Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመንግሥት ጋር አጋርነት የሚገቡ ኩባንያዎች የአምስት ዓመታት ሪከርዳቸው ከሕግ ተጠያቂነት የፀዳ እንዲሆን ሊገደዱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥትና በግል አጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን በቀጥታ ድርድር በሚያገኙ  ኩባንያዎች ውስጥ ከአምስት በመቶ በላይ ድርሻ ያላቸው ባለአክሲዮኖችና አመራሮች የአምስት ዓመት ሪከርድ፣ ከሕግ ከወንጀል ተጠያቂነት የፀዳ መሆን እንዳለበት የሚደነግግ ረቂቅ አዋጅ ቀረበ፡፡

በድርድር ፕሮጀክት የሚሰጣቸው ኩባንያዎች ከተቀመጡላቸው ዝቅተኛ መሥፈርቶች መካከል ሌላው፣ ኩባንያዎቹ ለሚሰጣቸው የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ጠቅላላ ወጪ ውስጥ በብድር የሚቀርበውን የሚመለከት ነው፡፡ ለፓርላማ በቀረበው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ፣ ኩባንያዎቹ ለፕሮጀክት ከሚያስፈልጋቸው ወጪ ውስጥ በብድር የሚሸፈነውን የገንዘብ መጠን ከአበዳሪ ስለማግኘታቸው አስቀድመው የብድር ፈቃድ የማቅረብ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት የወጣውን የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅ ለማሻሻል የተዘጋጀው ረቂቅ የማሻሻያ አዋጅ ማክሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ሁለተኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ስብሰባውን ላደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ፣ ወደ ዕቅድ በጀትና ፋይናስን ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር በአቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ  የቀረበው የአዋጁ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ በ2011 ዓ.ም. በፀደቀው አዋጅ መሠረት ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች ኩባንያዎችን ለመምረጥ የሚሄድበት የጨረታ አሠራር ‹‹ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድ›› ነው፡፡ ይህ ደግሞ መንግሥት ሊተገብር ያሰበውን ‹‹የሪፎርም ሥራ›› ፈጥኖ ለመተግበር እንዳላስቻለ በማብራሪያው ላይ ቀርቧል፡፡

ማሻሻያ በቀረበበት በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ላይ ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች ኩባንያዎች በቀጥተኛ ድርድር የሚመረጡበት ሁኔታ እንዳለ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በቀድሞው አዋጅ ላይ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችና በዚሁ አሠራር እንዲተገበሩ ለገንዘብ ሚኒስቴር እየቀረቡለት ያሉ ፕሮጀክቶች የሚጣጣሙ እንዳልሆኑ ማብራሪያው ያስረዳል፡፡

አሁን በአዋጁ ማሻሻያ ላይ የቀረበው አሠራር በመንግሥት ውሳኔ መሠረት ‹‹በሁለትዮሽ የመንግሥት ለመንግሥት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ አማካይነት ወይም ከግል ባለሀብት ጋር በሚደረግ ቀጥተኛ ግንኙነት››፣ ፕሮጀክቶች ለኩባንዎች እንዲሰጡ የሚፈቅድ ነው፡፡

በገንዘብ ሚኒስቴር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ በድርድር ከመንግሥት ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን የሚያገናኙ ኩባንዎች እንዲኖራቸው ከዘረዘረው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ፣ የሕግ ተጠያቂነት ሪከርድ ጉዳይ ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ በፕሮጀክቱ ውስጥ የሚሳተፈው ኩባንያ ፕሮጀክቱን እንዲያገኝ ከመወሰኑ በፊት፣ ወደኋላ ባሉት አምስት ዓመታት ኩባንያው ያለው ሪከርድ ከተጠያቂነት የፀዳ መሆን እንዳለበት በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡

ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ እንደሚያስረዳው ይህ ቅድመ ሁኔታ የተጣለው ኩባንያው ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ፣ ዳይሬክተሮችና በኩባንያው ውስጥ ከአምስት በመቶ በላይ አክሲዮን ባላቸው ባለድርሻዎች ላይ ጭምር ነው፡፡

ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ለሚተገበር ፕሮጀክት ቀጥተኛ ድርድር ውስጥ የሚገባ ኩባንያ፣ ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ያለው መሆኑን በማስረጃ አስደግፎ ማረጋገጥ ይጠበቅበታል፡፡ ከሚያስፈልገው ጠቅላላ ወጪ ውስጥ በብድር የሚሸፈነውን ወጪ በተመለከተም ረቂቁ፣ ‹‹በብድር ለሚሸፈነው የገንዘብ መጠን ከአበዳሪው ወይም አበዳሪዎች የተሰጠ የብድር ፈቃድ ማረጋገጫ ማቅረብ ይኖርበታል፤›› ሲል ደንግጓል፡፡

ኩባንያው ከተቋቋመበት አገር የሚሰጠውን ፕሮጀክት እንዲያለማ ‹‹ልዩ ድጋፍ›› ማቅረብ፣ ፕሮጀክቱ ባለበት ዘርፍ ሦስትና ከሦስት በላይ ፕሮጀክቶችን በማልማት ልምድ ያለው መሆን ለኩባንያዎች የተቀመጡ ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከግል ኩባንያ ጋር በአጋርነት የሚከናወን ፕሮጀክት በቀጥተኛ ድርድር እንዲመረጥ ሲያቀርቡ፣ ‹‹የፕሮጀክቱ ሐሳብ ያለው ልዩ ጠቀሜታ›› በባለ ፕሮጀክቱ መሥሪያ ቤትና በገንዘብ ሚኒስቴር አስቀድሞ እንደሚገመገም ረቂቅ አዋጁ አስቀምጧል፡፡ አንድ ፕሮጀክት በቀጥታ ድርድር በሚመረጥ ኩባንያና በመንግሥት አጋርነት እንዲተገበር የሚመረጠው፣ ‹‹የፕሮጀክት ሐሳቡ ቢተገበር ፕሮጀክቱ በፍጥነት ፋይናንስ እንዲያገኝ በማስቻል የሕዝብ አገልግሎት ጥቅም እንደሚያስገኝ ሲታመንበት›› መሆኑን ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል፡፡

መንግሥት በ2011 ዓ.ም. የመንግሥትና የግል አጋርነት (Public Private Partnership) አዋጅን ካፀደቀ በኋላ ከፀሐይና ከውኃ ኃይል ማመንጫ፣ እንዲሁም የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶችን ለማልማት በመጀመሪያ ዙር 17 ፕሮጀክቶችን ቢያቀርብም እስካሁን ተግባራዊ አልሆኑም፡፡

በመንግሥትና የግል አጋርነት የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን ለመምራት የተቋቋመው ቦርድ በ2012 ዓ.ም. በአፋርና ሶማሌ ክልሎች የሚለሙ ጋድና ዴቼቶ የተሰኙ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች፣ ለሳዑዲ ኤሲደብሊውኤ ፓወር ኩባንያ (ACWA Power) ሰጥቶ ነበር፡፡ ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡

ይሁንና ኩባንያው ፕሮጀክቱን ለመተግበር በመዘግየቱ ምክንያት ቦርዱ ባለፈው ዓመት ሰኔ 2014 ዓ.ም. ስምምነቱን መሰረዙ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች