በአሰፋ አደፍርስ
ሰዎች በየጊዜው ይማራሉ፣ ተምረውም ይሻሻላሉ፣ ይለወጣሉ፡፡ ከክፋት ደግነትን፣ ካለ መልማት መልማትንና የመሳሰሉትን ከጊዜ ጋር በመራመድ የማገናዘብ ችሎታን በከፍታ አዳብረው፣ ከአገርና ከወገንን አልፈው ተርፈውና ለዓለም በቅተው ብዙ አገሮች ከኋላችን ተነስተው ቀድመውናል። እኛም የቅም አያቶቻችን፣ የቅድመ አያቶቻችን፣ የአያቶቻችንና የአባቶቻችንን ታሪክ በጥሩ ወይም በሚያስከፋው ሁሉ ተያይዘነው እነሆ እዚህ ደርሰናል።
ሰው ካለፈው ይማራል፣ ያስተምራልም፡፡ የእኛ ግን ያለፈውን ማውገዝና ነባሩን የማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ከጀመርን ወደ 50 ዓመታት ወይም ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ደርሰናል። ያለፈው አጠፋ አልበጀም ካልን የተሻለ ለመሥራት ብንሞክር እንኳ መልካም ነበር። የእኛ ግን ‹ይሻልን አገባ ብላ ይባስን አገባች› እንደሚባለው እየሆነብን ከአንዱ ሌላው የማይሻልበት መቀመቅ እየገባን እዚህ ደርሰናል።
መቼም ይህችን ማስታወሻ የምታነቡ ሁሉ ምናልባት ይህ ሰው ሥራ የለውም ትሉኝ ይሆናል። ግድ የለም እንኳን አላችሁ ነው መልሴ። ብዙ ማየት መጥፎ ነው፣ ብዙ አይቼያለሁ፡፡ ችግሩንም፣ መከራውንም፣ ማጣትና ማግኘትንም አይቼያለሁ። በማየቴም የማመዛዘን፣ የአገርን ጉዳይ በየፈርጁ ማየት፣ ከሌሎች ጋር ማስተያየት፣ ማወዳደርና የመሳሰሉትን አከናውኛለሁ፡፡
ታዲያ ያየሁትንና የተመለከትሁትን ሳገናዝብ ታላቋ አገሬ ኢትዮጵያ ታዳጊ አገር እየተባለች ሁሌ ሲነገርላት ስሰማ በጣም እየገረመኝ፣ እንዲያው ይህንን ያለተገባ የአሉባልታ ዓይነት ወሬ እየሰማሁ ልለፈው እያልኩ ከቆየሁ በኋላ፣ ምናልባት ያለማወቅ እንደሆነ የሚጫወትብን? ከሆነስ የማውቀውን ያህል ከወገኖቼ ጋር ብካፈልስ በማለት ይህችን አጠር ያለች ማስታወሻ ለመጻፍ ተነሳሳሁ።
በጣም መጠንቀቅ ያለብን ሕገ መንግሥት ተብሎ አገሪቱን ለመበታተን በጫካ ውስጥ የተደነገገው ሕገ መንግሥት ሁሉም አውቆት፣ ተገንዝቦትና ወድዶ ያደረገው ነው? ወይስ ጊዜ የሰጣቸው ቡድኖች የፈጠሩት? ብለን በጥንቃቄ ማየት ያለብን ጉዳይ ነውና ይታሰብበት።
መጀመሪያ በተደጋጋሚ በሪፖርተር ጋዜጣ እንዳሰፈርኩት አገራችን ለይስሙላ ሳይሆን፣ ከ500 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ፍላጎት የሚበቃ ምርት ማምረት የምትችል ናት፡፡ በርካታ የሰብል ዓይነቶች፣ የእንስሳት ሀብት፣ በየትም ዓለም የማይገኙ የአዕዋፋት ዝርያ፣ የዱር አራዊት፣ የደን ብዛት፣ ለጎብኚዎች የሚያጓጉ ተራሮችና ሸንተረሮች፣ በርካታ ወራጅ ወንዞች፣ በመቶ ዓመታት የሚቆጠሩ ዕድሜ ያላቸው ገዳማትን የያዘች አገራችን ምን ጎድሏት ነው ሁሌ ታዳጊ ተብላ የልመና ኮረጆ ይዛ የምትዞረው? ይህንን ለመመለስ ነው ሩጫችን መሆን ያለበት፡፡ መሪዎቻችንም ለግል ዝና ሳይሆን ከሕዝባቸው ጋር ተግባብተውና ቆራጥነትንና ትህትናን ተላብሰው ጠንክረው መሥራት እንጂ፣ በእንካሰላንቲያ ጊዜ ባይባክን መልካም ይሆናል።
አንድ ዛፍ ሊበቅልባቸው የማይችሉ አገሮች አፈር ከውጭ አስመጥተው በረሃውን ለም አድርገውት እያየን፣ ለሟ አገራችን ሁሌም ተመፅዋች መሆኗን መገንዘብ ያቃተን የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች፣ አንድ ቀን እንኳ ወንዞቻችንን ገድበን ሕዝባችንን አብልተን፣ ሕፃናትን የደሃ የጌታ ሳይባሉ ሁሉንም ወደ ትምህርት እንሰዳለን ሳይሉ፣ ሁሌም የሚያወሩን ስለዴሞክራሲ መሆኑ እየገረመኝ ነው።
የሰው ልጅን ከጎዳና ልመና ሳናነሳ፣ ለአገሩ በየጦር ሜዳው ደሙን በማፍሰስ ግዳጁን ፈጽሞ ወደ ቤቱ ተመልሶ ከማናችን ባይበልጥ እንኳን፣ ባይሆን እኩል የመሆን ዕድል ሳይሰጠው፣ ሠሩም አልሠሩ ዕድሜያቸው ለጡረታ ሲደርስ አዛውንቶች በዜግነታቸው ብቻ የመጦር ተስፋ የሚሰጥ አመራር ሳይኖር በግዑዝ ታይቶ የማይታወቀውን የዴሞክራሲ መዝሙር ብቻ መዘመር ያሰለቸና ሕዝቡን ተስፋ ያስቆረጠ ነው።
ለደሃ ወገኔ ከዚህች ለም አገሬ ምን ላፍልቅ? ምን አዲስና ፍሬያማ፣ የተሻለና የተመረጠ ዓለምን ጉድ የምናሰኝበትን ሰብል አብቅዬ ኢትዮጵያን የበለጠ አስተዋውቄ፣ አሁን እግር በማውጣት ላይ ያለውን ጤፍ ሌሎች እንደ ቡናው ሳይቀድሙንና ሳንቀደም በተሻለ መንገድ ለማምረት አልተሞከረም፡፡ ፖለቲከኖች ወገኔን ከችግር ላውጣ ቢሉና የጮሌነት የአፍ ጉቦ ሳይሆን፣ ሊያሳምን በሚችል ሁኔታ ቢወዳደሩ መምረጥና መመረጥ የተባለው ቋንቋችን ሥራ ላይ በዋለ ነበር። አልፈው ተርፈው በቋንቋ፣ በድንበር፣ በዘርና በሃይማኖት ሲተናነቁ፣ ሊያለያዩንና ሊገነጣጥሉን ጠዋት ማታ ሲወራረፉ ያታያሉ። ያረጀ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት እስያና አፍሪካ የተበዘበዙበት የአውሮፓዊያኑ ዘዴ ተመልሶ እንዳይመጣብን በትኩረት እንገንዘብ። ጊዜያዊ የግል ገናናነት ቀርቶ ለጋራ ይታሰብበት።
ሕዝብ… ሕዝብ… የምትሉት የትኛው ሕዝብ ነው በይፋ ወጥቶ የወከላችሁና ነው ግራ የምታጋቡት? ይህ ነው አገር የሚመራበት ዘይቤ? ወገኖቼ እስቲ መለስ በሉና ለአገራችሁ ከፖለቲካና ከአፍ ጉቦ በፊት የአመራር ልምዳችሁን ለሕዝቡ ግለጹለትና ራሱ ይፍረድ። ለግል መታወቂያና ለአለሁ አለሁ ሳይሆን በእርግጠኝነት ለወገናችሁ መቆማችሁን አሳዩን። ከዚያ በኋላ ሌላው እውነተኛው መሪ ከመሀላችሁ ብቅ ሲል ሳትቃወሙ ደግፋችሁት አገርን ለመምራት ስትነሳሱ ነው፣ በእርግጥ ለአገር የተነሳችሁ መሆኑን ወገናችሁ የሚረዳው። አለበለዚያ የባዶ በርሜል ጩኸት እንዳይሆን ተጠንቀቁ፡፡
የዓለም ታላላቅ መሪዎች ከየት ተነስተው የት እን ደደረሱ የሥራ ልምዳቸውን ተመልከቱ። ለምሳሌ የአሜሪካ ሰባተኛ ፕሬዚዳንት አንድሩ ጃክሰንን እንውሰድ፡፡ የመጨረሻ የደሃ ልጅ ነበር፡፡ በአንድ የደሃ ጋሪ ውስጥ ከመወለዱ በፊት አባቱ የሞተበት፣ በ14 ዓመቱ እናቱን በሞት ያጣ፣ ማንበብና መጻፍ የማይችል ወጣት፣ ግን ቆራጥና ወገኑን አክባሪና የውሳኔ መንፈስ የነበረው፣ የፈረስ ግልቢያ በማየት በጉጉትና፣ በቆራጥነት የተማረ ስለነበር በዚህ ችሎታው ለእንግሊዝ የወታደር አለቆች በተላላኪነት ተቀጠረ። ግን ግፈኞቹ እንግሊዞች እንደ ፈለጋቸው ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡ ጫማቸውን ጥረግ ቢሉት የተቀጠርኩበትን እንጂ ጫማ አልጠርግም በማለቱ ጭንቅላቱን በዱላ ለሁለት ከፍለው አንዲሞት ፈልገው ነበር፣ ግን አልሞተም።
ለእንግሊዞች የነበረው ጥላቻ ቃላት የማይገኙለት ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ጎበዙ ጃክሰን የሕግ ትምህርት ተማረ፡፡ በጣም ጀብደኛ ነበርና አንዱ ሚስቱን ቢሰድብበት ያንን ባለጌ ዋጋውን ከፈለው፡፡ ከዚያም በትክክለኛ ፍርድ ወጣ፡፡ በዚህ ጀግንነቱ ምንም የጦር ትምህርት ሳይኖረው በሕዝብ ምርጫ ጄኔራል ሆኖ ከአሜሪካን ህንዶች ጋር ተዋጋ፣ አሸነፈም፡፡
እ.ኤ.አ. በ1812 በእንግሊዝና በአሜሪካ መሀል በተደረገው ጦርነት መሪ በመሆን አሸነፈ። ከዚያ በኋላ ሦስት ጊዜ የኮንግረስ አባል ሆኖ አገለገለ፡፡ ሳይታሰብ እ.ኤ.አ. በ1824 የቴነሲ ሕዝብ ለፕሬዚዳንትነት እሱ ሳያስበው በዕጩነት አቀረበው። እኔ ለፕሬዚዳንትነት አልበቃም ብሎ አሻፈረኝ አለ፡፡ ልብ በሉ የዛሬዎቹ ሰዎች እንኳን ተመርጠው ራሳቸውን ለማስቀደም ይሻማሉ፡፡ እሱ ግን የሕዝብ ፍላጎት ነውና ሳይፈልግ ምርጫው ውስጥ ገባ፡፡ ዘመኑ የበታችና የበላይነት የሰፈነበት በመሆኑ ኩውይንሲ አዳም አሸነፈው።
እ.ኤ.አ. ከ1828 ምርጫ ቀደም ሲል የነበረው የአመራረጥ ሥርዓት ተለወጠና በብዙኃኑ ተመርጦ አባቱ ከመወለዱ በፊት የሞተበት አንድ የደሃ ልጅ፣ ያለ አባት ያደገ፣ ከ14 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ እናቱ ሞታ በራሱ ተፍጨርጭሮ ያደገ ልጅ፣ ለአገሩና ለወገኑ በሰጠው አገልግሎት በጊዜው በዴሞክራቲክ ፓርቲ ተመርጦ ስምንት ዓመታት በጥሩ ሁኔታ አገሩን መርቶ ጨርሶ ለሌላው ቀጣይ አስረክቦ ወረደ። ይህ እንግዲህ ከዛሬ 181 ዓመታት በፊት የተከናወነ ታሪክ ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካኖች አገር ከነባሮቹ የአሜሪካን ፕሬዚዳንቶች በተሻለ ተምረውና ተመክሮ አግኝተው፣ እንኳን የእነሱን ያህል አንድ ባላገር የጭቃ ሹም የሚሠራውን መሥራትና ማሰብ የማይችሉ ናቸው፡፡ አገርን ከማልማት፣ ከማስተባበር፣ ለልማት ከማዘጋጀትና ወገናቸውን ከልመና ከማዳን ይልቅ ለማያውቁት ሥልጣን የሚሯሯጡ፣ የአገር ፍቅር ምን እንደሆነ ያልገባቸው፣ ነባሩን ቀደምት ታሪካቸውን ከቶውንም የማይገነዘቡና ለጠላት መንገድ የሚከፍቱ ናቸው፡፡ ወደ ልቦናቸው ተመልሰው በአንድነት ስሜት አገርን ሊመሩልን ይችላሉ፣ የኢትዮጵያን ምንነት ያውቃሉ፣ ሁሉን በእኩል ዓይን ያያሉ የሚሉትን አስቀድመው አገሪቱን ከጠላት ምኞትና ላንቃ ቢያወጧት ለዘለዓለም ሐውልት ይተከልላቸዋል።
እንደ መንግሥቱ አገር አጥፍተው ለመጥፋት ከሆነ የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርድባቸዋል። ተጠንቀቁ በማታውቁት ጉዳይ አትዘባርቁ፡፡ ማንም ይሁን ማን ያሻውን ቢል ምከሩት፣ ወደ መልካም መንገድ አምጡት እንጂ ለውድቀቱ መንገድ ለመክፈት አትሯሯጡ፡፡ የነገን በሚገባ አስተውሉ፣ ሥራ በወሬ አይሆንምና አስቡበት።
ለመጠቀም ስንፈልግ የሦስት ሺሕ ዘመናት ሥልጣኔ አለን ይባላል፡፡ በማያመቸን ጊዜ ደግሞ ታዳጊ አገር ነን እንላለን። ታዳጊነቱ ቀርቶ እየለማን ነው፡፡ ነገር ግን የተስተካከለ አመራር የለም፣ ያንን እናሻሽል፣ አብረን ለልማት እንነሳ፣ ሕዝባችንን ከችግርና ከመከራ እናድን፡፡ ገለታ፣ ገብረ እግዚአብሔር፣ ኦጁሉ፣ ዘለቀ፣ ታንጋ ወይም ረጠቦ ከእኔ ወይም እኔ ከማውቃቸው የተሻሉ ስለሆኑ እነሱን መርጠን እየመከርንም ቢሆን አገራችንን ብናለማ የተሻለ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሲገባ፣ ‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል› ዓይነት ሩጫ ለገራችን የማይበጅና አቆብቁበው ለሚጠብቁን ጠላቶቻችን መንገድ መክፈቱን ያለ ጥርጥር እያየን ነው።
ናፔር አገራችንን ከረገጠበት ዘመን ጀምሮ የተወረወረው ዓይናቸው ከመቶ ዓመታት በኋላ ይዞላቸው ታች ላይ ሲሉ፣ አሁንም በኢትዮጵያዊያን አምላክ የተረዳችው ኢትዮጵያ ነፃነቷን ይዛ ቆይታለችና እባካችሁ ታሪክ እንዳይፈርድባችሁ ተጠንቀቁ፡፡ ከላይ አንድሩ ጃክሰንን ያነሳሁበት ምክንያት ከየት ተነስቶ የት እንደ ደረሰ ብቻ ሳይሆን፣ አገልግሎቱን፣ ልምዱንና ችሎታውን ለመግለጽ ነው፡፡ እነዚህ ላስተማራቸው ሕዝብ ምንም ሳያበረክቱ እሽቅድምድም የያዙትን ወገኖቼን ወደ ልቦናችሁ ተመልሳችሁ፣ አገራችሁን አገር እንድትሆን አድርጓት ለማለት ነው።
በመቀጠል አገር ለመከፋፍል ለሚያደርጉት ሩጫ የሦስት ታላላቅ አገሮችንን ምሳሌ ለማስቀመጥ ወደድሁኝ። የዛሬዋ ታላቋ ብሪታኒያ ከ910 ዓ.ም. በኋላ ከታላቋ ሮማ አገዛዝ ወጣች፡፡ ከብዙ ከዘመናት በኋላ ኢንግላንድ፣ ዌልስና ደቡባዊ ስኮትላንድ በኅብረት ተነስተው የዛሬዋን ታላቋን ብሪታኒያ አቋቋሙ፡፡ በኋላ የታላቋን የአየር ላንድ ንጉሣዊ ግዛት፣ በመጨረሻም መላውን ስኮትላንድ በማቀላቀል ታላቅ አገር ለመሆን በቃች።
ከዚያም በ17ኛው ክፍለ ዘመን በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ አገሮች ቀድመው ቴክኖሎጂ አፍርተው አሁን ላሉበት ዘመን ደረሱ፡፡ ባይልላቸው እንጂ የዛሬዋ ታላቋ አሜሪካም የእነሱ ውጤት መሆኗ ይታወቃል፣ ግን ሳይሆን ቀረ። ተመልከቱ ያንን ሁሉ ነገር ከኋላችን ተነስተው ሲፈጥሩ ሌላውን ይጎዳሉ፣ እነሱ የያዙትን ይዘው የሌላውን ይቀማሉ፡፡ እርስ በርሳቸው አይጋደሉም፣ ከተጋደሉም አንድ ሆነን ሌላውን እንዝረፍ ለማለት አንጂ እንጥፋፋ ለማለትም አይደለም።
ለምሳሌ የዛሬው ታላቋ አሜሪካ ከእንግሊዝ ለመለየትና ራሷን ለመቻል በሰው አገር በፈጠሩት ጦርነት እንግሊዝ ተሸንፋ ልኳን አውቃ ወደ አገሯ ከገባች በኋላ፣ የተለመደ ተንኮሏን ለበኩር ልጇ አሜሪካ እያስተማረች በተንኮል ቀጠለች አንጂ ጨርሳ አልተለየችም። ዞረው ዞረው የአንድ እናትና አባት ልጅ ይመስል መክረውና ዘክረው የሚበጃቸውን አደረጉ እንጂ አልተፋጁም። እ.ኤ.አ. ከ1757 እስከ 1974 ድረስ ህንድን በጦርነት አሸንፈው ገዙ፡፡ ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምረው ወደ አፍሪካ ፊታቸውን አዞሩ።
ልብ በሉ ከዚህ ውሳኔያቸውና ትብብራቸው ውስጥ ያልታደለችው ጀርመን ጉልበት አገኘሁ ብላ ከመስመር በመውጣቷ፣ እንዲሁም ጣሊያን ያንን በመከተሏ ጀርመን በመጨረሻ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥታ ከሁሉም በታች ሆነች። ሆኖም ነጭ ነችና አንሰራርታለች። ታሪኩን ማወቅ የሚሻ አንብቦ ሊረዳ ይችላል። ከዚህ ሌላ አንድም እርስ በርሳቸው በመጣላት ሳይሆን፣ እኔ ይህንን ልውሰድ አንቺ ያኛውን ውሰጅ በመባባል ነበር ዓለምን የዘረፉት፡፡ እንዲያው በአጭሩ ተመልከቱ፡፡ አንድም የእስያ ወይም የአፍሪካ ታላቅም ሆነ ታናሽ እዚህ ክፍፍል ውስጥ አልገባም። ቢጣሉም ቢፋጁም አፍሪካንና እስያን ለመግዛት፣ ለባርነት ተስማምተውና ተዘጋጅተው የዘረፉት የሚከተሉ ነበሩ።
ብሪቲሽ፣ ፈረንሣይ፣ ደች፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመን፣ ስፔን፣ ጣሊያንና ቤልጂየም ነበሩ። ይህንን ያነሳሁበት ምክንያት የቀለም ተመሳሳይነትን ተመልከቱ ለማለት ነው፡፡ ሌላውን ሊገዙትና ሊያሰቃዩት የፈለጉት ከእነሱ እንዳነሰ ፍጡር አድርገው ስለቆጠሩት ነው፡፡ እነሱ ግን ተሰባስበው፣ ተስማምተውና አኅጉር እያቋረጡ ባለፈው ጠብና ጭቅጭቅ ቢኖርባቸው እንኳ ያንን ወደኋላ ጥለው ለጋራ ጥቅም ተሠለፉ፡፡ በማይመለከታቸው አገሮች ውስጥ ገብተው ከፍተኛ ሥቃይና መከራ ሲያደርሱ ኖሩ።
እንግዲህ የሚገርመው ነገር እኛ በአንድነት ተከባብረንና ተዋድደን የኖርን ሕዝብ ሆነን ሳለ፣ የእነሱን ዕውቀት ሳይሆን ተንኮል ይዘን አገር ለማጥፋት እየተሯሯጥን ነው። ጀርመኖች በአንዱ ክፍለ አገራችን ውስጥ ከ60 እና 70 ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በስመ ክርስትና (በሃይማኖት) ሽፋን ገብተው ያስተምሩ ነበር። በዘመኑ አንዲት ወጣት ዛሬ ትልቅ ሴት ናቸው አራተኛ ክፍል ገብተው ሲማሩ የክፍል አስተማሪያቸው፣ ‹እናንተ እኮ ጀርመኖች ናችሁ፣ ሰውነታችሁ በፀሐይ ጠቁሮ ነው እንጂ አጥንታችሁ ከእኔ ጋር አንድ ነው› ይላቸዋል፡፡
በዘመኑ ወጣቷ ሴት ‹እኔ ኢትዮጵያዊት እንጂ ጀርመን አይደለሁም› ይላሉ። ‹ጀርመን መሆንሽን ካላመንሽ ትምህርት ቤቱን ልቀቂ ወይም ወደ ሦስተኛ ክፍል በቅጣት ወደኋላ ትመለሽያለሽ› ተብለው እንደተመለሱ እንግሊዝ አገር በስደት በነበሩበት ጊዜ አጫውተውኝ ነበር። በመሰላቸውና በሚችሉት ሊያለያዩን ለብዙ ዘመን ያዘጋጁት ወጥመድ ዛሬ ስለተሳካላቸው፣ ገብተን እያዳከርን ስለሆነ ወገኖቼ ብዙ አንታለል፡፡ ለሹመት እንደሆነ እንደ ችሎታችን እንሾም፡፡ ንብረት ለማግኘት ከሆነ ለምለሟን አገራችንን ብናለማ ከማንም እንበልጣለንና ወደ ልቦናችን እንመለስ። ነባር ታሪካችንን በማይሆን መንገድ አናጥፋው።
ከላይ እንደ ጀመርኩት ወደ አሜሪካን ታሪክ ልመልሳችሁና አንዳንድ ነገር ላስገነዝባችሁ እሻለሁ። ሰሜኑና ደቡቡ ባሪያ ነፃ ይውጣ አይወጣም በሚል ጭቅጭቅ ሳይግባቡ ቀርቶ ጦርነት ገጠሙ፡፡ ከሁለቱም በኩል ከ620,000 እስከ 750,000 ወገናቸው በጦርነት አለቀ፡፡ በመጨረሻም ሰሜኑ አሸነፈ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አገራቸውን ይኼው እስከ ዛሬ በታላቅ ደረጃ፣ አንድ አገር አንድ ሕዝብ ብለው የዓለም ቁንጮ ሆነው እየመሩ ነው።
እኛ ግን በትንሹም በትልቁም ውኃ ቀጠነ ብለን ምንም አስተዋፅኦ ሳናበረክት ሕዝባችንን ከረሃብ፣ ከእርዛትና ከመጠለያ ዕጦት አላቀን ወገናችንን ቦታ ሳናስይዝ ሰው አገር ሄደን ቀላውጠን ባገኘነው ዕውቀት ከመጠቀም ይልቅ፣ ለተንኮልና ለጥፋት እየተወራጨን ነው። ጎበዝ አድፍጠው ይጣባበቁን ለነበሩት ወዳጅ መሳይ ጠላቶች ለባርነት አንዘጋጅ። አገርን ተመሳጥረን ብንሸጥ እንኳ ዞሮ ዞሮ በከሃዲነት ይቆጥሩን እንደሆን እንጂ፣ እንደ ጀግና አያዩንምና የአስተውሎት ሚዛናችንን ሰፋ እናድርገው፡፡ ታላቋን አገራችንን ለክብርና ለልማት እናብቃት እንጂ፣ ለመሸጥ አናቀንቅን።
በክብር ኖረን በክብር እንለፍ፡፡ የአገራችንን ክብርና ወሰን ያስጠበቁልንን ያለፉትን መሪዎች ታሪክ ለማጥፋት አንሽቀዳደም። አትፍረዱ ይፈረድባችኋልና፡፡ የመንግሥት ወኪሎችም ወገንን አትናቁ፣ ችግር ሲመጣ ብቻ አይደለም ወገን በአሰሳ የሚፈለገው። አገሩ የጋራ ነውና ለማንኛውም ሕዝቡን ለማሳተፍ ሞክሩ፣ ሐሳቡን ለማወቅ ጣሩ። ከእኛ በላይ ላሳር ማለት ጨርሶ አይበጅምና ባላችሁባት ጊዜ የምትችሉትን ከልብ ለአገርና ለወገን ሥሩ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባብያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