ከድሮ ጀምሮ ‘አንድ ሰው ጥፋተኛ መሆኑ ካልተረጋገጠ በስተቀር ንፁህ ነው’ በሚለው አባባል ለመመራት እጥራለሁ፡፡ በተመሳሳይ ተቃራኒ ማስረጃ ካልቀረበ በስተቀር አአራችን አሁን ባለችበት ዘመን በቋንቋ እንለያይ ይሆናል እንጂ ሁላችንም እኩል ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ሁላችንም አገራችንን እኩል እንወዳለን፡፡ ለልማቷም እኩል እንጥራለን በሚለውም አምናለሁ፡፡ አንዳንዴ ግን ግራ የሚያጋባ ነገር ያጋጥመኛል፡፡ ታላቅ ወንድሜ የጡረታ ዘመኑን ከባለቤቱ ጋር ለማሳለፍ አንድ ከአዲስ አበባ ጋር የሚዋሰንና በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ መለስተኛ ከተማ ውስጥ ቤት ገዝቶ ይገባል፡፡ በእቅዱም መሠረት ግማሽ ዓመት በዚሁ ከተማ፣ ግማሹን ዓመት ደግሞ በውጭ አገር ከሚኖሩት ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ጋር ለመኖር ያቅድና የጡረታ ዘመኑን ሁለት ቦታ መኖር ይጀምራል፡፡
ታዲያ በቅርቡ እሱና ባለቤቱ ካሉበት ውጭ አገር ደውለው የቤታቸውን የቦታ ግብርና ኪራይ እንድከፍልላቸው ይጠይቁኛል፡፡ እኔም ውክልናዬንና አስፈላጊ ሰነዶችን ይዤ ግብርና ኪራይ ለመክፈል ወደ ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ሄድኩ፡፡ ከትንሽ ውጣ ውረድ በኋላ የሚመለከተውን ግለሰብ አገኘሁና ለወንድሜ የቦታ ግብርና ኪራይ ለመክፍል እንደመጣሁ አስረዳሁት፡፡ እሱም የውክልና ወረቀትህን አሳየኝ አለኝ፡፡ እኔም በጥንቃቄ የያዝኩትን የውክልና ወረቀት ከቦርሳዬ አውጥቼ አሳየሁት፡፡ እሱም ይህ በአማርኛ ስለሆነ ወደ ኦሮምኛ አስተርጉመህ አምጣ አለኝ፡፡ እኔም እሺ ብዬ አስተርጉሜ አመጣሁ፡፡
በመቀጠል የመታወቂያ ደብተሬን እንዳሳየው ጠየቀኝ፡፡ የመታወቂያ ደብተሬን ከኪሴ አውጥቼ አሳየሁት፡፡ ይህም ወደ ኦሮምኛ መተረጎም አለበት አለኝ፡፡ እኔም መታወቂያው ላይ ያለው መረጃ በአማርኛም በእንግሊዝኛም ስለሆነ መረጃውን ከአማርኛው መውሰድ ካልፈለገ ከእንግሊዝኛው ሊያገኘው እንደሚችል ላስረዳው ሞከርኩ፡፡ አሁንም አይሆንም ሂድና አስተርጉመህ አምጣ አለኝ፡፡ ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ መታወቂያዬን ወደ ኦሮምኛ አስተርጉሜ አመጣሁ፡፡
ከዚያ የሚከፈለውን የቦታ ግብርና ኪራይ መጠን ነገረኝ፡፡ እኔም ጥሬ ገንዘብ በኪሴ ስለነበር ለመክፈል ስዘጋጅ በጥሬ ገንዘብ መክፈል እንደማይቻል ነገረኝ፡፡ እሺ ብዬ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሄጄ ሲፒኦ (CPO) አሠርቼ አመጣለሁ አልኩ፡፡ እሱም አይቻልም አለኝ፡፡ ታዲያ ምን ላድርግ አልኩት፡፡ ኦሮምያ ኅብረት ሥራ ባንክ የቁጠባ ሒሳብ አለህ ወይ ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እኔም እንደሌለኝ ነገርኩት፡፡ በል እንግዲህ እዚያ ሂድና የቁጠባ ሒሳብ ክፈት፣ ከዚያ ቢያንስ የግብርና ኪራይ መጠን ያክል ገንዘብ አስገባና ተመልሰህ እኔጋ ና አለኝ፡፡ ትንሽ ግራ ቢገባኝም ምንም ምርጫ ስላልነበረኝ የተባልኩትን አደረኩ፡፡ ከዚያ ገንዘቡን የማስገባበትን ሒሳብ ቁጥር ሰጠኝና ግብሩና ኪራዩን ከፈልኩ፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ለማድረግ ወደ ከተማው አስተዳደር 12 ጊዜ ተመላልሻለሁ፡፡ ልብ በሉ፣ ይህ ሁሉ ምልልስ እባካችሁ ገንዘብ ልስጣችሁ ባልኩ ነው፡፡
እንግዲህ ይታያችሁ፡፡ እሺ ውክልናዬ በአማርኛ ስለነበረ አሁን ባለው አሠራር መሠረት ወደ ክልሉ ቋንቋ ይተርጎም፡፡ መታወቂያዬ ግን በእንግሊዝኛም ጭምር ስለነበር ቅንነት ቢኖር ኖሮ በግድ መተርጎም አልነበረበትም፡፡ ለእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ካልጠቀመ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መታወቂያው ላይ የገባው ለቄንጥ ነው? ከሁሉም የባሰው ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲፒኦ (CPO) አንቀበለም፣ በግድ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ሄደህ ሒሳብ መክፈት አለብህ የሚለው ነው፡፡ ልብ በሉ፡፡ አንድ የመንግሥት የሆነ አካል አንድን ተገልጋይ ዜጋ በአክሲዮን መልክ ለትርፍ በተቋቋመ ተቋም የባንክ ሒሳብ እንድከፍት እያስገደደኝ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ በላይ ሙስና አለ? ያውም በግላጭ!! እንዲህ ዓይነት ርካሽ ዘዴ አንዳንድ ሰዎች ለጊዜው ተጠቃቅመውበት ይሆናል እንጂ ወደፊት ለባንኩም ቢሆን አያዋጣውም፡፡ መስተካከል አለበት፡፡
ይገባኛል፡፡ ይህ ችግር አሁን አገራችን ካለችበት ችግሮች ጋር ሲነፃፀር ኢምንት ሊመስል ይችላል፡፡ እኔም በችግር ላይ ችግር ለምን እጨምራለሁ በሚል ባላነሳው ይሻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች አሁን በሚቻልበት ጊዜ በአጭሩ ካልተቀጩ የሚያመጡት መዘዝ ዛሬ ከሚያተረማምሰን የብሔር ፖለቲካ ትኩሳት ጋር ተደማምረው ከማንወጣበት አዙሪት ውስጥ ሊከቱን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የሚሰማኝ ሰው ካለ የአቅሜን ምክር ልለግስ፡፡
ምክር አንድ፡- ይህና ተመሳሳይ ችግሮች በቀላሉ ሊስተካከሉ ይችላሉ፡፡ የሚያስፈልገው በተለይ አገልግሎት ከሚሰጡ አካላት ትንሽ ቅንነት ነው፡፡ ቅንነት ለሰው ልጅ በመከባበር አብሮ ለመኖር ዋነኛው እሴት እንደመሆኑ መጠን በቀላሉ ሊገኝ እንደማይችል ይገባኛል፡፡ አንድ ሰው ቅን ለመሆን መጀመሪያ በራሱ የሚተማመን ሰው መሆን አለበት፡፡ ይህ ቀላል አይደለም፣ ብስለትን ይጠይቃል፡፡ ካልሆነ የሰው መንገላታት የማይስማው ሰው ለጊዜው ትልቅነት ተሰምቶት ሊሆን ይችላል እንጂ በሥራውም በኑሮውም ደስተኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የኋላ ኋላ ተሸናፊው እሱ ነው፡፡ በአንፃሩ ቅን ለመሆን የሚጥር ሰው በማንኛውም መመዘኛ በኑሮውም በሥራውም ደስተኛ ነው፡፡ የኋላ ኋላ አሸናፊው እሱ ነው፡፡
ምክር ሁለት፡- ከላይ እንደጠቀስኩት ይህ ሁሉ ጣጣ ገንዘብ ልክፈል ባልኩ ነው፡፡ ከከተማው ነዋሪ በግብር መልክ የሚሰበስበው ገንዘብ የሚጠቅመው በመጀመሪያ ደረጃ የከተማዋን ነዋሪዎች መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነዋሪው ውኃ፣ መንገድ፣ ክሊኒክ ትምህርት እንዲሠሩለት ይፈልግ የለ? የከተማው አስተዳዳሪዎች ይህ አይገባቸውም? ሥራቸውስ ይህ አይደለም? ስለእውነት ከሆነ ወንድሜ ሦስት መኝታ ቤት ላለውና 500 ካሬ ሜትር ላይ ላረፈ ዘመናዊ ቪላ የሚከፍለው የቦታ ግብርና ኪራይ በጣም ትንሽ ነው፡፡ አንድ ዘመዴ ሲነግረኝ የቦታ ግብርና ኪራይ ከሚከፍለው ገንዘብ ይልቅ ለግብር ተመን አገልግሎት የሚከፍለው ገንዘብ ይበልጣል! አሁን ይህ ምን ይባላል?
እኔ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ ወንድሜ ለዚህ ቤት አሁን ከሚከፍለው ግብርና ኪራይ ሁለት ሦስት እጥፍ ምንም ቅር ሳይለው ለመክፈል ፈቃደኛ ይሆናል፡፡ አቅሙም አለው፡፡ ይህ ለሌሎችም ተመሳሳይ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ገንዘብ የከተማው አስተዳደር ሊሠራ የሚችላቸው የልማት ሥራዎች የከተማው ነዋሪዎች (ወንድሜንም ጨምሮ) ተጠቃሚ መሆናቸው ይገባዋል፡፡ ስለዚህ የከተማው አስተዳደር የቦታ ግብርና ኪራይ ለመክፈል የሚመጡትን ሰዎች በትንሹም በትልቁም ከማጎሳቆል ይልቅ የታክሱን መጠን አሻሽለውና አስተካክለው አገልግሎታቸውን በተቀላጠፈ መንገድ ቢያበረክቱ ግብርና ኪራይ ከፋዩም ነዋሪዎቹም ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩም ለልማት የሚሆን ገንዘብ ተጨማሪ ያገኝና ሥራውም ይሳካለታል፡፡ ሁሉም አሸናፊ ይሆናል፡፡
ይህንን ለማድረግ የአስተዳደር ኃላፊነት ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ቅንነትና ራዕይ ያላቸው የሕዝብ አገልጋይ ግለሰቦች መሆን አለባቸው፡፡ አለበለዚያ ልክ ያለፈው ታሪካችን እንደሚያሳየው የአገራችንን ዕጣ ፈንታ ቅንነትም ሆነ ራዕይ ለሌላቸው ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ትተንላቸው ከክፋትና ከድንቁርና ቀንበር ሳንወጣ እየማቀቅን መኖር እንቀጥላለን፡፡ ትልቁ የአገር በደል ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡
(አክሊሉ ኪዳኑ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ከአዲስ አበባ)