Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚወስዱትን ብድር መክፈል ካቃታቸው፣ አዲስ በተቋቋመው የፋይናንስ ማእከል በኩል ለአበዳሪዎች ዋስትና እንደሚሰጥ አስታወቀ፡፡ ብሔራዊ ባንክ ዋስትና (Credit Guarantee Scheme) መስጠት ለመጀመር ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም አበዳሪዎች ያለማስያዣና ያለሥጋት ብድሩን እንዲያቀርቡ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡

የማደግ ተስፋ ላላቸው የማይክሮ፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የብድር አገልግሎት የሚያቀርብ፣ አዲስ ፋይናንስ ማዕከል (Innovative Finance Lab) የተሰኘ ማዕከል ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ በይፋ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ትብብር የተቋቋመ ሲሆን፣ አሥራ ሰባት የቦርድ አባላት አሉት፡፡

ማዕከሉ ለብድር የሚያቀርበውን ገንዘብ ከሦስት ዋና ዋና ምንጮች የሚያገኝ ሲሆን እነዚህም ከውጭ ምንጮች፣ ከመንግሥት ድጋፍና ከአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት ናቸው፡፡

‹‹የማይክሮ፣ አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መያዣ (Collateral) ማቅረብ ስለማይችሉ ባንኮች ብድር ለማቅረብ ይፈራሉ፡፡ ባንኮች ያለ መያዣ ስለማያበድሩ ኢንተርፕራይዞቹ ፋይናንስ ማግኘት አዳጋች ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ብሔራዊ ባንክ ለኢንተርፕራይዞቹ ለሚቀርቡ ብድሮች ዋስትና ከአሁን ጀምሮ በማእከሉ በኩል እንሰጣለን፡፡ ይህ ማለት ማዕከሉ ለሚያቀርባቸው ብድሮች ኢንተርፕራይዞቹ መክፈል ቢያቅታቸው ብሔራዊ ባንክ በራሱ የተበላሸውን ብድር ይሸፍናል ማለት ነው፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን ደስታ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና አዲስ የተቋቋመው ማዕከል አንደኛው የቦርድ ሰብሳቢ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የተመድ የልማት ፕሮግራም የሕግ ገደብ ሳያግደው አዳዲስ የውጪ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ በማይክሮ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ የሙከራ ትግበራ (Pilot) ማድረግ እንዲችል ከብሔራዊ ባንክ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ምክትል ገዥው ገልጸዋል፡፡

‹‹ከዚህ በፊት ሕግ በብሔራዊ ባንክ እስኪወጣለት አንድን የፋይናንስ አገልግሎት ከውጪ ኮፒ አድርጎ እዚህ መተግበር አይፈቅድም ነበር፡፡ አሁን ግን ማዕከሉ የሙከራ ትግበራ በማንኛውም የፋይናንስ አገልግሎት ላይ እንዲያደርግ ፈቅደናል፡፡ ጎን ለጎን ብሔራዊ ባንክ ሕግ ያወጣለታል ማለት ነው፤›› ሲሉ አቶ ሰለሞን አስረድተዋል፡፡

ይህ ፈቃድ በተለይ ከውጪ ካፒታል ይዘው መጥተው በአዳጊ ኢንተርፕራይዞች ላይ ማፍሰስ (Venture Capital And angel Investors) ለሚፈልጉት በር ከፋች ነው ተብሏል፡፡

‹‹አብዛኛው የማይክሮ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሳያድጉ በእንጭጭ የሚቀሩበት ዋነኛ ምክንያት የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ነው፡፡ ገንዘብ (Capital) ሞልቶ እያለ ኢንተርፕራይዞቹ ግን እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ባለማወቅ ወደኋላ ቀርተዋል፤›› ሲሉ አቶ ግዛቸው ሲሳይ በተመድ የልማት ፕሮግራም የቡድን መሪ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ 2.29 ሚሊዮን ማይክሮ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 29 ከመቶ በአማራ ክልል፣ 28 ከመቶ በአዲስ አበባና 21 ከመቶ በኦሮሚያ ይገኛሉ፡፡

በ2013 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ባንኮች 329 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ብድር ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ግን ለማይክሮ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የቀረበው ብድር 1.52 ከመቶውን ብቻ ይይዛል፡፡ ይህም መጠን በ2011 ዓ.ም. ከነበረው 3.1 ከመቶ በግማሽ ያነሰ ሲሆን ኢንተርፕራይዞች ከባንኮችና ማይክሮ ፋይናንስ የሚያገኙት ብድር እየቀነሰ መምጣቱን አመላካች ነው፡፡

ምንም እንኳን እነዚህ 2.29 ሚሊዮን ኢንተርፕራይዞች በባንኮች ውስጥ ያላቸው ተቀማጭ ጠንካራ ቢሆንም ከባንኮቹ ግን ብድር ማግኘት እንዳልቻሉ ተገልጿል፡፡

ምንም እንኳን ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባንኮች ከሚሰጡት ጠቅላላ ዓመታዊ ብድር ውስጥ አምስት ከመቶውን ለማይክሮ፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ደግሞ ለእነዚህ ኢንተርፕራይዞች ብድር በማቅረብ የሚታወቁት የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና ኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ፀደይ፣ ሲንቄ፣  ሸበሌና ሲዳማ ባንክ መለወጣቸው ትልቅ ክፍተት ስለሚፈጥር አማራጭ የብድር አቅርቦቶችን ማማተር የግድ ማለቱ ተገልጿል፡፡

‹‹የተንቀሳቃሽ ንብረት አስይዞ መበደርም በቅርቡ ስለሚጀመር ችግሩን ይቀርፋል ብለን እንጠብቃለን፤›› ብለዋል ምክትል ገዥው፡፡

በሌላ በኩል ግን ለረዥም ጊዜ ራሱን የቻለ የጥቃቅንና አነስተኛ ባንክ ለመመሥረት ጥረቶች እየተደረጉ የነበረ ቢሆንም እስካሁን በዘርፉ የባንክ ፈቃድ ጥያቄ አለመቅረቡን አቶ ሰለሞን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች