Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባቡር አልባ ሐዲዶች ባለቤት እንዳንሆን!

የአገር ሀብት በብላሽ ከፈሰሰባቸው አሳዛኝ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መካከል የባቡር ትራንስፖር ዝርጋታ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አገርን በዕዳ ቀፍድደው በመያዝም እነዚህ የባቡር ፕሮጀክቶች በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

ያልተጠናቀቁትን ፕሮጀክቶች ትተን ወደ ሥራ የገቡት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርና የኢትዮ ጂቡቲ ምድር ፕሮጀክቶች ከአገልግሎታቸው ይልቅ ጣጣቸው የባዛ ሆነው ቀጥለዋል፣ ያስገኛሉ የተባለውን ያህል ጥቅም እየሰጡ አይደለም፡፡ የፕሮጀክቶቹን ሥራ መጀመርና ሊሰጡ የሚችሉትን ጠቀሜታ እንዳልዘመርንላቸው፣ አሁን ላይ ግብራቸውን ስናይ ለቅሶ እየቀደመን ነው፡፡ የፈሰሰባቸው ሀብት ያስቆጫል፡፡  

በተለይ አዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንስፖርት ጉዳይ አሁን ባለው አያያዙ ሐዲዱ ብቻ ሊተርፈን ይችላል፡፡ ከተማዋ ወደ 41 የሚደርሱ ባቡሮችን ይዞ ሲሆን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ምናልባትም ወደ 65 በመቶ የሚሆኑት አሁን ላይ ሐዲዱ ላይ የሉም፣ ቆመዋል ተበላሽተዋል፣ አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም፡፡ የበለጠ ሊያገለግሉ ሲገባ አሽቆልቁለዋል፡፡ ሥራ ከጀመረበት ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ በብልሽት ወይም በመለዋወጫ ዕጦት ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል፡፡ በሐዲዱ ላይ የሚሽከረከሩት ባቡሮች ቁጥራቸው እየቀነሰ መምጣት ደግሞ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ችግር በማቃለሉ ረገድ ይብዛም ይነስም አገልግሎታቸው የማይናቅ የነበረ ቢሆንም፣ ከዕለት ዕለት ግልጋሎታቸው እየቀሰነ፣ ተገልጋዮችን አስተጓጎሎ ቀጥሏል፡፡ ከመስመር የሚወጡት ባቡሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱና መልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ካልተደረገ፣ ሁለም ባቡሮች እስከ ወዲያኛው ሊቆሙ ይችላሉ፡፡ ‹እንደ ተርኪስ ባቡር ተገትረሽ ቅሪ›› በሚል ስንኝ እንደተደረደረለት የቀድሞ ባቡር ሁሉ፣ ‹‹እንደ አዲስ አበባ ባቡር ተገትረሽ ቅሪ›› እንዳይባል ብንሠጋ አይፈረድብንም፡፡ 

ይህ የሚያሳየን በትራንስፖርት እጥረት ፍዳውን የሚያየውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ወይም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ በማድረግ ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶች ላይ ጫናውን እንዲበረታ እያደረገ ነው፡፡ 

ለእነዚህ ባቡሮች ከመስመር መውጣት ዋነኛ ችግር ተደርጎ እየተጠቀሰ ያለው የመለዋወጫ ዕጦት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ ለመለዋወጫ ግዥ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ ዕጦት ነው፡፡ ይህ ምክንያት ግን የባቡር አገልግሎቱ በተጀመረ ወራት ዕድሜው ጅማሮ የሚነገርለት ሲሆን፣ አሁንም ችግሩ ብዙ በማይታይበት ወቅት እየተሰጠ ያለው ምክንያት ይኼው ቁጥራቸው እየጨመሩ የመጡትን ባቡሮች ለማንቀሳቀስ የውጭ ምንዛሪ ዕጦት በምክንያትነት እየቀረበ ነው፡፡ 

በአንፃሩ ደግሞ የእነዚህ ባቡሮች ዕዳ ቅጣት ጨምሮ እየተከፈለ ያለው በውጭ ምንዛሪ ነው፡፡ የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ሲገልጹ እንደተሰማው ዕዳው እየተከፈለ ነው፡፡ ያውም በወቅቱ ባልተከፈለበት ወቅት ቅጣት ታክሎ ሁሉ ዕዳው የሚከፈል መሆኑንም ሰምተናል፡፡

እስካሁን በቅጣት መልክ በውጭ ምንዛሪ የተከፈለው ገንዘብ ቢደማመር ግን፣ አሁን ለባቡሮቹ መቆም ምክንያት የሆነውን መለዋወጫ አይደለም ባቡሩን ራሱ ሊገዛ ይችል ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ 

ወትሮም የይድረስ ይደረስ ፕሮጀክት ነበርና በአግባቡ፣ በጥልቀት ጥናት ተደርጎ እንዲተገበር ያለመደረጉ ዛሬ ላይ ቀላል ዋጋ እያስከፈለ ነው፡፡ አሁን እየሰጠ ካለው አገልግሎት አንፃር እንመዝነው ከተባለ ‹‹አዲስ አበባ ባቡር አላት›› ከሚል ውጪ እየጠቀመ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ምናለ ለዚህ የፈሰሰው ሀብት ሚኒባስና አውቶብስ ተገዝቶበት ቢሆን፣ ዛሬ በሌለ የውጭ ምንዛሪ ያውም በተገቢው መንገድ ላላገለገለ ዕዳ ባልገፈገፍንና በኪሳራ ዓመታት እየቆረጠ ያለ ኩባንያ ባልታቀፍን ነበር፡፡ 

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ችግር ገና ከጥንስሱ ጀምሮ በችኮላ የተተገበረ ስለነበር ይዞት የሚመጣው ጣጣ ብዙ ከመሆኑም በላይ ባሉትም ባቡሮች ቢሆን ተገቢ ግልጋሎት እየሰጠ አይደለም፡፡ በየስድስት ደቂቃው ያገኟቸዋል የተባሉት ባቡሮች በስድስት ሰዓት የማይገኙበት አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ከተገኙም በኃይል መቆራረጥ አጉል ቦታ ቆመው አጠቃላይ የባቡር እንቅስቃሴ የሚታጎልባቸው ተገልጋዮች ምሬት ሳይመለስ ከስድስት ዓመታት በላይ ሊሆነው ነው፣ አሁን ደግሞ ብሷል፡፡  

 ቲኬት ቆርጦ ወደሚፈልገው ቦታ ለመሄድ የሚጠባበቅን ተጓዥ ባቡሮቹ የውኃ ሽታ በመሆኑ ከስንት ጉዳይ አሰነካክለውታል፡፡

ገራሚው ነገር የባቡሮቹ መቅረት ተገልጋዩን ከጉዳዩ ማሰነካከላቸው ሳያንስ፣ ለቲኬት ያወጡትን ወጪ መተካት እንኳን አለመቻላቸው የዚህ ባቡር ዕዳ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ተገልጋዮችንም መበደል ጭምር ሆኗል፡፡ እንደ ዜጋ ወይም እንደ ተገልጋይ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአግባቡ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት ቢሰጥ ከአገልግሎቱ የሚያገኘውን ክፍያ ሰብስቦ ዕዳውን ቢከፍል ምኞታችን ነው፡፡ ግን ይህ እየሆነ አይደለም፡፡ የአገልግሎቱ ማሽቆልቆል አይደለም ዕዳውን ለመክፈል፣ ራሱንም ለማስተዳደር እየቸገረው ስለሆነ መንግሥት ዕዳውን እየከፈለ ነው፡፡ ኪሳራ ማለት ይህ ነው:፡ በብላሽ የተሠራ ፕሮጀክት የምንለውም ለዚህ ነው፡፡  

የአገር ሀብት ያውም በብድር የተገኘ ነገር ትርፍም አጥቶ፣ በዕዳ ተነክሮ፣ በሌለ የውጭ ምንዛሪ በኪሳራ ዕዳው መከፈሉ ሳያንስ በአግባቡ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት ያለመስጠቱ ያማል፡፡ 

ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት ዕዳው እየተከለፈ መሆኑ ካልቀረ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ሰጥቶ ባቡሮቹ ተንቀሳቅሰው በኪሳራም ቢሆን ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ ቢደረግ ይሻላል፡፡ ምክንያቱም ያለብን የትራንስፖርት ችግር ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት ይህንን ባቡር በማንቀሳቀስ የሚያወጣው ወጪ ኅብረተሰቡን እንደ መደጎም የሚቆጠር ስለሚሆን፣ ይህንን ያህል ሀብት የፈሰሰበት ሀብት ብላሽ እንዳይሆን ቢወስን ጥሩ ነው፡፡ 

ስለዚህ ካለው የትራንስፖርት ችግር አንፃር ይሰጥ የነበረው አገልግሎት አጋዥ ነውና ወጪ መውጣቱ ካልቀረ ተገቢ የውጭ ምንዛሪ ተመድቦ ባቡሮቹን ወደ ሐዲድ መመለስ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ትራንስፖርት እየተጠቀመ ያለው አነስተኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ ክፍል በመሆኑ መንግሥት ኅብረተሰቡን ለማገዝ ለጊዜው ያለው አማራጭ ይህ ነው፡፡ 

ካልሆነ አሁን ግን መስመር ላይ ያሉት ባቡሮችም የነገ ዕጣ ፈንታቸው እንደ ሌሎቹ መቆም ነውና መጨረሻው ባቡር አልባ ሐዲዶች ይዞ መቅረት ይሆናል፡፡ ሌሎች አማራጮችም ካሉ በባለሙያዎች ተፈትሸው አገልግሎት ይቀጥል ዘንድ ማድረግ በረዥም ጊዜ ዕቅድ ደግሞ ከተማዋን የከፋፈለው ፕሮጀክት እየተካ የማድረጉ ሐሳብን ቢኖር መልካም ነው፡፡ አሁን ላይ ግን በኑሮ ውድነት የተማረረው ኅብረተሰብን በትራንስፖርቱ ረገድ እየገጠመው ያለው የበረታ ችግር እንዳያጎብጠው ባለው አማራጭ ሁሉ እነዚህ ባቡሮች ወደ ሐዲዳቸው እንዲመለሱ ይደረግ፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት