Monday, April 15, 2024

የሙስና አደጋ በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም. መንግሥት በሙስና በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ መውሰድ ጀመርኩ ያለው ተከታታይ ዕርምጃ፣ በጉዳዩ ላይ ያመረረ ያስመስለው ነበር፡፡ የፌዴራል አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በሙስና ተጠርጥረው የመታሰራቸው ዜና ትኩረት የሳበ ነበር፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የወጣው የ20/80 እና የ40/60 የአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ ውዝግብ ይዞ መምጣቱ ደግሞ ሌላ ትኩረት ሳቢ ጉዳይ ነበር፡፡ የቤት ዕጣ አወጣጥ ሒደቱ ተጭበረበረ ተብሎ መሰረዙና ለዚህ ደግሞ ተጠርጣሪ ናቸው የተባሉ ግለሰቦች መታሰራቸው፣ የሙስናና የብልሹ አሠራር ጉዳይ ዳግም የመነጋገሪያ አጀንዳ እንዲሆን የሚጋብዝ አጋጣሚ ነበር፡፡

በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበጀት መዝጊያ የፓርላማ ስብሰባ ላይ የሙስናን ጉዳይ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው የመንግሥት አጀንዳዎች አንዱ ይሆናል ብለው ነበር፡፡ የሐምሌ ወሩ ተከታታይ ዕርምጃም የዚሁ የመንግሥት ትኩረት ውጤት እንደሆነ ቢገመትም፣ ነገር ግን ብዙም ሳይገፋ ዕርምጃው መልሶ ሲቀዘቅዝ ነው የታየው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰኔው የፓርላማ ውሏቸውም ሆነ ከዚያ በፊት ባለው የሥልጣን ዘመናቸው፣ ሙስናን በተመለከተ የመረሩና ጠንካራ አስተያየቶች ከመስጠት ተቆጥበው አያውቅም፡፡ ዓብይ (ዶ/ር) ሙስናን ሳያሽሞነሙኑና በዳቦ ስሙ ሳይሆን ‹‹ሌብነት›› ብለው በቀጥታ በመጥራትም ሆነ ጠንካራ አቋም በመያዝ እንደማይታሙ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሙስና ተጋላጭነት ምዘናዎች ኢትዮጵያ የሚታይ ለውጥ ማምጣቷንም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሙስናና የምዝበራ ችግሮች አሁንም ቢሆን አገሪቱን በከባዱ እየፈተኗት መሆኑን ነው ብዙዎች የሚስማሙበት፡፡ ከዚህ በመነሳትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙስና ጠል አቋማቸውን በተጨባጭ በሙሰኞች ላይ ዕርምጃ በመውሰድ ቁርጠኝነታቸውን በተግባር እንዲያሳዩ የሚፈልጉ ወገኖች በርካታ ናቸው፡፡

ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በተደረገው 16ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ዓብይ (ዶ/ር)፣ ‹‹ፓርቲያችን ብልፅግና ግዴታውንና ኃላፊነቱን አውቆ የሚንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን፣ በሞራል ሕዝብን አገልጋይ እንዲሆን ብዙ ተሠርቷል፡፡ ነገር ግን በዚህ ረገድ ብዙ ጥረት ቢደረግም በዚህ ረገድ በቂ ውጤት አልመጣም፡፡ የሚሰርቅና ሌባ አመራር የምናፈራ ከሆነ ሁሉም ዕቅድና ልፋታችን ከንቱ ነው የሚሆኑት፤›› በማለት ነበር ሙስና የሥርዓቱ ከባድ ተግዳሮት መሆኑን ያስረዱት፡፡ በ2015 ዓ.ም. ዋና የትኩረት መስኮች ይሆናሉ ያሏቸውን ጉዳዮች ሲያስረዱም፣ ‹ብድር ቅነሳ፣ የበጀት ጉድለት ቅነሳ፣ የዋጋ ንረት ማረጋጋት፣ የአገር ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅ፣ መልሶ ማቋቋምና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲሁም ሀብትን በቁጠባ መጠቀም› የሚሉ ነጥቦችን ዘርዝረው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ የሙስናን ችግር በጉልህ ያነሱ ሲሆን፣ መንግሥት በ2015 ዓ.ም. በትኩረት ከሚሠራባቸው ጉዳዮች አንዱና ዋናው እንደሚሆን ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ጠንካራ ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ሲሉ ነበር ቃል የገቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ከተናገሩ ወራት ቢቆጠሩም፣ በሐምሌ ወር ከታየው የጥቂት ግለሰቦች እስራት ውጪ ሙስና ዋናው የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ ተከታታይነት ያለው ዕርምጃ ሲወሰድ አለመታየቱን በቅሬታ የሚናገሩ አሉ፡፡ መንግሥት እንደሚለውም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶታል የሚለውንም ይጠራጠራሉ፡፡

የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ካሳሁን ሙስና ተገቢ ትኩረት እንዳልተሰጠው ይናገራሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ሙስናን ለመከላከል በተለያዩ ጊዜያት ፍላጎቱን ከመግለጽ በዘለለ በተጨባጭ በተግባር የሚተረጎም ዕርምጃ መውሰድ ላይ እምብዛም ነው፡፡ ዕርምጃው ቢጀመር ኖሮ ለውጥ እናይ ነበር፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

አቶ አማኑኤል እንደሚናገሩት ከሆነ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከመጡ ወዲህ በሙስና ተጋላጭነት ኢትዮጵያ በጎ መሻሻሎችን አምጥታለች፡፡ ለአብነት እሳቸው ወደ ሥልጣን በመጡበት ዓመት ከ180 የዓለም አገሮች በሙስና ተጋላጭነት ሰንጠረዥ 114ኛ ደረጃ ላይ ኢትዮጵያ ተቀምጣ ነበር፡፡ በቀጣዩ ዓመት ከ180 አገሮች ትልቅ መሻሻል አሳይታ 96ኛ ደረጃን አገኘች፡፡ በተከታዩ ዓመትም ቢሆን ለውጥ በማሳየት 87ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ እንደቻለች ማሳያዎችን ያወሳሉ፡፡

ይህ የሙስና ተጋላጭነት ቅነሳ መሻሻል የመጣው ደግሞ፣ የዓብይ መንግሥት በዚህ ረገድ ዕርምጃ ወስዶ ለውጥ ያመጣል በሚል ተስፋና እምነት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ሆኖም በሒደት መንግሥት የተጠበቀውን ያህል ዕርምጃ ባለመውሰዱ፣ ‹‹ዛሬ ሙስና አካል አውጥቶ ገዝፏል፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ‹‹ድሮ በኮሚሽን ኤጀንቶች (ደላሎች) ነበር ሙስና የሚጠየቀው፣ ዛሬ ግን ራሱ ሌባው ሆኗል ስጠኝ የሚለው፤›› የሚሉት አቶ አማኑኤል የመንግሥት አገልግሎት መስጫዎች፣ የመሬት አገልግሎት፣ የዕቃ ግዥ ዘርፍ፣ የፋይናንስ ሴክተሩና ሌሎችም ለሙስና በእጅጉ እየተጋለጡ ያሉ መሆናቸውን አመልከተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ሁሉ መንግሥት ሙስናን መዋጋት በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚሉ ወገኖች፣ ከሰሞኑ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ወቅት ያቀረቡትን የዘንድሮ በጀት ዓመት የመንግሥት ዋና ዋና የሥራ ዕቅዶች ሪፖርትን ማሳያ በማድረግ ያቀርቡታል፡፡ ፕሬዚዳንቷ በዚህ የምክር ቤቶች መክፈቻ ሪፖርታቸው ላይ አንድም ጊዜ ሙስና የሚል ቃል አለመጠቀማቸው፣ መንግሥት ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ደካማነት አመላካች ነው ይላሉ፡፡ ወደ 25 ደቂቃዎች ባስቆጠረው የፕሬዚዳንቷ ንግግር ሙስና፣ ሌብነትና ምዝበራ የሚሉ ቃላት ሳይጠቀሱ ነው የሚቋጨው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ጉዳዩን አላተኮረበትም የሚል አስተያየት እያስነሳ ነው፡፡

እርግጥ ነው ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ የአገልግሎት አሰጣጥን ስለማሻሻልና ስለማዘመን በዝርዝር አውስተዋል፡፡ ስለመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሕዝብ እንግልትም ተናግረዋል፡፡ የኑሮ ውድነትና ድህነትን በማንሳትም እነዚህን ችግሮች ለማቃለል መንግሥት ብዙ እንደሚሠራ ነው ያብራሩት፡፡ ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ስላለው የሙስና ቀውስ፣ እንዲሁም በመንግሥት ስለተሰጠው ትኩረት ይህ ነው የሚባል ትኩረት አለመሰጠቱን በማንሳት አንዳንድ ወገኖች በመናገር ላይ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የሙስና ተጋላጭነት ገጽታ ምን ይመስላል? ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ መስኮች የትኞቹ ናቸው? ለሚለው ጥያቄ ከፌዴራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን መረጃ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ ባይሳካም ድርጅቱ ‹ፀረ ሙስና› ብሎ ለመጀመርያ ጊዜ በሐምሌ ወር ባሳተመው ጋዜጣ ላይ ሁኔታውን ለመገንዘብ የሚረዱ በርካታ ነጥቦችን አስነብቧል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት 3,655 የሙስናና ብልሹ አሠራር ጥቆማዎች እንደደረሱት ያመለከተው ተቋሙ፣ 2,348 የሚሆኑ ጥቆማዎችን በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ሥራ ማምከኑን ይናገራል፡፡ በዚህም ሥራ ከ406 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ከምዝበራ መታደጉን፣ ከ68 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ከቅርምት ማዳኑን፣ ከ97 ሺሕ ሔክታር በላይ የገጠር መሬት ማዳኑን፣ እንዲሁም ከ275 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ከብክነት ማትረፉን ነው ተቋሙ ያስረዳው፡፡

ኮሚሽኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ከወረዳ እስከ እላይ ላሉ አመራሮች ሥልጠና እንደሰጠ ከመጥቀስ ባለፈም፣ የባለሥልጣናትን ሀብት በዲጂታል መንገድ ለመመዝገብ የሚያስችል አሠራር ማበጀቱንም በሰፊው ይዘረዝራል፡፡ ከ6,537 በላይ አመራሮች ሀብትና ንብረት መመዝገቡን ገልጾ፣ የ382 ግለሰቦች መረጃ ትክክል ሆኖ ባለመገኘቱ ዕርምጃ መውሰዱን ይናገራል፡፡

 ይሁን እንጂ ከ2002 ዓ.ም. የጀመረው የሀብት ምዝገባ በበቂ ሁኔታ አለመከናወኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች በቅርብ ጊዜያት ሲወጡ ታይተዋል፡፡ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. የሀብት ምዝገባ መርሐ ግብሩ ሲጠናቀቅ ዋዜማ የዜና ምንጭ አጣራሁ ብሎ ባወጣው ዘገባ፣ ከ2.3 ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ 72 ሺሕ ብቻ ሀብት ማስመዝገባቸውን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል ተከናወኑ የሚባሉ ሥራዎች የተዓማኒነት ጥያቄ ሲነሳባቸው ይታያል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የሙስና ተጋላጭነት በአገሪቱ አስከፊ ገጽታን እየያዘ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡

ሰኔ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ 24 የመንግሥት ተቋማት ከተፈቀደላቸው በጀት በላይ መጠቀማቸውን ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ በኦዲት ግኝቶች ሁሉም ለሙስናና ምዝበራ የተጋለጡ ናቸው ባይባልም እንኳ ጉድለቶቹ የሙስና ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ተቋሙ በየዓመቱ በሚያወጣቸው ሪፖርቶች የሚያስረዳው፡፡ ለአብነት በኅዳር 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ዋና ኦዲተር ባቀረበው ሪፖርት ከ511 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከብክነት ማዳኑን አረጋግጧል፡፡ ተቋሙ በዚህ ሪፖርቱ በሐሰተኛ ደረሰኝ ነዳጅ ሳይቀዱ ቀዳን ብለው ገንዘብ የሚመዘብሩ የመንግሥት አሽከርካሪዎች ጉዳይ ይታሰብበት ሲል ገልጾም ነበር፡፡ በፌዴራል ተቋማት በተለይ በ53 ዩኒቨርሲቲዎች ያለው የሀብት አስተዳደር ጉድለት ጉዳይ ቁጥጥር እንደሚያስፈልገውም ለፓርላማው ባቀረበው የክዋኔ ኦዲት ጠቁሞ ነበር፡፡

የምዝበራና ሙስና ተጋላጭነት የመንግሥት ተቋማትን ብቻ ሳይሆን፣ በብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል የሚደረግባቸው የንግድ ባንኮችንም ጭምር እየፈተነ ያለ ችግር መሆኑ ይነገራል፡፡

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋ፣ የፋይናንስ ዘርፉ ለሙስናና ምዝበራ ተጋላጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹በሴክተሩ የሙስና ሁኔታ ይህ ነው ብሎ በአኃዝ ለማስቀመጥ ብዙ ማጥናት ቢጠይቅም፣ ዘርፉ ብዙ ገንዘብና ሀብት የሚንቀሳቀስበት እንደ መሆኑ መጠን ለሙስና እጅግ ተጋላጭ ተብለው ከተለዩት አንዱ ነው፤›› በማለት አቶ እንዳለ ያክላሉ፡፡

ይሁን እንጂ የፍትሕ ሚኒስቴር ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት፣ በ16 ባንኮች ላይ በተካሄደ ምርመራ ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ማጭበርበር መፈጸሙን የሚያረጋግጥ አስደንጋጭ መረጃ ማውጣቱ አይዘነጋም፡፡

የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነርና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ከፍተኛ አመራሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ሙስና ዘርፈ ብዙ ገጽታ እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሙስና በባለሥልጣንና በባለሀብት መካከል የሚደረግ ሕገወጥ የጥቅም ግንኙነት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ በአብዛኛው እውነት ቢሆንም፣ ነገር ግን የሙስና አድማስ እጅግ ሰፊ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ማንም ሰው እኔ ንፁህ ነኝ ስላለ ብቻ ከሙስና አደጋ አይድንም፤›› የሚሉት አቶ ግርማ፣ በማንኛውም መንገድ የሚፈጸም ሙስና ዞሮ ዞሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ተጎጂ የሚያደርግ የቀውስ አዙሪት እንደሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

