Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ለመንግሥት ከምንም ነገር በላይ ትልቁ ትኩረት የህዳሴ ግድብ ነው›› ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር

የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትንና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ በሥሩ ሦስት ተቋማትን የሚያስተዳድረውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን እንዲመሩ ከተሾሙ አንድ ዓመት የሆናቸው ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በመስኖና ውኃ ምሕንድስና ከመጀመርያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ተምረዋል፡፡ የምሕንድስና ሙያን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጀምረው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችም በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በበርካታ ቢሮዎች ያገለገሉት ሀብታሙ (ዶ/ር) በሚኒስትርነት እስኪሾሙ ድረስ የኦሮሚያ ውኃና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮን ለሁለት ዓመት መርተው ነበር፡፡ ያለፈው አንድ ዓመት በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተገኘውን ስኬት ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ የኃይል ዘርፉ ትልቅ ዓመት ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በበርካታ የውኃና የኃይል ጉዳዮች ላይ ሳሙኤል ቦጋለ ከሚኒስትሩ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፈው አንድ ዓመት በታላቁ ህዳሴ ግድብ የተመዘገበውን ድል ጨምሮ በኢትዮጵያ የኃይል ዘርፍ ትልቅ ዓመት ነበር ይባላል፡፡ እርስዎም ይህንን ተቋም መምራት ከጀመሩ አንድ ዓመት የሞላዎ ሲሆን፣ ዓመቱ እንዴት ነበር? የተመዘገቡት ስኬቶች እንዴት ይገለጻሉ?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን መምራት መቻል እንደ ግብርና፣ መስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ተቋማት ለአገሪቱ ዕድገት ቁልፉን ድርሻ መጫወት ነው፡፡ የእነዚህ ተቋማት ወሳኝነት ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የረሃብና የድህነት ታሪክ ለመቀየርና ከስማችን ጋር ተጣብቆ የሚመጣውን መጥፎ መታወቂያ የምንቀይርበት ነው፡፡ በእጃችን ያለውን እንደ ውኃ ዓይነት ሀብት ወደ ግብርናም ሆነ ወደ ኃይል በእኛ፣ በመስኖና ቆላ ሚኒስቴር አማካይነት እየቀየርን በጋራ ግብርናችንንም የኃይል አቅርቦታችንንም ማሳደግ እንችላለን፡፡ የኃይል አቅርቦት ግብርናን ወደ ማኑክቸሪንግ ይቀይራል፣ ማኑፋክቸሪንግ ደግሞ የውጭ ንግዳችንን ያሳድግልናል፡፡ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ዕድገት የሚረጋገጥበት ተቋም በመሆኑ እሱን መምራት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላለፉት አሥር ዓመታት ዋጋ ሲከፍሉበት የቆዩበት ፕሮጀክት ነው፡፡ እንደ ግለሰብም ሆነ ተቋሙን እንደሚመራ ሰው ባለፈው አንድ ዓመት በግድቡ ላይ የተመዘገበው ለውጥ እጅግ የሚያኮራ ነው፡፡ የውኃውን ሙሌት ማከናወን እንደማንችል በጠላቶቻችን ሲፎከርብን ቢቆይም፣ እኛ ግን መሙላት እንደምንችል ያሳየንበት ነው፡፡ የህዳሴ ግድብ ሦስተኛው ዙር ሙሌት ከአሁን በኋላ የውኃ መሙላት አለመሙላት ጉዳይ እንዳልሆነ በደንብ አድርጎ ፋይሉ የተዘጋበት ነው፡፡ በዚህም በጣም ኩራት ይሰማኛል፡፡ የእኛም ሚኒስቴር በዚህ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይሰማኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ በቁጥር አስደግፈው ሊነግሩን ይችላሉ? ሁለት ተርባይኖች ኃይል እያመነጩ ስለሆነ ምን ያህል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት እየገባ ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የአንዱ ተርባይን የማመንጨት አቅም 375 ሜጋ ዋት ሲሆን፣ አሁን ሥራ የጀመሩት ሁለቱ ተርባይኖች በአንድ ላይ 750 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም አላቸው፡፡ ነገር ግን ከተርባይኖቹ በላይ ያለው የውኃ መጠን ወሳኝነት አለው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከባህር ጠለል በላይ ያለው የግድቡ 100 ሜትር ከፍታ የያዘው የውኃ መጠን ተርባይኖቹ የሚያመርቱትን የኃይል መጠን እንዲቀያየር ያደርገዋል፡፡ ሁለቱ ተርባይኖች በአሁን እያመረቱ ያለው የኃይል መጠን 540፣ 560 እና 570 ሜጋ ዋት መካከል የሚቀያየር ሲሆን፣ በትንሹ በየቀኑ ከ540 ሜጋ ዋት በላይ እያመረቱ ይገኛሉ፡፡ ግድቡ ተጠናቆ የሚጠበቅበትን ከባህር ጠለል በላይ 140 ሜትር ከፍታ ሲደርስና በቂ የውኃ መጠን ሲይዝ፣ በሚያገኘው ጉልበት እያንዳንዳቸው ተርባይኖች በሙሉ አቅማቸው 370 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ ግድቡ የያዘው የውኃ መጠን ስንት ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አሁን የያዝነው የውኃ መጠን 22 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ነው፡፡ በ100 ሜትር የግድብ ከፍታ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው ጊዜ ከግድቡ ቁመት በላይ 2.3 እና 2.4 ሜትር ጥልቀት ያለው ውኃ ይፈስ ነበር፡፡ ይህም ርቀቱ ከግድቡ በላይ አልፎ ከ102 ሜትር በላይ የነበረ ሲሆን፣ በዚያን ጊዜም ከ22 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በላይ ነበር ግድቡ ውስጥ የነበረው የውኃ መጠን፡፡

ሪፖርተር፡- ግድቡን ለማጠናቀቅ  የቀረው ጊዜና የሚያስፈልገውን ሀብት አስመልክቶ ኢትዮጵያ ያለችበት የኢኮኖሚና የውጭ ምንዛሪ ችግር ሥጋት አይሆንም? ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል የተባለ በመሆኑ አብዛኞቹ የማጠናቀቂያ ሥራዎች የውጭ ምንዛሪ አያስፈልጋቸውም?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው ጊዜ አሁን በትልቁ ሁለት ዓመት ተኩል ሲሆን፣ በጣም ከበረታን ግን እዚያም ላይደርስ ይችላል፡፡ የሲቪል ሥራዎች በሚያስገርም ሁኔታ ከ98 በመቶ በላይ ደርሰዋል፡፡ አሁን ትልቁና ወሳኙ ሥራው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን ማጠናቀቅ ነው፡፡ ለእነዚህ የሚውሉ መሣሪያዎች ደግሞ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከኮቪድ-19 በኋላ በተፈጠሩ ችግሮች በዓለም ላይ ያሉ ፋብሪካዎች ምርቶች ማዘግየታቸውን እንደ እንቅፋት ማየት እንችላለን፡፡ ነገር ግን ለመንግሥት ከምንም ነገር በላይ ትልቁ ትኩረት የህዳሴ ግድብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም የፕሮጀክት ቢሮው ድረስ በመሄድ በየጊዜው ትኩረት የሚሰጡበት ስለሆነ፣ ይህንን ትኩረት በመጠቀም ከጊዜው እንዳያልፍ በጥንቃቄ እንሠራለን፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የውጭ ምንዛሪ ችግር ውስጥ ሆና የህዳሴ ግድብ በምንም ሁኔታ አልተስተጓጎለም ነበር፡፡ እንዲያውም ከሲሚንቶ እጥረትና ከፀጥታ ጋር በተያያዘ ማጓጓዝ ላይ ከገጠመን የሲቪል ሥራዎች መጓተት በስተቀር፣ ምንም የገጠመ ተግዳሮት አልነበረም፡፡ ያለንን ሀብት በአግባቡ ከተጠቀምን አሁንም የውጭ ምንዛሪ ያሠጋናል ብዬ አላስብም፡፡ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ላይ  በያዘችው ንቅናቄ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማዳን ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኢኮኖሚ ባሻገር በዲፕሎማሲ በኩል ያሉ ተግዳሮቶችን ኢትዮጵያ እንዴት እየተወጣች ነው? የሦስቱ አገር ድርድር ጉዳይ ወሬ የማይሰማው ከምን ደርሶ ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የቀጣናው የፖለቲካ አካሄድ ከሁኔታዎች ጋር ነው የሚሄደው፡፡ እንደሚታወቀው የህዳሴ ግድብ አሞላል ላይ ነበር ንግግሩ፡፡ ከዚያም አስገዳጅ ስምምነት ብለው አመጡ፡፡ ነገር ግን ሦስተኛውን ሙሌት ካከናወን በኋላ ይህ ነገር አጀንዳ መሆን እንደማይችል እርግጠኛ ሆነዋል፡፡ አሁን እኛን በውኃ ሙሌት ማስገደድ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስላልሆኑ ድርድሩ በቆመበት ነው ያለው፡፡ እኛ መቼም ዝግጁ ነን፡፡ ነገር ግን የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ ጉዳይ መሆን ስለማይችል፣ ምናልባት ይዘቱን ሊቀይር ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ያም ሆነ ይህ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ድርድሩ መቀጠል እንዳለበት እኛም እየተጫንን ነው ያለነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃው መሙላትና አለመሙላት ጉዳይ ላይ ተስፋ ከቆረጡ ታዲያ በቀጣይ ምን ዓይነት አጀንዳ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- በእርግጠኝነት መስመሩም ወደዚያ ይመስላል፡፡ ድርቅን እንደ አጀንዳ ይዘው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ይህም በግብፅ ድርቅ ቢፈጠር ከግድቡ ውኃ ይለቀቃል የሚል ሲሆን፣ ይህ ደግሞ እጅግ አስነዋሪ ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሳይኖራቸው በአንጡራ ሀብታቸው የገነቡትን ግድብና የያዝነውን ውኃ እኛ እንድንሰጣቸው ማስገደድ የሚመስሉ ነገሮችን ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በግብፅ የሚገኘው አስዋን ግድብ ውስጥ ያለውን የውኃ መጠን ለማስጠበቅ፣ ኢትዮጵያ ይህን ያህል ውኃ መልቀቅ አለባት የሚል አንድምታ ያለው ክርክር ሊያነሱ እንደሚችሉ ምልክቶች አሉ፡፡ አሁን የሙሌቱ ጉዳይ አልቋል፡፡ በቀጣይ ስለሚላቀቀው ውኃ ነው ሊያደርጉት የሚችሉት፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ አጀንዳ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተቀባይነት አይኖረውም? ከጥቂት ሳምንት በኋላ በግብፅ የሚካሄደው የኮፕ27 (Cop27) አየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስስ ትልቅ ማግባቢያ አይሆናቸውም?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ግብፆች የሚናገሩት እንኳን በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአጎራባች አገሮች ሱዳንን ጨምሮ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ የኮፕ27 (Cop27)  ኮንፈረንስን እንደ ማግባቢያ ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ እኛም እየተዘጋጀን ነው፡፡ ነገር ግን እነሱ እንደ አዘጋጅ አገር ከእኛ በላይ እየተዘጋጁ ነው ያሉት፡፡ ከአየር ንብረትና ከባቢ አየር ወጥተው በበለጠ ወደ ግብርና በመውሰድ ነው ጉዳዩን እየተዘጋጁ ያሉት፡፡ ‹ምክንያቱም እኛ ዝናብ የለንም ለግብርና፣ ሌሎች ተፋሰስ አገሮች ውኃውን እየወሰዱብን ነው ያሉት› በማለት ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ በእኛ በኩልም ከውጭ ጉዳይ፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴሮች ጋር በመሆን የጋራ ግብረ ኃይል በማቋቋም እየተዘጋጀን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንደ አዲስ ሲቋቋም ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ አንደኛው፣ በመንግሥትና በግል አጋርነት የኃይልና የውኃ ልማት ሥራን ማካሄድ ነበር፡፡ በዚህ በኩል ምን እየተሠራ ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የመንግሥትና የግል አጋርነት ሥራዎች በተለይ በውኃ ልማት ላይ ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ነገር የለም፡፡ በኃይል በኩል ግን በጅምር ደረጃ እንደ ፀሐይን ጨምሮ የመሳሰሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ብዙ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የማልማት አዝማሚያ እያሳዩ ናቸው፡፡ ከቱርክ፣ ከጀርመን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በርካታ ባለሀብቶች በኃይል ልማት ፍላጎታቸውን እያሳዩ ነው፡፡ አንዳንዶቹም ሥራ ጀምረዋል፡፡ በውኃ በኩል ግን ተጨማሪ ሥራ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ረዥም ዓመታት ያስቆጠረው የውኃ ፖሊሲ ይህን የመንግሥትና የግል አጋርነት እንዲፈቅድ በሚያደርግ መንገድ መከለስ አስፈላጊ ነው፡፡ ፖሊሲውን በአጭር ጊዜ በሁለትና ሦስት ወራት ውስጥ ለካቢኔ አቅርበን፣ ከዚያም አልፎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማፀደቅ ነው ዕቅዳችን፡፡

ሪፖርተር፡- በታሪፍ ምክንያትም ይሁን በሌላ ባለሀብቶች በአጋርነት ለመሳተፍ በበቂ ሁኔታ አለመምጣት አለ?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- በውኃ ላይ ያለውን ፍላጎት እስካሁን ገና ስለሆነ መናገር ይከብዳል፡፡ በኃይል ላይ ግን ከፍተኛ ፍላጎት አለ፡፡ የኢትዮጵያ ኃይል አረንጓዴና ታዳሽ እንደ መሆኑና ምንም ዓይነት የካርቦን ልቀት ሳይኖር የሚለማ ነው፡፡ በዚህ ላይ ባለሀብቶች መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ ወደፊትም በዓለም ላይ ያለው ተቀባይነት ይጨምራል፡፡ በዓለም ላይ አሁን ትልቁ ጥያቄ እየሆነ ያለው የካርቦን ልቀትን መቆጣጠር ነው፡፡ ስለዚህ ከመጠጥ ውኃው በበለጠ እዚህ ላይ ነው ከተለያዩ አገሮች ጥያቄዎች እያዘነበሉ ያሉት፡፡

ሪፖርተር፡- የኤሌክትሪክ ኃይል ቢመረትም በሥርጭት በኩል ከፍተኛ ችግር እንዳለ ይታወቃል፡፡ በዚህ በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በእናንተ መሥሪያ ቤት እንዴት ይታገዛል?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- እኛ በፖሊሲ በኩል ነው ተቋሙን የምንመራው፡፡ በማክሮ ኮሚቴ ደረጃም በኤሌክትሪክ ሥርጭት ላይ እንዴት ይታገዝ? በሚል ሰፊ ዕቅድም አለ፡፡ እኛም በግል አጋርነትም ሆነ በሌላ በፖሊሲ የምንደግፋቸው ሲሆን፣ በኢነርጂ ፖሊሲ ውስጥ እንዳካተትናቸው ወደ ውድድርና የሥራ ቅልጥፍና እንዲገቡ እናግዛቸዋለን፡፡ ከግል ዘርፉ ጋር ወይ በሽርክና ይሠራሉ፣ አልያም አብረው ሠርተው ወደ ውጭ ገበያ እያቀረቡ ያተርፋሉ፡፡ እውነትም ዕዳ አለባቸው፣ ነገር ግን አሁን ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ አሁን እንዲያውም እንደ መንግሥት ተቋም ብቻ ሳይሆን አትራፊ ድርጅት ወደ መሆንም መጥተዋል፡፡ በውስጥ ጥንካሬያቸውና በትጋት በመሥራትም አሁን ካላቸው ችግር ይወጣሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ትርፍ ኃይል (Surplus Power) አላት ይባላል፡፡ ለዚህ የማይሠራጭ ትርፍ ኃይል ምን ታቅዷል?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ኢትዮጵያ ትርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ያላትና የውኃ ማማ ናት የሚባሉት ትርክቶች ትክክል አይደሉም፡፡ ትርፍ ኃይልም የላትም፣ የውኃ ማማም አይደለችም፡፡ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ከ50 እና ከ60 ሚሊዮን የማይበልጥ በብሉ ናይል ተፋሰስ መስመር ተይዞ፣ የቀረው ደግሞ በምሥራቁና በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ድርቅ ባለበትና ዝናብ በማያገኝበት ሁኔታ እየኖረ የውኃ ማማ ናት የሚለው አይሠራም፡፡ ይህ ውኃ ካልተሠራጨ ከፍታ ላይ ናት ብቻ ብንል ዋጋ የለውም፡፡ በእርግጥ በኢትዮጵያ በኃይድሮ ፓወር (በውኃ ኃይል) ብቻ እስከ 45,000 ጊጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይቻላል፡፡ ይህ በእርግጥ ትልቅ ነው እንደ አቅም ቢታይ፡፡ ነገር ግን ትርፍ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ተመርቶ እየባከነ ያለ የኤሌክትሪክ ኃይል አለ አይደል እንዴ?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አዎ አለ፡፡ መስመሮቹም በጣም የቆዩና ያረጁ ከመሆናቸው ባሻገር አሠራሩ በቂ ባለመሆኑ በጣም አለ፡፡ ኢትዮጵያ የምታመነጨውን ያህል አታከፋፍልም፡፡ መስመሩ በብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትር ርቀት ነው የሚሄደው፡፡ የራሱ የሆነ የሕግ ማዕቀፍና ድጋፍ ኖሮት ይህንን መቀየርና ማደስ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ አገሮች ጋር ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ስምምነት አድርጋለች፡፡ በመስመር ላይ ያሉም አሉ፡፡ ይህ ቀጣናዊ የኃይል ትስስር እንዴት እየሄደ ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- የምሥራቅ አፍሪካ ኃይል ፑል (East Africa Power Pool) የሚል አንድ ትልቅ ፕሮጀክት አለ፡፡ በእርግጥ ሌሎችም አገሮች ኃይል ከአንዱ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ የራሳቸውን ድርሻ ቢወጡም፣ ኢትዮጵያ ግን ትልቁ ድርሻ አላት፡፡ በመጀመርያ የነበረው ዕቅድ ቢታይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ እስከ ግብፅ ካይሮ ድረስ የሚደርስ መስመር ነበር የታቀደው፡፡ የዓለም ባንክም የቀጣናዊ ትስስርን ስለሚያበረታታ ይህን ድጋፍ ያደርግ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ለጂቡቲና ለሱዳን ኃይል እየሰጠች ሲሆን፣ ለኬንያ ደግሞ የመስመር ዝርጋታን ጨምሮ ብዙ ሥራዎች ተጠናቀዋል፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋር የመግባቢያ ሰነዶች ተጠናቀዋል፡፡ በተጨማሪም ሱዳን ተጨማሪ ኃይል ትፈልጋለች፡፡ በቀጣናው ውስጥ ትልቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ በመሆኗ ይህ ትልቅ ጥቅም አለው፡፡

ሪፖርተር፡- የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮቹ አዘረጋግ ከኢትዮጵያ መሄድ ብቻ ሳይሆን ከሌሎችም አገሮች ኃይልን ለመቀበል የሚያስችል ነው ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ኃይል የመቀበል ዕድል አላት?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ትልቁ አቅም ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ጂቡቲ ብዙ የኃይል መጠኗ የሚሸፈነው በኢትዮጵያ ስለሆነ ከዚህ ነው እንጂ ወደ እዚያ የሚሄደው ከእነሱ ብዙም አንጠብቅም፡፡ ለሱዳንም፣ ለደቡብ ሱዳንም ከዚህ የሚሄድ ነው እንጂ ከዚያ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣ ነገር የለም፡፡ ኬንያ በጂኦተርማል ኃይል የማመንጨት ጅማሮዎችና አቅም አለ፡፡ ሲስተሙ በሁለቱም በኩል ስላለ ምናልባት ልውውጥ የማድረግ ዕድል ሊኖር ስለሚችል እሱን ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በህዳሴ ግድብ ከሁለቱ ተርባይኖች በተጨማሪ ሌሎች ተርባይኖች እንዴት ነው ቀጣይ ኃይል የሚያመነጩት?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- አሁን ያለቁትና ኃይል እያመነጩ ያሉት ሁለቱ ከታች ያሉት ተርባይኖች ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት 11 ተርባይኖች በእኩል ደረጃ ላይ ያሉ በመሆናቸው፣ የግድቡን ግንባታ በቂ ደረጃ ስናደርሰውና ውኃውን ሙሉ ለሙሉ ስንይዝ ተርባይኖቹ በሙሉ አንድ ላይ ኃይል ያመነጫሉ፡፡ ቀጣዩ ሥራ አሁን ከባህር ጠለል በላይ 100 ሜትር ቁመት ያለውን የግድብ ከፍታ ማስቀጠልና ከ140 ሜትር በላይ ማድረስ ነው፡፡ እሱም በአጭር ጊዜ ያልቃል፡፡ አሁን የቀረው ጊዜና ጉልበት የሚጠይቀው የኤሌክትሮ ሜካኒካልና መሰል ሥራ ነው፡፡ የብረት ሥራ ነው በአብዛኛው የሚቀረው፡፡ ሙሉ ትኩረት መሰጠት ያለበት እሱ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሥራ በሳሊኒ ኩባንያና በመሰል ድርጅቶች ነው የሚከናወነው፡፡ ድርጅቱ ከዚህ በፊት የካሳ ክፍያ በመዘግየቱ ጠይቆ እንደተከፈለው ይታወቃል፡፡ በዓለም ላይ በተፈጠሩት ችግሮች ምክንያት ተጨማሪ ክፍያዎችን እየጠየቀ ነው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ወደ እኛ የመጣ ግልጽ ጥያቄ የለም፡፡ በፕሮጀክት ቢሮው ወይም በኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን በኩል ጥያቄ ቀርቦ ከሆነም አናውቅም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ሊመሠገን የሚገባ ሲሆን፣ በጣም በጥሩ መንፈስ እየሠራ ነው የሚገኘው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ለዚህ ግድብ ዋጋ እንደሚሰጡ ድርጅቱ ዓይቶታል፡፡ ያለው ግንኙነት እጅግ በጣም ጥሩና የተመዘገበውም ውጤት ከእነሱ ቁርጠኝነት ጋር ተዳምሮ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ የግድቡን አስተማማኝነትና ዘላቂነት ለማስጠበቅ ምን ዓይነት ሥራዎች መከናወን አለባቸው?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- ቀጣይ መታሰብ ያለበት ነገር አሁን ህዳሴን በሚያህል ትልቅ ግድብ ተገንብቶ የተፋሰስ ልማት ካልተሠራ ምንም ዋጋ የለውም፡፡ እንደ አረንጓዴ አሻራና እርከን ዓይነት አጠቃላይ ሥራዎች ትልቅ ትኩረት የሚሹ ናቸው፡፡ ግድቡ ላይ ገንዘብ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ደለልም እንዳይገባ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ግድቡ የቱሪዝም መዳረሻና ትራንስፖርትን ጨምሮ በዘላቂነት በርካታ ሥራዎች የሚከናውኑበት ነው፡፡ በዘላቂነት ይህን ማልማት እጅግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ከአዲስ አበባ ብዙም ሳይርቁ ባሉ አካባቢዎች ዝናብ እየጠፋ ነው፡፡ ይህ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ውኃ መቆጠብ፣ ዝናብ ውኃ መያዝና ወንዞችን ጠልፎ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- የውኃ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ላይ እየተከናወኑ ያሉ እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ?

ሀብታሙ (ዶ/ር)፡- በእኛ ሚኒስቴር ሥር ካሉ ተጠሪ ተቋማት አንደኛው የኢትዮጵያ ውኃ ቴክኖሎጂ ተቋም ሲሆን፣ እሱም ከሚሰጣቸው የሥልጠና ሥራዎች ባሻገር ጥናት በማድረግ ውኃን በማቆር ለኅብረተሰቡ ለማዳረስ የተጀመሩ ንቅናቄዎች አሉ፡፡ ‹‹ግድቤን በደጄ›› የተባለው አንደኛው ንቅናቄ በወጣለት ሞዴል መሠረት የዝናብ ውኃ በየአካባቢው በመሰብሰብና በማውጣት ማጣራትና መጠቀም ይቻላል፡፡ በቦረና በስምንት ቦታዎች፣ በጎንደር ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ አራት ቦታዎች ላይ ጀምረናል፡፡ በትምህርት ቤቶች ይህንን በማድረግ ትምህርት ቤቶችን በውኃ ራስን ማስቻል ይቻላል፡፡ ሁሉም በየቦታው የሚዘንበውን ውኃ መያዝ ቢቻል ውኃ በውኃ መሆን ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የመሬትና የሰው ኃይል አቅም ይህን ማስቻል ይችላል፡፡ የጎንደሩ ቢያመልጠንም የቦረናው ከዚህ በኋላ ስለሆነ በሚዘንበው ዕድል አለ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...

‹‹ባለፉት 25 ዓመታት ባለን አቅም ሁሉ የተለያዩ አጀንዳዎችን ለመዳሰስ ሞክረናል›› የራስወርቅ አድማሴ (ዶ/ር)፣ የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ›› በመባል የሚታወቀውን በኢትዮጵያ ታሪክ ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል ገለልተኛ ሆኖ የተቋቋመ ሐሳብ አመንጪ የጥናት ተቋም (ቲንክ ታንክ) ከመሠረቱት አንዱ መሆናቸውን...

‹‹ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ሊያግዙ የሚችሉ ወጥ የሆኑ ሕጎች ያስፈልጉታል›› አቶ ኑሪ ሁሴን፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት (ከወለድ ነፃ ባንክ...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር ብርቱ ትግል ተካሂዷል፡፡ ከብዙ ጥረት በኋላ አገልግሎት በመስኮት ደረጃ እንዲሰጥ ተወስኖ፣ ከዚያም ከለውጡ ወዲህ ሙሉ በሙሉ ከወለድ...