Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቋጥኝ ሸክሞቻችን!

ሰላም! ሰላም! መስከረም አልቆ ጥቅምት ውስጥ ሆነን፣ ከጥቅምት አበባ ጋር ንፋሱ ሽው ሲልብን ፀደይና ውበት እንዴት ይዘዋችኋል ያሰኛል፡፡ ለካስ ዘንድሮ ለመዋብ ቦታና ጊዜ መምረጥ ተትቷል።  ለነገሩ ወቅቱ ከተዛባም ቆየ እኮ። ምን ያልተዛባ አለ አትሉም? እኛም ኑሯችንም እንደ አየር ንብረቱ ሁሉ ውጥንቅጣችን ከወጣ ሰነባብተናል። ታዲያ በዚህ ዓይነቱ ወቅትም የስንቱ ሰው የፍቅር ትዝታ ያለባት ፀደይን ሳነሳ፣ የብዙዎቻችሁን ትዝታ ሳልነካካ ቀረሁ ብላችሁ ነው? ማለት? ካላችሁኝ በሰፊው ላጫውታችሁ። አንዱ ጩልሌ ልክ እንዳያችሁ በተለይ ከአንድ አሥር ዓመት በፊት ትንሽም ቢሆን ዕውቂያ ከነበራችሁ፣ እንደሚከተለው ብሎ በመነዝነዝ ይጀምራል። ‹‹አቤት ጊዜ፣ ምን ያላሳለፍነው አለ ብለህ/ሽ ነው?›› በማለት ጀምሮ፣ ‹‹ውኃ ሽቅብ ሲወጣ ዱባ ዛፍ ላይ ሲበቅል›› ዓይነት ወሬ እያወራ የነበረውንም ያልነበረውን አስታውሶ ንዝንዝ ያደርጋችኋል። ኑሯችን እንደ ‹ጀምስ ቦንድ› ፊልም በ‹አክሽን› ተሞልቶ ዕፎይ ማለት ከብዶናል፣ እንዲህ ያሉት ደግሞ እንደ ምዕራባውያን ጥልቅ እያሉ ይበጠብጡናል። ‹‹አይገርምህም? የነበር የነበርማ እግዜርስ ራሱ ሰውን በመፍጠሩ መቼ ይፀፀት ነበር? ጊዜን መልሶ ሰውን ከምድር መዝገብ መሰረዝ ሲችል…›› ይላሉ አዛውንቱ ባሻዬ ነገር የሚያበዛ ሰው ሲያጋጥማቸው። ምን ያድርጉ ታዲያ!

ለማጣፈጥ አንድ ነገር ልጨምር። እንዲህ ያሉት የትናንት ወገኞች ደህና ነገር በልተው አልያም ሰምተው አገኟችሁ ማለት አለቀላችሁ ማለት ነው፡፡ ‹አብዮታችን ባይቀለበስ፣ ሶሻሊዝም አድጎ ኮሙኒዝም ቢገነባ፣ ኢምፔርያሊስቶችን ማባረር ችለን ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ አገር ከላይ እስከ ታች በወገን ላይ በሚያላግጡ ምግባረ ብልሹዎች ባልተጣበበች ነበር…› ዓይነት ትኩሳት የሚለቅ ነገር ሲለቁባችሁ ልባችሁ ቅልጥ ይላል። ይህን ጊዜ ተነስታችሁ መሄድ አልሆንላችሁ ይላል። ዛሬን በትናንት ክፉኛ ትኮንኑና ነገ ጨልሞ ልቦናችሁ ዓይናችሁን ካልወጋሁት ይላችኋል። ጮማ እያማራችሁ በዋዛ እንደማይገኝ ትዝ ሲላችሁ ደግሞ ጮማ ወሬ መዘልዘል በመቻላችሁ፣ ራሳችሁን እንደ ታላቅ ዕድለኛ ቆጥራችሁ ቁጭ ነው። ‹‹ገንዘብ መቁጠር ሲያቅት ዕድላችንን ለማቃናት ከኮብ ቆጠራ መጀመራችንም አይደል… ይሁን እስኪ…›› ይሉ ነበር ባሻዬ ይህንን ጉድ ቢሰሙ፡፡ ምሁሩ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹አዕምሮአችንን ማሠራት ሲያቅተን ሕይወታችንን ለምትሃታዊና ለትንቢት መሰል ዕድሎች አሳልፈን እየሰጠን እንጃጃላለን፡፡ ኮከብ ቆጣሪው የራሱን ሳያውቅ የእኔን አውቅልሃለሁ ብሎ ቢያጃጅለኝ፣ ጥፋተኛው እኔ እንጂ እሱ አይደለም…›› ብሎ ‹ታክል› ይገባል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

ይኼው በዚህም ብለን በዚያ እየኖርን ነው። ጊዜውም ሳንሠራበት እያወራንበት እየሮጠ ነው። ‹‹ዘንድሮ ሳይንሱ ከእውነት ይልቅ በፈጠራ ውሸት መኖር ለሰው ልጅ ጤነኛ አኗኗር መልካም ነው ያለ ይመስል እየተሸወድን ነው…›› እንደሚለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ስለራሳችን በብዙ ውሸቶች ታጥረን እንኖራለን። ግን አንዳንዴ ያው እንደምታውቁት ኪስ ሲራቆት በዋዛ ያሳለፍነው ትዝ ስለሚል ጤና አይዘንም። እኔም ድንገት ኪሴን ብዳብሰው 105 ብር ናት የቀረችኝ። ‹የደላላ ውሸታም አንተን አየን…› እያላችሁኝ መሆን አለበት፡፡ አስባችሁታል በዛሬ ጊዜ አዋዋል እንኳን 105 ብር እኔ ራሴ መቶ አምስት ቦታ ብተረተር ለምን ልበቃ? ወዲያው ከተማውን ቃኘት ቃኘት ማድረግ እንዳለብኝ ወስኜ እንደ ጥንታውያን አሳሾች ጉዞዬን በእግሬ ጀመርኩት። ለእግር ግብር ክፈሉ ወይም በቴሌ ሲም ካርድ ተጠቀሙ ቢባል ምን ሊውጠን ነበር ግን? ‹ሳይደግስ አይጣላ…› አትሉም። አንድ ወዳጃችን ደላላ አዲስ አበባን እያካለለ የሚሠራው ድለላ አግኝቶ ታክሲ ጥበቃው ቢያቅተው በእግሩ መንገዱን ጀመረው፡፡ ይታያችሁ እስቲ ከቦሌ ተነስቶ ለቡ፣ ከሃያ ሁለት ጀምሮ ልደታ፣ ከፒያሳ ተነስቶ መገናኛ… ታከተው፡፡ ሜትር ታክሲ አይከራይ ነገር እሱም ጣራ ነካ፡፡ ‹‹እዚህ አገር ሰው ሲረክስ ሁሉም ተወዷል…›› ብሎ ሲነግረን ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡ እውነት ነው!

እግረ መንገዴን ለወዳጄ በዚህ ብንለው ብንሠራው ፍንክች አልል ስላለው ኑሮ አንስቶ ያለኝን ላጨውታችሁማ። እግርን እግር፣ ጨዋታን ጨዋታ አነሳው ማለት ታዲያ እንዲህ እኮ ነው፡፡  ይኼ ወዳጄ፣ ‹‹ዶላር ከሌለ ለምን አገሪቱንም አይዘጓትም?›› ሲለኝ፣ ‹‹እንዴት ማለት?›› አልኩት። የአንዳንዱ ሰው አማርኛ የሰዋሰው ችግር ቢኖርበትም ጭብጥ አላገኝበት እያልኩ ስለሆነ ለማጣራት ጓጉቼ። ዳሩ ሰው በሰው ላይ እየተረባረበ ጉድ ባስባለን ዘመን ሰዋሰው ለሰው ምኑ ሊሆን? ‹‹በቃ ኑሮአችን በጥቁር ገበያ የሚመራ እስከሚመስል ድረስ በየደረስንበት ዋጋ ጨምሯል ነው፡፡ በቀደም ዕለት የሸቀጣ ሸቀጥ ግሮሰሪ ገብቼ አንድ ኪሎ በሶ ስጠኝ ስል በአንድ ጊዜ ሰላሳ ብር ጨመረብኝ፡፡ የበሶ ዋጋ ጭማሪ ምክንያቱ ምን ይሆን ብዬ ሻጩን ስጠይቀው፣ ‹እናንተ የምትደልሉት መኪና በቆመበት አንድ ሚሊዮን ብር ሲጨምር ይኼ ምን ይገርምሃል ብሎ› ቆሌዬን ገፈፈው፡፡ ይታይህ እንግዲህ የቅንጦት መኪናውና የእኔ ቁርስ የሆነው በሶ ዋጋቸው በጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሪ ተመን እኩል ሲዳኙ፣ ለመሆኑ መንግሥት አለ ወይስ እሱም ወደ ስደት እየሄደ ነው…›› ብሎ በንዴት ሲስቅ እኔ ግን ፊቴ ደመና መስሎ ነበር፡፡ ወይ ነዶ!

እኔም ኑሮ ጀርባዬን አጉብጦት መንገድ ላይ የማገኛቸውን ደላላ ወዳጆቼን እያነጋገርኩ፣ ደህና ዝግ የምዘጋበት ሥራ ሳፈላልግ ግማሽ ቀን አለፈ። ለእኔ ያለው እስኪመጣ ለሌላው ያለውን በወሬ ደረጃ ሳጋግል ቆይቼ ‹‹ኤግዘከቲቭ ቶዮታ›› የሚባል መኪና ይሸጣል ሲሉኝ ገዥ ፍለጋ መቅበዝበዝ ጀመርኩ። እግረ መንገዴንም ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም እንዳከራይ ተነግሮኝ ስነበር፣ በሰላሳ አምስት ሺሕ ብር የሚከራይ ተገኝቶ ጨራርሼ ወዲያው መኪናውን ገዥ ማፈላለጌን ቀጠልኩ። ዘንድሮ የሻጭና የገዥ ብዛትና ዓይነት ጉድ ነው መቼም። ዘንድሮ ብሩ ከየት እንደሚመጣ ባላውቅም ከተማውን ወጣት ባለገንዘቦች ሞልተውት ጉድ እያልን ነው። አንዱ እነዚህን ኳስ ጠልዘው ያልወጣላቸው ወጠጤ ባለገንዘቦችን ‹ንፋስ አመጣሽ› ይላቸዋል፡፡ ይህንን ስል የሰማኝ የኮንዲሚኒየሙ ተከራይ፣ ‹‹እንደ እኔ ያለው ምስኪን ይኼው ቤተሰቡን ለማሳረፍ ሲል 35 ሺሕ ብር እየከፈለ በቀን ሦስቴ ብቻ እንደነገሩ እየቀመሰ ይኖራል። ይኼ አሁን ምን ተኖረ ይባላል….›› ብሎ ሊያስቀኝ ሞክሯል። እሱም እኮ በቤቱ ‹ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ተሁኖ ምን ኑሮ አለ?› ማለቱ እኮ ነው። ከበታቹ ያሉትን ዘቅዝቆ ማየት ከብዶት ይሆን ወይም ከላይ ያሉት ሰዎች ሁኔታ አብግኖት ይሁን አላውቅም፣ ብቻ ሰውየው የገዛ ቪላውን ወይም አፓርታማውን ለሀብታም ቅምጥ አከራይቶ ኮንዲሚኒየሙን መከራየቱ ያስታውቅበታል፡፡ እንዴት አይታወቅ! 

የሚገርማችሁ ደግሞ ‹አለሁ› እና ‹አለኝ› እያልን ካልዋሸን የምንዘልቀው ዓይነት እንዳልሆነ የሚያረጋግጥ አጋጣሚ ከኮንዶሚኒየሙ ግቢ ሳልወጣ አያጋጥመኝ መሰላችሁ? ውል ተፈራርመው አከራይና ተከራይ እንደተስማሙልኝ ኮሚሽኔን ወስጄ ለ‹‹ኤግዘከቲቩ›› ሽያጭ ልሮጥ ስንደረደር አምባጓሮ መሰል ጭቅጭቅ ገጠመኝ። ‹‹እሺ ቢያንስ ልሸኝሽ?›› ይላታል አንዱ ጎረምሳ እንዳታመልጠው እየታገለ። ‹‹ልቀቀኝ ብዬሀለሁ ዛሬ…›› ትላለች ወጣቷ ቆንጆ። ‹‹አሁን ምን አቅለበለበው?›› ትላለች አንዷ ውስጥ አዋቂ ታዛቢ። ‹የራሱ ያልሆነውን የእኔ ነው ብሎ ያውም ለእጮኛው ይዋሻል? የዘንድሮ ፍቅርስ ኧረ እንጃለት?› ይባባላሉ ቀስ በቀስ እሷን መሰሎች እየተሰባሰቡ። ወሬ አነፍናፊ ነዋሪዎች ግቢውን ሰላማዊ ሠልፍ የወጡ አስመስለው ሞሉት። ይኼን ያህል ምን ብሎ ነው አትሉም? ጓደኛው ሊሸጠው አስጭኖ ያስመጣውን መኪና የእኔ ነው ብሎ እጮኛውን አንሸራሽሮ ሲያበቃ እውነቱ ባርቆበት ነዋ፡፡ ይኼኔ ጠዋት የማንጠግቦሽን ዘይት የናፈቀውንና ቅቤ ሕልም የሆነበትን ደረቅ ፍርፍር እየበላሁ የሰማሁት ዜና ትዝ አለኝ። ዜናው፣ ‹‹ዘንድሮ የታየው የስንዴ ልማት ውጤታማነቱ አመርቂ በመሆኑ በቅርቡ ኤክስፖርት ይጀመራል…›› የሚል ነበር። መጀመሪያ ለእኛ ይዳረስ ከዚያ ለሌላው ይትረፍ ብንል መልካም ነው ለማለት ነው፡፡ አዎ ለማለት ያህል ነው!

ጉድ ነው እያልኩ ሩጫዬን ስቀጥል ስፖርተኛ እንዳልመስል ይህ የነተበ ካፖርት ይጎትተኛል፡፡ በኑሮ ቋሚ አሠላለፍ ውስጥ ለመካተት ሸንቃጣ መሆን ጠቃሚ ነው፡፡ እኔ ከተማውን ሳካልል እየዋልኩ የአዲዳስ፣ የፑማ፣ የናይኮ ወይም የፊላ የስፖርት ቱታ ከእነ ስኒከሩ ባደርግ ኖሮ ሸንቃጣነቴ ይታይ ነበር፡፡ ግና ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ለዚህ አልታደልኩም፡፡ በዚህ ሐሳብ ውስጥ ሆኜ ቤት ደረስ ብዬ ውዷ ማንጠግቦሽን አቅፌ ስሜ ዛሬ እንኳን ጃኬት ደርቤ ልወጣ ስል፣ ከዓይኖቿ ሐዲድ ላይ እንባ ቅርር ሲል አየሁ። መጀመሪያ ለእኔ ያላት ጥልቅ ፍቅር መስሎኝ ልቤ በኩራት አበጠ። እሷ ግን የእኔ ካፖርት አውልቆ በጃኬት ለመሸለል መሞከር ምክንያቱ እንደሆነ ስትነግረኝ ከመደንገጥም አልፌ ተገረምኩ። ማንጠግቦሽን ከእኔ ከባለቤቷ ይልቅ ሐሳቧን ገዝቶ ሊያሸንፋት በቻለው ቅናት ላይ ቀናሁ። ለመሆኑ ለአንድ አፍታ አንድ ዓይነት ችግር መሆን አምሯችሁ ያውቋል? ምክንያቱም ሰው ከችግሩ ውጭ ለእናንተ ጊዜና ዋጋ (ዋጋ ያልኩት ለሐረግ ማሟያነት እንጂ ዋጋ ቢስነታችን እየባሰበት እንደመጣ ጠፍቶኝ እንዳይመስላችሁ) ሰጥቶ ማሰብ ትቷላ። ‹‹አንበርብር…›› አለችኝ ድምጿን ለስለስ አድርጋ። የእኔዋ ማንጠግቦሽ እንዲህ መንፈሷ ተሰብሮ እንኳን በእውኔ በሕልሜ አጋጥማኝ አታውቅም። ‹‹እባክህ አንተን የማያገኙብኝ ወደ አንዱ አገር እንጥፋ…›› ስትለኝ፣ አብዮታዊ ዕርምጃ ውሰዱበት የተባልኩ ይመስል አመዴ ቡን አለ፡፡ በስንት ማፅናናትና ግሳፄ ካረጋጋኋት በኋላ ወጥቼ ሄድኩ። የማንጠግቦሽ የሰሞኑ አመል እንዲህ እንዳይመስላችሁ። ብቻ ደርሶ እንባ እንባ ሲላት ብታዩዋት የእኔ ሚስት ስለሆነች ሳይሆን፣ እንዲሁ ራርታችሁላት አትጠግቡም። እንዲህ ብዬ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ብነግረው፣ ‹‹በማንጠግቦሽ አልተጀመረም ቅናት፡፡ የአገሩ ሰው ሁሉ በቅናት አይደለም እንዴ እርስ በርሱ የሚጠባበቀው…›› ብሎ ከአገሬው ጋር ደባለቀው። እሱ ደግሞ ትንሹንም ነገር ሳይቀር በፖለቲካ ሒሳብ ማስላት ሲወድ አይጣል ነው፡፡ ለምዶበት ነው!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ከስንት ውጣ ውረድ በኋላ ገዥ ተገኝቶ መኪናው ተሸጠ። እኔም ጠቀም ያለ ጉርሻ ይዤ ቀኑም መሽቶ ስለነበር ወደ ሠፈሬ ልመለስ አሰብኩ። ወዲያው፣ ‹‹እዚህ አገር ሐሳብ ነው እንጂ ተግባር ብርቅ ከሆነ ብዙ መንግሥታት ዓይተናል…›› የሚሉት ባሻዬ ትዝ አሉኝ። እንዴት ትዝ አይሉኝ መመለሻ ታክሲ አጥቼ ስገተር። የቀኑ ፀሐይ ደግሞ በአንድ በኩል ልብ ይነሳል። ታክሲ እስኪገኝ ካፌ ገብቼ ለማሳለፍ ሳስብ በዘንድሮ የዋጋ ውድነት ተራግፌ ልገባ ሆነ። ደግሞ ባለትዳር ነኝ። ‹ባለትዳር ካፌ አይገባም ያለው ማን ነው?› ብላችሁ ያሰባችሁ እንደሆነ ሰሞኑን ከምሰማው የአንዳንድ ካፌዎች ፍቅረኛ የማገናኘት ሥራ ከመነሳት መሆኑን ልብ እንድትሉልኝ እጠይቃለሁ። መጨረሻ ላይ የገረመኝ ደግሞ ካላጣሁት ዘዴ ሜትር ታክሲ ይዞ ለመመለስ ማሰቤ ነው። ‹‹ዝም ያሉት ማሽላ ስንዴ ነኝ ይላል…›› ብለው ፈጥረው ይሁን ወይ ሲባል ሰምተው፣ ለጆሮ አዲስ የሆነ ባሻዬ የሚተርቱት ተረት መጣብኝ። ለነገሩ አቅም አላውቅ ያልነው ሁላችንም ሆነናል፡፡ አቅማችንን ብናውቅና ብናገናዝብ ኖሮ ሸንተረር ለሸንተረር እየተሳደድን እንጨራረስ ነበር ወይ እንዳልል፣ የኑሮው ክብደት ቀና አላደርግ ብሎኝ ያንገዳግደኛል፡፡ ቋጥኝ በሉት፡፡

ከብዙ ሺሕ ሜትሮች ዕርምጃ በኋላ ሠፈሬ ተቃረብኩ። ከተለመደችዋ ግሮሰሪ ደጃፍ ‹‹አንበርብር!›› ብሎ የጠራኝ ድምፅ ጆሮዬ ደረሰ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነበር። ግሮሰሪያችን ተሰይመን የባጥ የቆጡን ስናወራ አንደኛችንን ጨርሰን ሁለተኛችንን አዝዘናል። ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› አልኩት ለቺርስ ብርጭቆ እያነሳሁ። ‹‹ምን ይኖራል? አዲሱ ዓመት ወደ አሮጌነት እየገሰገሰ ነው…›› ብሎኝ በረጅሙ ተነፈሰ። ‹‹ማለት?›› ስለው፣ ‹‹መስከረም አልቆ ጥቅምት ገብቶ ለከርሞ ያድርሰን እያልን የዘመኑን ባለፀጎች እያኖርን ነዋ…›› አለኝ አንገቱን ዘመም አድርጎ ዓይኖቹን አሞጭሙጮ እያየኝ። ‹‹ምን ይሆን?›› አልኩት ቶሎ ብዬ። ‹‹ዘንድሮ መቀስቀሻው ሁሉ ያው ድህነታችን ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በድህነት ስም ተቀስቅሶ ተሠራ ተብሎ የተሻሻለው የጥቂቶች ኑሮ ነው….›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹ዝም ብለህ ስታስበው ሁሉም በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ እከታለሁ ብሎ ሊያሳምነን ይጥራል። በኋላ ቀር ቲዮሪ…›› ብሎኝ ዝም አለ። ቆየት ብሎም፣ ‹‹በአዲስ ሐሳብ፣ በአዲስ ራዕይ፣ በአዲስ ዕይታ አዲስ መንገድ ይናፍቀኝ ጀመር፡፡ አዲሱ ዓመት አሮጌ ሊሆን ሲኳትን እኛ እዚያው ነን…››  ሲለኝ አይ ቅኔ? ‹‹በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን?›› እኛ ደግሞ ‹‹በአሮጌ ቲዮሪ ቅስቀሳ?›› እየተባባልን ከሕይወታችን በስተጀርባ ስላለው ቁም ነገር ብናወጋስ? ተተኪዎች ስለዘነጉት፣ ተኪዎች ደግሞ ማጤን ስላለባቸው ጉዳዮች ብናወሳስ? በጣም ብዙ ብዙ ጉዳዮችን ብናስታውስስ? ቋጥኝ የሚያካክሉ ሸክሞቻችን ብዙ ያነጋግራሉ፡፡ መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት