በአማራ ክልል ሽንዲ ወንበርማ በተባለች ከተማ ነው የተወለደችው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ስትከታተል በስፖርት ክፍለ ጊዜ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ታደርግ ነበር፡፡ በትምህርት ቤት በሚከናወኑ የሩጫ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ የተመለከታት መምህሯ በአትሌቲክሱ ብትቀጥል ውጤታማ ልትሆን እንደምትችል ይነግራት ነበር፡፡ በ2005 ዓ.ም. የአትሌቲክስ መልማዮች ባህር ዳር መምጣታቸውን ሰምታ፣ ወደ ሥፍራው ያቀናቸው የዓለም ዘርፍ የኋላዋ፣ በአንዴ የመልማዮቹን ቀልብ መግዛት ችላ ነበር፡፡ በ2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ስፖርት አካዴሚን ተቀላቅላ በ1,500 ሜትር ርቀት ልምምዷን ጀመረች፡፡ በአካዴሚው ሁለት ዓመታት ቆይታ ያደረገችው አትሌቷ፣ የምትሮጥበትን ርቀት ወደ 5,000 ሜትር አሳድጋ፣ የተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ መካፈሏን ቀጠለች፡፡ የአካዴሚ ሥልጠናዋን ካጠናቀቀች በኋላ፣ በ2010 ዓ.ም. ሐዋሳ ከተማ ክለብን ተቀላቅላ፣ በተለያዩ የአገር ውስጥ ውድድሮች በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ሜትር ስትካፈል ቆየች፡፡ አትሌቷ ፈጥና ፊቷን ወደ ጎዳና ውድድሮች አዙራ በአሠልጣኟ ተሰማ አብሺሮ እየተመራች፣ የታላቁ ሩጫ ተሳትፎን ጨምሮ በ16 ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ላይ ተካፍላ፣ በ13ቱ በድል መውጣት ችላለች፡፡ የዓለም ዘርፍ በርካታ የግማሽ ማራቶን ክብረ ወሰን በእጇ መጨበጥ የቻለች ሲሆን፣ የሴቶች 10 ኪሎ ሜትር ክብረ ወሰን ባለቤትና ለመጀመሪያ ጊዜ በሀምቡርግ ማራቶን ላይ ተካፍላ፣ የቦታውን እንዲሁም ብሔራዊ ክብረ ወሰን ማሳካት ችላለች፡፡ ከሳምንት በፊት ሁለተኛዋን ማራቶን ለንደን ላይ ያደረገችው አትሌቷ፣ ከወደቀችበት ተነስታ አሸንፋለች፡፡ ዳዊት ቶሎሳ ስለአትሌቲክስ ሕይወቷ አነጋግሯታል፡፡
ሪፖርተር፡- በበርካታ አንጋፋ አትሌቶች የሚስተዋለው ከመካከለኛ ርቀት ጀምረው፣ በመም ርቀቶች ላይ ለዓመታት ተካፍለው፣ ማምሻውን ወደ ጎዳና ውድድሮች ሲገቡ ነበር፡፡ በአንፃሩ አንቺ ፈጥነሽ ወደ ጎዳና ሩጫው ገብተሻል፡፡ እስኪ አጋጣሚውን አብራሪልን?
የዓለም ዘርፍ፡– ከአካዴሚ ከወጣሁ በኋላ በሐዋሳ አትሌቲክስ ክለብ እያለሁ 5 ሺሕና 10 ሺሕ ሜትር እሳተፍ ነበር፡፡ በተለያዩ አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ እየተሳተፍኩ፣ አምስተኛ፣ ስድስተኛና ስምንተኛ ደረጃን ይዤ አጠናቅቅ ነበር፡፡ በ2011 ዓ.ም. በተደረገው የታላቁ ሩጫ በሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድር የመጀመሪያ ተሳትፎ አራተኛ ወጣሁ፡፡ በ2012 ዓ.ም. የታላቁ ሩጫ 10 ኪሎ ሜትር አንደኛ እንዲሁም የሴቶች 5 ሺሕ ሜትር ውድድር ሁለተኛ ደረጃ ሆኜ ማጠናቀቅ ቻልኩ፣ በውጤቱ ደስተኛ ነበርኩ፡፡ በትራክ ውድድሮች ላይ መሳተፍ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ በ2012 እና 2013 ዓ.ም. በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የ5 ሺሕ፣ 10 ሺሕና የአገር አቋራጭ ውድድሮች መሰረዛቸውን ተከትሎ፣ በአንፃሩ የተለያዩ አገሮች የጎዳና ውድድሮችን በተወሰነ ደረጃ ማከናወን መጀመራቸውና የጎዳና ውድድሮች ላይ ትኩረት እንዳደርግ አድርጎኛል፡፡ በዚህም ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካትቼ በመላ አፍሪካ ዋንጫ በግማሽ ማራቶን ወርቅ ካገኘሁ በኋላ፣ በግሌ የመጀመሪያዬን የግማሽ ማራቶን ውድድር በህንድ ኒው ዴልሂ አድርጌ ማሸነፍ ቻልኩ፡፡ ከዚያም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ላይ መሳተፌን ቀጠልኩ፡፡
ሪፖርተር፡- በአጭር ጊዜ በርካታ ውድድሮችን በስኬት መውጣት ችለሻል፡፡ ወደ አትሌቲክስ ከገባሽበት ወቅት አንስቶ ለአንቺ የተለየ ደስታ የሰጠሽ የቱ ነው?
የዓለም ዘርፍ፡– የማስታውሰውና ልዩ ስሜት የፈጠረብኝ አጋጣሚ ባህር ዳር መልማዮች መጥተው ውድድር ስናደርግ ነበር፡፡ ውድድሩን ስናከናውን በጣም ፈርቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም አሸንፈው የተመረጡ አትሌቶች አዲስ አበባ ሄደው አካዴሚ ይገባሉ ስለተባለ ነበር፡፡ ከዚያም ባሻገር ኢትዮጵያን ወክዬ በመላ አፍሪካ ጨዋታ ላይ ስካፈል፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ወጥቼ የተካፈልኩበት ስለነበር ፍርኃት አድሮብኝ ነበር፡፡ ሆኖም ውድድሩን በድል ተወጣሁት፡፡ እነዚህን አጋጣሚዎች አልረሳቸውም፡፡
ሪፖርተር፡- በጎዳና ውድድሮች የሚካፈሉ አትሌቶች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም ባሻገር የርቀቱ ሰዓት እየተሻሻለ ነው፡፡ አንቺም በበርካታ ውድድሮች ላይ ተካፍለሽ፣ አዳዲስ ክብረ ወሰኖች ማሳካት ችለሻል፡፡ የስኬቱ ምስጢር ምንድነው?
የዓለም ዘርፍ፡- አትሌቲክስ ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ጥንቃቄና እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ የሚፈልገውን ሁሉ መስጠት ያሻል፡፡ ዝግጅቱ ጥሩ ሊሆን ይገባል፡፡ መጀመሪያ ወደ ውድድር ከመግባቴ በፊት ከአሠልጣኜ እንዲሁም ከማናጀሬ ጋር እወያያለሁ፡፡ ወደ ውድድር ከመግባቴ በፊት ሕመም ሊያጋጥመኝና በግል ምክንያት ሊበላሹ የሚችሉ ነገሮች ስለሚኖሩ፣ ማጤንና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አንድ የማራቶን ውድድር ለማድረግ የሁለት ወራት ዝግጅት ይደረጋል፡፡ በሳምንት ከእሑድ በስተቀር ጠዋትና ከሰዓት ልምምድ አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ የውጤቱ ምስጢር ተጠንቅቆ በቂ ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመሪያ የማራቶን ውድድርሽን ዓምና በጀርመን ሀምቡርግ እንዲሁም ሁለተኛውን ማራቶን ከሳምንት በፊት በለንደን አድርገሽ፣ ከወደቅሽበት ተነስተሽ አሸንፈሻል፡፡ የሁለቱ ማራቶን ተሳትፎ እንዴት ነበር?
የዓለም ዘርፍ፡– የመጀመሪያዬን የማራቶን ተሳትፎ ያደረግኩት በ10 ኪሎ ሜትር የዓለም ክብረ ወሰን መጨበጥ ከቻልኩ በኋላ ነበር፡፡ የሀምቡርግ ማራቶን በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሁለት ወራት ነው የተዘጋጀሁት፣ ኮርሱ ይከብድ ነበር፡፡ ሆኖም ደስ የሚል ውድድር ነበር፡፡ በተመሳሳይ ለለንደን ማራቶን ጥሩ ዝግጅት አድሪጌ ነበር የገባሁት፡፡ ከዚህ ቀደም ቦታውን ስለማላውቀው አንዴ ለቀቅ፣ አንዴ ያዝ እያደረግኩ ነበር የሮጥኩት፡፡ ሆኖም 33 ኪሎ ሜትር አካባቢ ወድቄ ነበር፡፡ መውደቄ ትንሽ ድንጋጤ ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ግን ከወደቅኩበት ተነስቼ፣ ፍርኃቴን አጥፍቼ ወደ ውድድሩ ተመልሼ ማሸነፍ ችያለሁ፡፡ በጣም ጥሩ ውድድር ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በውድድሩ ወቅት ለመውደቅሽ ምክንያቱ ምን ነበር? ስትወድቂ ምን ተሰማሽ?
የዓለም ዘርፍ፡- ከፊት ለፊቴ የመኪና ፍጥነት መቆጣጠሪያ (ስፒድ ብሬከር) ነበር፡፡ ፍጥነት መቆጣጠሪያውን አላየሁትም ነበር፡፡ አጋጣሚው ሲፈጠር ደንግጬ ነበር፡፡ ልፋቴን፣ ቤተሰቤን፣ የአሠልጣኞቼን ልፋትና የእኔን ውጤት የሚጠባበቀውን የአገሬን ሕዝብ ነበር ያሰብኩት፡፡ ወድቆ መነሳት በጣም ከባድ ነው፡፡ ልክ እንደ ወደቅኩ ሰውነቴ ሌላ ስሜት ነበር ያመጣው፡፡
ሪፖርተር፡- ከግል ውድድሮች ላይ ከመሳተፍ በዘለለ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተሽ፣ በመላው አፍሪካ ጨዋታና በዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮና ላይ ብቻ መካፈልሽ ይታወሳል፡፡ ሆኖም በቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም በዓለም ሻምፒዮና የአንቺ አለመመረጥ ቅሬታ አስነስቶ ነበር፣ ምርጫውን እንዴት ተመለከትሽው?
የዓለም ዘርፍ፡- በግል ውድድሮችን ከማድረግ ባሻገር፣ አገሬን ወክዬ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ መካፈል ፍላጎት አለኝ፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ 10 ሺሕ ሜትር እመረጣለሁ የሚል ሐሳብ ነበረኝ፡፡ ማጣሪያውን አራተኛ ነበር የወጣሁት፡፡ አጋጣሚውን ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በተመሳሳይ በዓለም ሻምፒዮናውም በግማሽ ማራቶን እንዲሁም በማራቶን ጥሩ ሰዓት ቢኖረኝም ልመረጥ አልቻልኩም፡፡ ምክንያቱ ለእኔ ግልጽ አልነበረም፡፡ ቀድሞ ጥሩ ሰዓት ያመጣ አትሌት ነው፣ አስቀድሞ እንደተመረጠ የሚያውቀው፡፡ የአመራረጥ ሥርዓትና አተገባበር ላይ ክፍተት አለ ባይ ነኝ፡፡ በጊዜው ባለመመረጤ ቅር ብሎኝ ነበር፡፡ ሆኖም ትኩረት ማድረግ የፈለግኩት የቀጣይ ዝግጅቴን አጠናክሬ መቀጠል ላይ ነበር፡፡ በቀጣይ ዕድሉን አገኛለሁ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- መቀመጫውን ኔዘርላንድ ባደረገው የኤንኤን ሩጫ ድርጅት የተለያዩ በርካታ ውጤታማ አትሌቶች በሥሩ አቅፎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አንቺም የድርጅቱ አባል ነሽ፡፡ ከድርጅቱ ጋር በመሥራትሽ ምን ፈይዶልኛል ትያለሽ?
የዓለም ዘርፍ፡- ድርጅቱ ለአትሌቶች የተለያዩ አስተዳደራዊ ድጋፎችን ያደርጋል፣ አትሌቶችን ጤንነት ይከታተላል፣ ውድድሮችን ያመቻቻል፣ የመሮጫ ትጥቆችን ያቀርባል፣ አባል ከሆኑ አትሌቶች ጋር በጋራ ልምምድ እንድናደርግ ያደርጋል፣ እንዲሁም አትሌቶችን ያበረታታል፡፡ ለአትሌቶች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ አባል በመሆኔ ብዙ ነገር ተጠቅሜያለሁ፣ እስካሁን ባለው ነገርም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ዕቅድሽ ምንድነው?
የዓለም ዘርፍ፡- በቀጣይ የተለያዩ ትልልቅ ዓለም አቀፍ የማራቶን እንዲሁም የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ይኖሯሉ፡፡ በእነዚያ ውድድሮችም በለንደን ማራቶን ያመጣሁትን ስኬት መድገም እፈልጋለሁ፡፡ ከዚያም ባሻገር በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በኦሊምፒክ ጨዋታ ተሳትፌ የራሴን ታሪክ ማኖር ፍላጎትና ዕቅድ አለኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በአትሌቲክሱ እንደትቀጥይ ያነሳሳሽ እንዲሁም እንደ ምሳሌ የምታነሺው ሰው አለ?
የዓለም ዘርፍ፡- የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ በርቺ እያሉ የሚያበረታቱኝ ጋሽ ሰዒድ የሚባሉ መምህሬን አስታውሳለሁ፡፡ እዚህ ደረጃ እንድደርስ የእሳቸው ማበረታታትን አልረሳውም፡፡ እሳቸው ባለውለታዬ ናቸው፡፡ በአትሌቲክሱ ኃይሌ ገብረሥላሴና መሠረት ደፋር ምሳሌዎቼ ናቸው፡፡