Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊቅነሳ ያላሳየው የጨቅላ ሕፃናት ሞት

ቅነሳ ያላሳየው የጨቅላ ሕፃናት ሞት

ቀን:

የእናቶችና ሕፃናት ሞት ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት መጠነ ሰፊ ሥራዎች ቢሠሩም በአሁን ጊዜ በተለይ የጨቅላ ሕፃናት የሞት ቁጥሩ ግን መቀነስ አለማሳየቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የጨቅላ ሕፃናትን ጽኑ ሕመም የሕክምና አገልግሎት ጥረት ለማሻሻል በተዘጋጀው የምክረ ሐሳብ መድረክ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ደረጀ ድጉማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በዘርፉ የተገኙ መሻሻሎች ቢኖሩም በኢትዮጵያ ያለው የጨቅላ ሕፃናት ሞት መጠን በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቷል፡፡

‹‹የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ሪፖርት የማድረጉ ሥራም ሲታሰብበት ይገባል፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ በኢትዮጵያ ከሚሞቱት ጨቅላ ሕፃናት ውስጥ ከአሥር በመቶው በላይ ሪፖርት እንደማይደረግ፣ ሪፖርት ካልተደረገ ደግሞ በዚያው ደረጃ ምላሽ ለመስጠት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

የጨቅላ ሕፃናትን ጽኑ ሕመም የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማሻሻል የተከናወኑ የጤና ልማት ሥራዎችን በገመገመው የጥቅምት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. መርሐ ግብር ላይ ሚኒስትር ዴኤታው እንዳብራሩት፣ በ2008 ዓ.ም. በተካሄደው ጥናት አዲስ ከተወለዱ 1000 ሕፃናት መካከል 30ው ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ከዚህም ሌላ በ2011 ዓ.ም. በተካሄደው ተመሳሳይ ጥናት የሟቾች ቁጥር ወደ 33 አሻቅቧል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ተመሳሳይ ውጤት እንዳለ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማብቂያ ወይም ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ አሁን ያለውን 33 የሞት መጠን ወደ 21፣ በ2022 ዓ.ም. ደግሞ ደግሞ ወደ 12 ለማውረድ እየተከናወነ ነው፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ በየክልሉ በሰማንያ ዞኖች በሚገኙ 80 ሆስፒታሎች የሦስተኛ ደረጃ የጨቅላ ሕፃናት የጽኑ ሕመም ክብካቤ ክፍል በ24.2 ሚሊዮን ዶላር በማደራጀት ወደ ሥራ እንዲገቡ ክፍሎቹም በ34 ዓይነት ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች የተደራጁ ናቸው፡፡

የጽኑ ሕሙማን ሕክምና አገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ በተመረጡ ሆስፒታሎች የከፍተኛ ደረጃ የጨቅላ ሕፃናት ጽኑ ሕመም ሕክምና መስጫ ክፍሎች በመሠረተ ልማት ላይ ያተኮሩ ተግባራት መከናወናቸውን የገለጹት፣ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ሥርዓተ ምግብ ዳይሬክተር መሠረት ዘላለም (ዶ/ር) ናቸው፡፡  በዘመናዊ መሣርያዎች ተከላ፣ ገጠማና ለባዮሜዲካል ኢንጂነሮችና አገልግሎቱን ለሚሰጡ ነርሶችና ሐኪሞች የአቅም ግንባታ ሲተገብር መቆየቱንም አስታውሰዋል።

በዚህም የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረጉ የጨቅላ ሕፃናት የጽኑ ሕመም ሕክምና አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆንና አላስፈላጊ የሕሙማን ቅብብሎሽ (ሪፈራል) እንዲቀንስ የበኩሉን ድርሻ እንደተወጣም ገልጸዋል፡፡

በከፍተኛ ወጪ የተገዙትን መሣሪያዎች በተገቢው ደረጃ ለማስተዳደር የክልል ጤና ቢሮዎችና ሆስፒታሎች ተገቢውን ባለሙያ መመደብ፣ ለጥገና ሥራ በቂ በጀት መያዝና ተያያዥ ጉዳዮችን መፈጸም እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናትን ሕይወት መታደግ እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታወሱት፣ በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ምክትል ተወካይ ጄን ሚታ (ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስቴር ጽኑ ሕሙማን የሚታከሙባቸውን መሣሪያዎች ከውጭ በማስገባትና ባለሙያዎችን በማሠልጠን ሥራ ማስጀመሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

የእናቶችና የሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችንና ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ እንሠራለን ሲሉም ቃል ገብተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...