የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት ለማስጠበቅ ሲል፣ በትግራይ ክልል የሚገኙ አየር ማረፊያዎችንና በክልሉ የሚገኙ የፈዴራል መንግስት ተቋማትን እንደሚቆጣጠር አስታወቀ።
መንግስት ይህንን እርምጃ ለመውሰድ የተገደደው ፣በህወሓት ኃይል ተደጋጋሚ ጥቃት ብቻ ሳይሆን ይህ ኃይል ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ እንደሆነ የመንግስት ኮሚንኬሼን አገልግሎት በዛሬው ዕለት ያወጣው መግለጫ ያመለክታል።
ይህንን እርምጃ መውሰድ የኢትዮጵያን የአየር ክልል ማስከበርና የአገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት አደጋ ላይ እንዳይወደቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው የሚለው መግለጫው ፣ ለትግራይ ክልል ህዝብ አስፈላጊው የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርስም ጠቃሚ መሆኑን አክሎ ገልጿል።