Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የእንቁላል ዋጋ መወደድ ዋነኛ ምክንያት የመኖ ዋጋ መጨመር መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቅርብ ጊዜ በኋላ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የእንቁላል ዋጋ መናር ዋነኛ ምክንያቱ የመኖ ዋጋ መወደድ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡

ማኅበሩ ይህንን ያስታወቀው 11ኛው የዶሮ ኤክስፖና 7ኛው የእንስሳት ሀብት ዓውደ ርዕይና ጉባዔ፣ ከጥቅምት 17 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚካሄድ ለመግለጽ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንድ እንቁላል ገበያ ውስጥ 13 ብር እየተሸጠ በመሆኑ፣ ሸማቾች ከአቅማቸው በላይ ለመክፈል መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ማኅበሩ ከግብርና ሚኒስትርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው የእንሰሳት መኖ ዋጋ፣ በተለያየ ወቅት በሚከሰት የዶሮ በሽታ ምክንያት የዶሮዎች መሞትና በሽታውን የሚከላከል ክትባት በሚፈለገው መጠን አለመኖር የእንቁላል ዋጋ ንረት ማስከተሉን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ ዓለማየሁ ተናግረዋል፡፡

የእንስሳት መኖን ለማዘጋጀት ከሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች ውስጥ 60 በመቶ በቆሎ፣ 20 በመቶ አኩሪ አተርና የተቀሩት ከዱቄት ፋብሪካ የሚገኙ ተረፈ ምርቶች ናቸው፡፡

‹‹የበቆሎና የአኩሪ አተር ምርት በመቀነሱ ምክንያት የመኖ ግብዓት በኩንታል 700 ብር ይሸጥ የነበረው 3,000 ብር ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ የዶሮ አርቢና አምራች ድርጅቶችን የማምረቻ ዋጋ (Production Cost) 80 በመቶ እንዲጨምሩ ያደርጋቸዋል፡፡ የዶሮ አምራቹ የማምረቻ ዋጋው መቆጣጠር ከሚችለው በላይ ሲሆን ዋጋ ጨምሮ ይሸጣል፤›› ሲሉ አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ከዘይት ፋብሪካዎችና ከዱቄት ፋብሪካዎች የሚለቀቀው ተረፈ ምርት፣ ማለትም እንደ ፋጉሎ ያሉ ግብዓቶች ወደ ውጭ እንዲላክ መፍቀዱ ዋነኛ ለመኖ መወደድ ዋነኛ ምክንያት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

‹‹አገር ደረጃ ያለብን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች መከልከል የለባቸውም፡፡ ነገር ግን ከአገር ውስጥ ገበያ የሚገኙት በቆሎና አኩሪ አተር ምርታቸው እንዲጨምርና የእንሰሳት ክትባቶች በተፈለገው መጠን እንዲገኙ በማድረግ ችግሩን መፍታት ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

በእንስሳትና በዶሮ ሀብት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ በመሆኑ የንግድ ትርዒቶች አዘጋጅ ከሆነው ፕራና ኤቨንትስና መቀመጫውን ሱዳን ካደረገው ‹‹ኤክስፖ ቲም›› ጋር በመሆን፣ የዶሮ ኤክስፖና የእንስሳት ሀብት ዓውደ ርዕይ ለማዘጋጀት ታቅዷል፡፡

የእንስሳት እርባታ አጠቃላይ የእሴት ሰንሰለትን የሚወክሉ ከአሥር የተለያዩ አገሮች የተወጣጡ ከ70 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የዶሮ እርባታና የእንስሳት ንግድ ትርዒት፣ ከጥቅምት 17 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ የፕራና ኤቨንትስ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ገልጸዋል፡፡

በኤግዚቢሽኑ ላይ ከኢትዮጵያ፣ ከጀርመን፣ ከሃንጋሪ፣ ከፈረንሣይ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከህንድ፣ ከኬንያ፣ ከቱርክ፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከስኮትላንድ የተውጣጡ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡

ዝግጅቱ በወተት፣ የዶሮ እርባታና የሥጋ እሴት ሰንሰለቶችን ንግድ በማመቻቸት፣ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር በማድረግ፣ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስተዋወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ስለኤግዚቢሽኑ በነበረው መግለጫ ላይ የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደሚገኙ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

እንደ የዓለም ምግብ ድርጅት ዘገባ የእንስሳት ሀብት በአደጉት አገሮች 40 በመቶ፣ እንዲሁም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ደግሞ 20 በመቶ የሚሆነውን የግብርና ምርት ይሸፍናል፡፡ በዚህም የእንስሳት ሀብት በዓለም ዙሪያ የ1.3 ቢሊዮን ሕዝቦች ኑሮ ይደግፋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የእንስሳት ሀብት ያላት የሆነች አገር ስትሆን፣ በ2014  በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላከው 22,689 ቶን ሥጋና ተረፈ ምርት 121 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ 57 ሚሊየን የሚጠጉ ዶሮዎች የሚገኙ ሲሆን እንቁላል የሚጥሉ፣ ጫጩቶችና ቄብ ዶሮዎች በመባል ይታወቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች