የባለድርሻ አከላት የጋራ ፎረም ለመመሥረት ስምምነት ላይ ደረሱ
የኅብረት ሥራ ማኅበራት ባለፉት አምስት ዓመታት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አስተዋጽኦ ቢያደርጉም፣ የሚያቀርቡት ምርትና ያላቸው የገበያ ድርሻ ከጊዜ ወደ ጊዜ መቀነሱ ተገለጸ፡፡
የማኅበራቱ የቡና የውጭ ግብይት ድርሻ በ2013 ዓ.ም. ከነበረበት 6.74 በመቶ ወደ ሦስት በመቶ የወረደ መሆኑን፣ ከገቢ አንፃር 6.5 በመቶ የነበረው ድርሻቸው ወደ 5.2 በመቶ ዝቅ ማለቱ ታውቋል፡፡
የቡና የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ በ2013 ዓ.ም. 12,082 ቶን ቡና በማቅረብ 65 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተው እንደነበረ፣ በ2014 ዓ.ም. የአቅርቦት መጠናቸው ወደ 11,357 ቶን ዝቅ ማለቱ ተሰምቷል፡፡ ከገቢ አንፃር በዓለም አቀፍ ገበያ ባለው የቡና ዋጋ ማንሰራራት ምክንያት በመጠን የቀነሰው የማኅበራቱ የቡና ምርት፣ 72 ሚሊዮን ዶላር ማስገኘቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የተለያዩ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ ያላቸው ኅብረት ሥራ ማኅበራት 55 እንደሆኑ፣ የቡና ምርት ወደ ውጭ በመላክ ላይ የሚገኙት 45.45 በመቶ መሆናቸውን የአትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የኅብረት ሥራ ማኅበራት የቡና የውጭ ግብይት ድርሻን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የቡና ምርት ልማትና ግብይት ሲምፖዚየም፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሚዛን ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡
ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የምርት መጠን መቀነስና መቆራረጥ ምክንያትን ለመለየት 25 በሚደርሱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ በኮሚሽኑ የዳሰሳ ጥናት የተካሄደ ሲሆን፣ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ማኅበራቱ መሰብሰብ ከሚችሉት ምርት መካከል 65 በመቶ ብቻ እንደሚሰበስቡና ለዚህም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በቂ ፋይናንስ አለማግኘት፣ አስተማማኝ የገበያ መዳረሻ ችግርና የዋጋ መዋዠቅ ተጠቃሾቹ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ ባሻገር የውጭ ግብይት ሒደት ረዥምና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ፣ የገበያ መዳረሻ አለመስፋትና የመጨረሻ ገዥዎችን አለማግኘት፣ ለተቀነባበረ ቡና የውጭ ገበያ አለማግኘት፣ ከመንግሥታዊ መዋቅር የሚደረግ ድጋፍ ችግር ፈቺ አለመሆን፣ እንዲሁም ተግባሩን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት አለመኖርና ሌሎችም በኅብረት ሥራ ማኅበራት ቡና ልማትና ገበያ ያሉ ተግዳሮች መሆናቸው በመድረኩ ላይ ቀርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ እንዳስታወቁት፣ አገሪቱ በቡና ምርት የውጭ ንግድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ገቢ እያገኘች ነው፡፡ ነገር ግን የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ በዚያው ልክ እያደገ አልመጣም ብለዋል፡፡ ከአምስት ዓመታት አስቀድሞ በቡና የውጭ ንግድ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ 12 በመቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አብዲ፣ በተጠናቀቀው ዓመት መጨረሻ ይህ ወደ አሥር ዝቅ ማለቱን ተናግረዋል፡፡
ሲምፖዚየሙ ሲዘጋጅ ዋነኛ ምክንያቶች የነበሩት የኅብረት ሥራ ማኅበራት ለምን ድርሻቸው ዝቅ አለ? ዋናዎቹ ማነቆዎች ምንድን ናቸው? ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን የፖሊሲ፣ የአሠራር፣ የአደረጃጀት፣ የገበያ፣ የፋይናንስና የአባላት ተጠቃሚነትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ነቅሶ በማውጣት ማኅበራቱ በራሳቸው ያሉባቸው ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ሌሎች አካላትስ የሚፈቷቸው ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚሉት ላይ መክሮ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ለምርትና ግብይት የሚያስፈልግ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ማድረግ፣ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የምርት መዳረሻቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍና ክትትል ማድረግ፣ እንዲሁም ሌሎችም በኅብረት ሥራ ማኅበራት የቡና ልማትና ግብይት ላይ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት የሚጠበቁ ተግባራት መሆናቸው ተብራርቷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተሳፉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴርና ቡና ወደ ውጭ የሚልኩ ማኅበራት የጋራ ፎረም በመመሥረት ችግሩን ወደ ዕቅድ በመቀየር ለይቶ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
በሚዛን አማን ከተማ በተከናወነው ሲምፖዚየም የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ከማድረጋቸው ጎን ለጎን፣ በተዘጋጀው የቡና ዓውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ የቡና ምርቶች፣ ቅመማ ቅመምና የማር ምርቶች አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ 101,834 መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሲኖሩ፣ 343 ያህሉ በቡና ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ 395 የኅብረት ሥራ ዩኒየኖች በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተቋቋሙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት በቡና ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ከአምስት የኅብረት ሥራ ፌዴሬሽኖች ደግሞ ሁለቱ የቡና ናቸው፡፡