በመንግሥት አገልግሎት መስጫዎች፣ በግዥ ዘርፍ፣ በመሬትና በኮንስትራክሽን ብቻ ሳይሆን በንግድና ግብይት ዘርፍም ሙስናና ምዝበራ እንደሚታይ መንግሥትም ይናገራል፡፡ አሁን በአገሪቱ ለሚታየው የዋጋ ንረትና የገበያ አለመረጋጋት የንግድ አሻጥርን አንዱ ምክንያት አድርጎ መንግሥት ይናገራል፡፡ በወጪና ገቢ ንግድ ከዋጋ በላይና ከዋጋ በታች የሆነ ደረሰኝ በማቅረብ ማጭበርበር እንደሚፈጸም ያክላል፡፡ ግብር ሥወራና ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ለማስመሰል የመሞከር ድርጊት በሰፊው የሚታዩ የሙስና ገጽታዎች መሆናቸውን ነው መንግሥት በተደጋጋሚ የሚገልጸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሙስናና ምዝበራ ከዚህም አልፎ የእምነት ተቋማት ውስጥ ጭምር መግባቱን ይናገራሉ፡፡ ‹‹የእምነት ተቋማት ከሊዝ ነፃ የሆኑት፣ ግብር የማይከፍሉትና ኦዲት የማይደረጉት በግብረ ገብ የታነፁና አገር ለመገንባት ክፍተቶቻችንን ይሞላሉ ተብሎ ነው፡፡ አሁን እንደምናየው ግን ተቋማቱ ፖለቲካ ሲሠሩ ነው የሚገኘው፤›› በማለት ነበር በሰኔው የፓርላማ ውሏቸው በምሬት የተናገሩት፡፡

የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ ‹‹በኢትዮጵያ ሙስና መስፋፋቱ በእጅጉ ያሳስበኛል፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡ አደጋው የመግዘፉን ያህል ትኩረት እንዳላገኘ የሚጠቅሱት አረጋ (ዶ/ር)፣ አገሪቱን ለከባድ አደጋ የሚዳርግ ችግር መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ሙስና ካንሰር ነው፡፡ በቀላሉ የሚዛመት ሱስ ነው፤›› ሲሉ የተናገሩት ምሁሩ፣ ችግሩን አገሪቱ ትኩረት ሰጥታ ለመከላከል ካልሠራች የሚገጥማት አደጋ ከባድ መሆኑን ነው የሚያሳስቡት፡፡

በሙስናና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ ከማጥናት ጀምሮ ሥልጠናና ግንዛቤ የመስጠት ሥራ የሚሠራው የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ ተቋም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አማኑኤል፣ ይህን ሥጋት እንደሚጋሩ ይናገራሉ፡፡

‹‹ሙስና ፖለቲካዊ ይደረጋል፡፡ ከብሔር ጋር ይያያዛል፡፡ በችሎታ ሳይሆን በዝምድናና በጥቅም ለመዝረፍ የመቧደን ባህል ይታያል፡፡ በሥልጣን መባለግም ቢሆን ተንሰራፍቷል፡፡ ነገር ግን ሌባ ሃይማኖት፣ ብሔርም ሆነ ቡድን የለውም፡፡ ስለዚህ አይነኬ የሚባል ሙሰኛ መኖር የለበትም፤›› ሲሉ፣ ሙስናን የመዋጋት ትግሉ እስከ የት መሄድ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡

የኑሮ ውድነት በሰፋበትና የሸቀጦች ዋጋ አልቀመስ ባለበት በዚህ ወቅት ከድሆች ጉሮሮ ነጥቆ ሀብት ማጋበስ ትልቅ ኃጢያት እንደሆነ ነው አቶ አማኑኤል የሚናገሩት፡፡  ይህም ቢሆን ግን ሌብነትና ሙስናን ተገቢ ለማድረግ ምክንያት ሊቀርብ እንደማይችል በመጠቆም፣ ‹‹ኑሮዬ ወይም ገቢዬ አነስተኛ ስለሆነ ሰረቅኩ ማለት አሳማኝ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

ሙስና በኢትዮጵያ በእጅጉ መንሰራፋቱንና ብዙ ገጽታ ማበጀቱን የገለጹት አቶ አማኑኤል፣ ‹‹መንግሥት አንድ ሰሞን ብቻ ዕርምጃ ከመውሰድ ባለፈ ተከታታይ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፤›› ይላሉ፡፡ እየነካኩ መተው አንዳንድ ችግሮችን የበለጠ ሊያባብስ እንደሚችል ነው ሥጋታቸውን የገለጹት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -