Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልከሁለት አሠርታት በላይ የዘለቀው ቴአትር

ከሁለት አሠርታት በላይ የዘለቀው ቴአትር

ቀን:

አቶ ዓለማየሁ ግርማ በ40ዎቹ ዕድሜ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ እያሉ ቴአትርን መመልከት እንደጀመሩ ይናገራሉ፡፡ ቴአትርን እንደሱስ መያዛቸውን የሚናገሩት አቶ ዓለማየሁ አሁንም ድረስ በውስጣቸው ሠርፆ እንደሚገኝ ያስረዳሉ፡፡

የወጣትነት ጊዜያቸው ቴአትር በመመልከት ያሳለፉት አፍቃሪ ቴአትር የወደዱትን ተውኔት ደግሞ ደጋግሞ በማየት ዳያሎጉን ጨምሮ እያነበነቡ እንደሚያዩ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ለረዥም ዓመታት ቴአትር የመመልከት አጋጣሚዎች አግኝቻለሁ፡፡ ነገር ግን እንደ ባቢሎን በሳሎን ደጋግሜ ያየሁት ቴአትር ማግኘት አልቻልኩም፤›› ይላሉ፡፡

ቴአትር ቤት አዘውትረው መሄድ የጀመሩት በለጋ ዕድሜያቸው እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ዓለማየሁ፣ የዚያን ጊዜ የባቢሎን በሳሎን ተዋናዮችም ልጅ እግር  እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ1992 ዓ.ም. ‹‹ባቢሎን በሳሎን›› ለመድረክ ሲበቃ ሌሎች ቴአትሮችን በሀገር ፍቅር ቴአትርና በሌሎች ቴአትር ቤቶች ይታዩ እንደነበሩ ያወሱት አቶ ዓለማየሁ በጊዜውም የሌሎች ቴአትር ተመልካቾች ወደ ባቢሎን በሳሎን ቴአትር ማዘንበላቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹እኔ ባቢሎንን ደጋግሜ ብመለከትም አይሰለችም፡፡ ሁልጊዜ አዲስ ይሆንብኛል፡፡ አንዳንዴ በተደጋጋሚ ከማየቴ ብዛት የአንዳንድ ገፀ ባህሪያት ዳያሎጎችን አብሬ እጫወታለሁ፤›› ይላሉ፡፡

በተለይም ተዋናዮቹ ዓለማየሁ ታደሰና ፍቃዱ ከበደ የተሰጣቸው ገፀ ባህሪያኑ ለተመልካች በእጅጉ አስቂኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

‹‹ቴአትሩን ለመጀመርያ ጊዜ ያየሁት መታየት በጀመረበት ዓመት ነው፡፡ መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ከመድረክ ሲወርድ ለ80ኛ ጊዜ ተመልክቼዋለሁ፤›› ሲሉ አቶ ዓለማየሁ በደስታ በተሞላበት ድምፀት ያስረዳሉ፡፡

ቴአትሩ ከመድረክ ይወርዳል ሲባሉ መደንገጣቸውን ያልሸሸጉት ለመጨረሻ ጊዜም ሲታይ የነበረውን ግፊያ ተቋቁመው ማየታቸውን በማስረዳት ነው፡፡

ለረዥም ጊዜያት ሲያዩ እንዳልሰለቻቸው የገለጹት አቶ ዓለማየሁ፣ በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ጓደኞቻቸውንና የትዳር አጋራቸው ጭምር ቴአትሩን ደጋግመው የማየት ልምድ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል፡፡ ከእሳቸው በተጨማሪ በርካታ ተመልካችን በመጋበዝ ደጋግመው እንዲያዩት ምክንያት መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡

እንደ እሳቸው ዕይታ ተመልካቹ ከገፀ ባህሪያቱ መካከል የወደደው ውብሸት ሆኖ (ዓለማየሁ ታደሰ) የሚተውነውን ነው፡፡ ተውኔቱ በማኅበረሰቡ ያለውን ዕውነታ በገሃድ የሚያሳይ አስቂኝና አስተማሪም መሆኑን አስረድቶኛል፡፡

አቶ ዓለማየሁን ጨምሮ ሌሎች ተመልካቾች ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ተውኔቱ አስቂኝና አስተማሪ ገፀ ባህሪያት የተላበሱ ተዋንያን ያሉበት ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ በኑሮ ውድነት፣ በፖለቲካና ማኅበራዊ ቀውስ የተጨናነቀ ተመልካች ቴአትሩን ሲመለከት ነገር ዓለሙን እንዲረሳው ያደርጋል ይላሉ፡፡

‹‹ዓለማየሁ ታደሰ ሲተውን ሳየው ገጸ ባህሪውን ውብሸት እንጂ እሱን አላየውም፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ቴአትሩ ከመድረክ ቢወርድም፣ አሁንም በአንጋፋው ብሔራዊ ቴአትር ቤት ይቀርባል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

ቴአትሩ የተመልካች ችግር እንደሌለበት፣ ከልጅ እስከ አዋቂ ሁሉም ሊያየው የሚፈቅደው ቴአትር ነው ብለዋል፡፡

‹‹ባቢሎን በሳሎን›› ሲገለጽ

‹‹ባቢሎን በሳሎን›› ቴአትር በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ከሁለት አሠርታት በላይ በመታየት ስሙ በቀዳሚነት ሊነሳ የሚችል ቴአትር እንደሆነ ይጠቀስለታል፡፡

የብሔራዊ ቴአትር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በዘርፉ ጥናታቸውን እየሠሩ የሚገኙ አጥኚዎች ጠቅሶ እንደሚገልጸው፣ ባለሙያዎቹ ተውኔቱ  በኢትዮጵያ ቴአትር ውስጥ ረዥም ጊዜ መድረክ ላይ በመቆየት የክብረ ወሰን ባለቤት ነው ይላሉ፡፡

ባቢሎን በሳሎን ቴአትር ውድነህ ክፍሌ ተደርሶ፣ በተስፋዬ ገብረሃናና በሰሎሞን ሙላቴ (ነፍስ ኄር) የተዘጋጀ ነው፡፡ ስለቴአትሩ ጭብጥ የሚገልጸው ጽሑፍ፣ ‹‹ይህ ኮሜዲ ቴአትር በሁለት ባልና ሚስት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት አድጎና ጎልብቶ ጥንዶቹ ሳሎናቸውን ለሁለት ከፍለው ቋንቋቸው ተደባልቆ፣ ‹እልህ ምላጭ ያስውጣል› እንደሚባለው ሆነው እልህ ላይ የቅናት ቤንዚን ተርከፍክፎበት ለሁለት የተከፈለውን የባልና ሚስቶቹን ግድግዳ የሚሻገር ቅናትና እልህ ቤታቸውን ሲያጨሰው ያሳያል፤›› ይላል፡፡

የቴአትሩ ዋና ገጸ ባህሪ ውብሸት (ዓለማየሁ ታደሰ) እና የትዝታ (ሉሌ አሻጋሪ) ትዳር የመለያየት ነፋስ ገብቶበት በእልህና በቅናት የሚንገላታ አሳዛኝ ትዳር ቢሆንም፣ ቤታቸውን ለሁለት ከፍለው የተለያዩት ባልና ሚስቶች በቅናትና በእልህ ምክንያት የሚከውኑት ድርጊታቸው ነው የቴአትሩ ውበት ሆኖ የተመልከቹን የሳቅ ማዕበል የሚያስነሳውና ሳቅ የሚነግሰው፡፡

ቴአትሩ ከመደበኛ ማሳያ ቦታው ከብሔራዊ ቴአትር ባሻገር በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ለተመልካቾች መቅረቡም ይታወቃል፡፡

በብዙኃን ዘንድ ተወዳጅ በሆነው ቴአትር ላይ ከተሳተፉ ተዋናዮች መካከል በሞት የተለዩት ሦስት ከያንያን መሆናቸውን እነሱም ሰሎሞን ሙላት፣ ያረጋል አጥናፉና እድሪስ አህመድ መሆናቸው ቴአትር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጾታል፡፡

‹‹ባቢሎን በሳሎን›› ለምን ከመድረክ ወረደ?

የተውኔቱ ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከቴአትር ቤቱ ጋር የረዥም ዓመታት ውል ነበረ፡፡ ቴአትር ቤቱ የራሱ ሕግና ሥርዓት እንዳለው ያመለከቱት ደራሲው፣ አንዳንዴም የተመልካች ቁጥር አነስተኛ ከሆነ በተለዋጭ ቀን እንዲቀየር እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ረገድ ቴአትሩ በ22 ዓመታት ውስጥ የተመልካች ችግር እንደሌለበት ከዕረፍት ቀናት ባሻገር በአዘቦት ቀናት ተቀይሮለት ሲቀርብ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡

ቴአትሩ በአብዛኛው ጊዜ አዳራሹ በተመልካቾች ተሞልቶ የሚቀርብ መሆኑን፣ አንዳንዴም ቦታ ሞልቶ የሚመለሱ መኖራቸውን  ገልጸዋል፡፡

በቴአትር ቤት ታሪክ በተመልካች እጦት ከመድረክ የወረዱ ብዙ ቴአትሮች መኖራቸውን፣ ባቢሎን ግን በዚህ ችግር የሌለበት መሆኑን፣ እንዲያውም ብሔራዊ ቴአትር ቤት ከፍተኛ ገቢ ያስገኘ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡

የቴአትሩ ከመድረክ መውረድ እንደ ሌሎች በፌስቡክና በመገናኛ ብዙኃን እንደሰሙ ደራሲው አስረድተዋል፡፡ ቴአትሩ ከመቆሙ በፊት በውሉ መሠረት፣ ለደራሲው ደብዳቤ መጻፍ እንደነበረበት፣ ነገር ግን ነገሩ ሁሉ ከሆነ በኋላ መረጃው እንደደረሳቸው ደራሲው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በቴአትር ቤቱ ሌሎች ሥራዎችንም ማቅረባቸውን ያስታወሱት ደራሲው፣ ነገር ግን እንደ ባቢሎን የተመልካች ፍቅር ያገኙ አይደሉም ብለዋል፡፡

ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ‹‹ከባቢሎን በሳሎን›› ቴአትር በተጨማሪ የተለያዩ የሬዲዮ ድራማዎችንና የልብወለድ ሥራዎችን መሥራታቸውን ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ ካቀረቧቸው ነጭ ጥቀርሻ፣ ሞተ ሞት፣ ከዋርካ ሥርና የቼዝ ዓለም የተሰኙ ይገኙባቸዋል፡፡

ከ60 ያላነሱ የሬዲዮ ድራማዎችን ከማዘጋጀት፣ በተጨማሪ በአዘጋጅነትና በጋዜጠኝነት ማገልገላቸውንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

‹‹ባቢሎን በሳሎን›› ለምን ከመድረክ ወረደ? ብለን የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ የቴአትር ዳይሬክተር አቶ ደስታ አስረስ፣ ቴአትሩ የተቋረጠው አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰ ‹‹በቃኝ›› በማለቱ ነው ብለዋል፡፡

አርቲስቱ በግል ምክንያት ቴአትሩን መተወን እንደማይችልና ከአምስትና ስድስት ወራት በፊት ለቴአትር ቤቱ ደብዳቤ ማስገባቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ አርቲስቱን የሚተካ ተተኪ ተዋናይ ለማለማመድ ወይም ለማሠልጠን ፈቃደኛ እንደነበር አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን የ22 ዓመታት ልምድን በተወሰኑ ቀናት ማምጣት እንደማይቻል አቶ ደስታ ገልጸው፣ የቴአትሩ መውረድ ምክንያት የአርቲስት ዓለማየሁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ የቴአትር ቤት ሙያ እንደሌሎች ቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች በግድ መሥራት አለብህ? የሚል አስገዳጅ ነገሮች እንደሌሉት ጠቁመዋል፡፡

የቴአትር ሥራ ወይም ተዋናይነት በፍቅርና በግለሰብ ውዴታ መሠራት ያለበት በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ ባቢሎን በሳሎን ሊቋረጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውጭ ቴአትሩ በብዙዎች የሚወደድና የሚናፈቅ ከመሆኑ በበለጠ ለረዥም ዓመታት ሲታይ የተመልካች እጦት ገጥሞት እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡

ቴአትር ቤቱም ከመድረክ እንዳይወርድ ፍላጎት እንዳለው፣ ነገር ግን ለረዥም ዓመታት በዋና ገፀ ባህሪነት ሲጫወት የቆየው ዓለማየሁ ታደሰ በቃኝ በማለቱ ሊወርድ ችሏል ብለዋል፡፡

ለቴአትሩ መውረድ ምክንያት የሆነው አርቲስት ዓለማየሁ ታደሰን በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡም ተስተውሏል፡፡

 ዓለማየሁ በሙያው  እጅግ የተወደደና ጎበዝ ተዋናይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አይተኬ አይደለም  የሚባለው ትክክል እንዳልሆነና የማይተካ ተዋናይ  እንደሌለ የሚሞግቱ ባለሙያዎች አሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...