‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡
አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡
‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡ ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡
‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡
ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …
‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡
ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡
‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡
- አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)