Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከጂቡቲ የሚገቡ አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ከቀየሩ  ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጋላፊ ኬላ መንገድ በመበላሸቱ አሽከርካሪዎች ደዋሌን ይመርጣሉ

ከጂቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አገር አቋራጭ አሽከርካሪዎች በጋላፊ መቆጣጠሪያ ጣቢያ እንዲጠቀሙ ከተመደቡ በኋላ፣ በደዋሌ በኩል የሚጠቀሙ ከሆነ ከሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. በኋላ በቅጣት እንደሚስተናገዱ፣ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ የደዋሌ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ አስታወቀ፡፡

አሽከርካሪዎቹ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋላፊ በኩል እንዲያልፉ ሰነድ ከተሠራላቸው በኋላ፣ በደዋሌ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በኩል እንዲያልፉ ቢፈቀድም፣ ከዚህ ማሳሰቢያ በኋላ ‹‹አይቻልም›› ተብለዋል፡፡ በጋላፊ በኩል ሲገቡ ሊገጥማቸው የሚችለውን የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት በማድረግ፣ እንዲሁም በመስመሩ ላይ ያለ ድልድይና የተወሰነ መንገድ በጎርፉ በመጎዳቱ ምክንያት ደዋሌን እንዲጠቀሙ ይፈቀድላቸው እንደነበር ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአገር አቋራጭ አሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበር አባላት ተናግረዋል፡፡

በጎርፉ ተበላሽቶ የነበረው ድልድይና መንገድ ቢሠራም፣ በተጨማሪ በጋላፊ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በኩል ያለው መንገድ በጂቡቲ ክልል ውስጥ እስከ 200 ሜትር ድረስ መንገዱ በመበላሸቱ፣ ተሽከርካሪዎቹን ለአደጋ አጋላጭ በመሆኑና የጉዞ ቀን በማራዘሙ፣ አሽከርካሪዎች መንገዱን አይመርጡትም፡፡ የዩኒክ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ኃይሌ በላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተበላሸው መንገድ የተሽከርካሪዎች ጎማና የተለያዩ መለዋወጫዎችን በከፊል የሚጎዳና የጉዞ ቀንንም የሚያራዝም በመሆኑ አሽከርካሪዎች አይመርጡትም፡፡  

አሠራሩ ከመላላቱ በፊት ግን አሽከርካሪዎች መቆጣጠሪያ ጣቢያ ተሳስተው ባልተመደቡበት በኩል ለማለፍ ሲመጡ እንዲመለሱ ይደረግ እንደነበር አቶ ኃይሌ ገልጸው፣ የተበላሸው መንገድ ለረዥም ጊዜም እንዲሠራ ይጠየቅ እንደነበር አውስተዋል፡፡ ‹‹ከ200 ኪሎ ሜትር በተለይ 80 ኪሎ ሜትሩ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ለመንግሥት አካላት፣ የተወካዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በብዙ መድረኮች ጉዳዩ ተነስቶ ነበር፤›› ሲሉ አቶ ኃይሌ አስረድተዋል፡፡

በጉምሩክ ሥርዓት ኮንትሮባንድ ለመቆጣጠር እንዲያመችና አሽከርካሪዎች  የተመደቡበትን መቆጣጠሪያ ጣቢያ ብቻ እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ ሕግ በመኖሩ የቅጣቱን ትክክለኛነት ቢያምኑም፣ መንገዱን በመሥራት መፍትሔ ማምጣት  ለአገሪቱም የሎጂስቲክስ ቅልጥፍና እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ሦስት ቀናት ቢፈጅም፣ በዚህ መንገድ ግን አራትና አምስት ቀናት ይወስዳል፤›› ብለዋል፡፡

በጂቡቲ ውስጥ ያለው መንገድ ባለመታደሱ ወይም ተለዋጭ መንገድ ባለመኖሩ የጋላፊ መንገድ አመቺና ቀጥ ያለ ቢሆንም፣ ተመራጭነት እንዳለው የሚገልጹት ደግሞ፣ የእኛ ህልም አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅና የትራንስፖርት አሠሪዎች ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ሉጬ ናቸው፡፡

ተሽከርካሪዎች በጋላፊ መስመር ሲሄዱ የተበላሸው መንገድ በጉድጓዶቹ ብዛት በተለይ የጭነት መጠናቸው ከ300 ኩንታል በታች ያሉትንና የባለ ነጠላ አክስሎችን (Axel) እስከ መገልበጥ እንደሚደርስባቸው፣ ሲገለበጡም ከንብረቶቹ መበላሸት ባሻገር ከፍተኛ የሆነ የማንሻ ወጪ በጂቡቲ በኩል እንዳለባቸው በመግለጽ፣ እስከሚስተካከል ድረስ መንግሥት መታገስ እንዳልቻለ አቶ ደጀኔ ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም በድሬዳዋ-ደዋሌ መስመር መንገዱ ቀጥ ያለ ባለመሆኑ ለተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርግ የተናገሩት አቶ ደጀኔ፣ ተሽከርካሪዎቹ ወደው ሳይሆን ከመለዋወጫና መሰል ወጪዎች ለመዳን እንጂ በሌላ ምክንያት የጋላፊን መንገድ እንደማይሸሹ ይገልጻሉ፡፡

‹‹በደዋሌ መሄድ አዋጭ ሆኖ ሳይሆን መኪና ከሚገለበጥና ትልቅ ኪሳራ ከሚያስከትል ነው፤›› በማለት የድሬዳዋ ደዋሌን መንገድ የሚመርጡበትን ምክንያት ያስረዳሉ፡፡ አቶ ደጀኔ አክለውም፣ ‹‹ጉምሩክ ኮሚሽን ተሽከርካሪዎቹ በየትኛውም ቢሄዱ አገሪቱ ውስጥ ገብተው እስከተፈተሹ ድረስ ለምን ይህን ጉዳይ አክርሮ ማየት እንዳስፈለገው አልገባንም፤›› ብለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አዘዘው ጫኔ፣ ተሽከርካሪዎቹ በየትኛውም መቆጣጠሪያ ቢገቡም መዳረሻቸው ኢትዮጵያ እስከሆነ ድረስና የጉምሩክ ሥርዓት እስከፈጸሙ ድረስ በአሠራሩ ላይ ችግር እየተፈጠረ እንዳልሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ አክለውም በአንድ ወቅት የጋላፊ መንገድን ጎርፍ ሰብሮት እንደነበር፣ ያን ጊዜ መኪኖች በደዋሌ እንደገቡና የተፈጠረ ችግር የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለእኛ የቀረበ መረጃም ሆነ ሪፖርት የለም፡፡ እንደ ዋና መሥሪያ ቤት አንዳንድ ጊዜ የፀጥታ ችግር፣ የመንገድ መበላሸትና ተሽከርካሪ ተገልብጦ የመንገድ መዘጋት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ይህ የትራንዚት ቁጥጥር ቦታውን በመቀየር ሊካሄድ ይችላል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች