ የሚሰጣቸው በማጣታቸው፣ የተፈጸመባቸው በደልና ድርጊት ከእውነት የራቀና ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ‹‹የቂም በቀል ዕርምጃ›› መሆኑን በመጥቀስ፣ ውሳኔው እንዲሻርላቸው፣ ለኤጀንሲው ቦርድ ቢያቀርቡም መፍትሔ አለማግኘታቸውን ሰነዶቹ ያስረዳሉ፡፡

ድርጊቱ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ በመሆኑና የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው በመተማመን፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ያቀረቡት አቤቱታም ምላሽ ማጣቱን የሚናገሩት ወራሽ ባለቤቶቹ፣ መሠረታዊ የሕግ ጥሰት ተፈጽሟል በማለት፣ ወደ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቢያመሩም፣ ሁሉም ሊቀበሏቸው እንዳልቻሉ ያብራራሉ፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ በአዋጅ ቁጥር 110/87 ድንጋጌ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት፣ ‹‹ኤጀንሲው የሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት ውሳኔ ፍርድ ቤቶች ሊሽሩት አይችሉም፤›› በመባሉ ምክንያት፣ ኦሜድላ ሆቴል ከሕግ አግባብ ውጪ በሐሰተኛ ሰነድና የሆቴሉ ባለቤቶች (ወራሾች) ሳያውቁ በድብቅ በተጻፈ ደብዳቤ (ወ/ሮ እንወይ ገብረ መድኅን በጻፉት ደብዳቤ) መሠረት መወረሱን ጠቅሰውም ቢያቀርቡ፣ ‹‹ይህንን ጉዳይ ማየት አንችልም፤›› በማለት ፍሬ ነገሩን ሳይመለከቱ አየር በአየር ውድቅ እንዳደረጉባቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የጻፉት አቤቱታ ያሳያል፡፡ ምንም እንኳን ለፍርድ ቤቶቹ፣ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቧቸው ‹‹ጥያቄዎቻቸው›› የተለያዩ ቢሆኑም፣ የድርጅቱ ስም ተመሳሳይ በመሆኑ ብቻ፣ ‹‹ይህንን ጉዳይ በድጋሚ አናይም፤›› በማለት ንብረታቸው ከሕግ ወጪ እንደተወሰደባቸው አብራርተዋል፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40(2) ድንጋጌ መሠረት፣ ንብረት ማፍራት እንደሚችሉ የሰጣቸውን ሕገ መንግሥታዊ መብት ጭምር፣ በጉልበትና በበቀል እንደተወሰደባቸው የሚናገሩት ባለቤቶቹ፣ ሌላው ቢቀር ጉዳያቸውን እንዲያስረዱ ጊዜ እንዲጣቸው ያቀረቡትን ጥያቄን እንኳ ሊቀበላቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 37 ድንጋጌ መሠረት ፍትሕ የማግኘት መብታቸውና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 25 ድንጋጌ መሠረት በሕግ ፊት እኩል የመታየት መብታቸውን ጭምር ለማስከበር፣ ይግባኝና አቤቱታቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡም፣ ምክር ቤቱ ለመስማት እንኳን ፍላጎት እንደሌለውና ሊያናግራቸው ባለመፈለግ አጭር ደብዳቤ ጽፎና በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፊርማ፣ አቤቱታቸውን ውድቅ እንዳደረገባቸውም አብራርተዋል፡፡

የኦሜድላ ሆቴል ባለቤቶች በድጋሚ የተፈጸመባቸውን ሕገወጥ ሒደት በመቃወም ከ1998 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. ድረስ ለ16 ዓመታት ፍትሕ ፍለጋ ሲንከራተቱ ቢቆዩም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኙ፣ ንብረታቸውን ለፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እንዲያስረክቡ፣ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት በተጻፈ ደብዳቤ መሠረት በድጋሚ እንደተወሰደባቸው በመግለጽ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደራዊ መፍትሔ እንዲያሰጧቸው አቤቱታ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ከደብዳቤው ተገንዝቧል፡፡

ንብረታቸው (ኦሜድላ ሆቴል) በሕገወጥ መንገድ በመወረሱ ምክንያት ከ60 በላይ ቋሚና ከ20 በላይ ጊዜያዊ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ መሆናቸውንም ወራሾች ለተለያዩ ተቋማት ያቀረቧቸው የአቤቱታ ደብዳቤዎች ያስረዳሉ፡፡ እነሱም (ወራሾች) ከሆቴሉ ሌላ ሠርተው የሚተዳደሩበት ምንም ዓይነት ገቢ እንደሌላቸው ጠቁመው፣ ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸው አገር ጥለው መሰደድ ወይም ጎዳና ላይ መውጣት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ባለንብረቶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብደቤ ላይ እንዳብራሩት፣ ኦሜድላ ሆቴል በአዋጅ ቁጥር 47/67 እንዳልተወረሰ ተረጋግጦ በ1991 ዓ.ም. ተመልሶላቸዋል፡፡ ሆቴሉ ከተመለሰላቸው ሰባት ዓመታት በኋላ በ1998 ዓ.ም. በሐሰተኛ ማስረጃና በበቀል ምክንያት ውሳኔው መለወጡንና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠው ፍትሕ የማግኘትና የመሰማት መብት፣ ማስረጃ የማግኘት መብት፣ ሕግን መሠረት አድርጎ መሥራትና ተገቢ የሆነ ፍትሕ የመስጠት  ሒደት ታልፎ፣ በተገማች የፍትሕ ሥርዓት ላይ የተመሠረተ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባት አገራዊ ጉዳይን ትቶ፣ የዜጎችን የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብትን የሚያስቀር፣ የመንግሥት ሥራ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ መመራት ያለበት መሆን ሲገባው፣ በርካታ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎችን የሚጥስና ያልተረጋጋ የፍትሕ ሥርዓት እንዲኖር የሚያደርግ በደል መሆኑን ተመልክተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደራዊ ፍትሕ እንዲሰጧቸው ተማጽነዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...