Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮርፖሬሽኑ ፎረም በማዘጋጀት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ለመሳብ መዘጋጀቱን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመጪው ጥር ወር ላይ ‹‹ኢንቨስት ኦሪጂንስ›› በማለት የመጀመሪያውን የኢንቨስትመንት ፎረም ለማድረግ ያቀደው፣ የፌደራል መሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን፣ በፎረሙ ላይ ለሚካፈሉ ባለሀብቶች በሚያዘጋጃቸው መሬቶች ላይ፣ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሊያወጣ የሚችል ኢንቨስትመንት ማቀዱን ገለጸ፡፡ ፎረሙን በየዓመቱ በማካሄድ ተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ገቢ ለማግኘትም አቅዷል፡፡

በፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይዞታ ሥር ያሉትን ያልለሙ መሬቶች በመመዝገብና ለልማት በማዘጋጀት፣ ከልማት ድርጅቶችና ከግል ባሀብቶች ጋር በሽርክና የተለያዩ የልማት ሥራዎችን በማቀድ የመጀመርያውን የኢንቨስትመንት ፎረም በመጪው ጥር 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ለማድረግ ማቀዱን ትናንት ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡

በዚህም ከሦስት ያላነሱ ውሎችን ለመግባትና ከሁለት ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ማቀዱን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሌንሳ መኰንን ገልጸዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ማክሰኞ ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ድርጅቱ የተለያዩ ኢንቨስተሮችንና አልሚ ድርጅቶችን በማሰባሰብ በሰጠው መግለጫ፣ በቀጣይ አራት ዓመታት ከተማ ነክ ባሉ ቦታዎች በአምስት የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ላይ፣   ከኢንቨስተሮችና ከአልሚዎች ጋር አብሮ ለማሰማራት አቅዷል፡፡ እነሱም በቤቶች፣ በጤና ዘርፍ፣ ትምህርት ዘርፍ፣ በሆቴሎችና በመረጃ ቴክኖሎጂ ላይ ሲሆን፣ በቤቶች ዘርፍ ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ዋነኛው እንደሆነ ወ/ሮ ሌንሳ ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት አቅዶበት ሊያካሂድ ያሰበውን ይህን ፎረም በመጠቀም በቀጣይ አምስት ዓመታት ከፍተኛ የቤቶች አልሚ ተቋም የመሆን ዕቅድ ኮርፖሬሽኑ የያዘ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ በሁለቱ የፎረም ቀናቶች ውስጥ በትንሹ ሦስት ኮንትራት ውሎችን መፈረምና ከአምስት ያላነሱ  የሥራ ማስጀመሪያ መግባቢያ ሰነዶችን ለመፈራረም አቅዷል፡፡

በአጠቃላይ በአገር ደረጃ 4.7 ሚሊዮን ሔክታር መሬቶችን የለየና የሰበሰበው ኮርፖሬሽኑ፣ ለጊዜው ዋነኛ ሥራው አድርጎ የተነሳው በአዲስ አበባ ባሉ ያልለሙ መሬቶችን ማልማት ሲሆን ለዚህም በከተማዋ 3,700 ሔክታር መሬቶችን በመለየት እንዳዘጋጀ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከዚህ ውስጥ ምን ያህሉን ለኢንቨስትመንት  እናቀርባለን የሚለውን ጥናት እያጠናን ሲሆን፣ በተዘጋጀንበት ዘርፎች ላይ ምን ያህል ለእያንዳንዳቸው እንደምናዘጋጅም በቅርቡ ይፋ እናደርጋለን፤›› ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሁን ቅድሚያ የሚሰጥበት ልማት ያልተካሄደባቸውን የመንግሥት ድርጅቶች ይዞታዎች ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጠበትን ቃሊቲ የሚገኘውን የውኃ ልማት ጊቢን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ እንደ አዲስ ለማልማት የሚችል ቦታ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ለምተው ያሉ ይዞታዎችን መልሶ የማልማትና የማደስ ሥራም እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡ ፎረሙ ለማካሄድ በአብሮነት ለመሥራት ኮርፖሬሽኑ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ አቪድ ኮንስትራክሽንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር አጋርነት መፈጠሩን በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች