ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሴቶች በትምህርት ፕሮግራም ላይ የመሳተፍና በሥራ ዕድል ተቋዳሽ የመሆን ፍላጎታቸው አነስተኛ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ይህም የሆነበት አንዱ ምክንያት ልጆቻቸውን እየተንከባከበ የሚያቆይላቸው አካል ማጣታቸው ነው፡፡
ከዚህ ዓይነቱ ችግር ለመላቀቅ መፍትሔ የሕፃናት የቀን ማቆያ ማዕከልን ማስፋፋትና ማሳደግ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በዚህም የተነሳ ‹‹ፓርትነርሺፕ ቼንጅ›› ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት አዲስ ለተወለዱና ዕድሜያቸው እስከ አራት ዓመት ለሆኑ ሕፃናት አገልግሎት የሚውል የቀን ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከልን ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ ቀርፆ ተግባራዊ ለማድረግ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ጋር እየሠራ ይገኛል፡፡
መቀመጫው ኖርዌይ የሆነው ዓለም አቀፉ ተቋም የሕፃናት የቀን ማቆያና መንከባከቢያ እንዲሁም የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ማዕከል ለማቋቋም የመግባቢያ ሰነድን ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የተፈራረመው ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ የሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ነው፡፡
የሚቋቋመው የቀዳማይ ልጅነት ማዕከል ዕድሜያቸው እስከ ሰባት ዓመት በሚሆናቸው ሕፃናት ላይ ያተኮሩ ሕፃናቱን በአግባቡ ለማነፅ ይረዳል ተብሏል፡፡
‹‹ልጅነቴ መሠረቴ ብሩህ ተስፋዬ›› የሚል ዕይታን የሚያንፀባርቀው ማዕከሉ ለመልካም ሰብዕናና ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሕፃናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከል መስፋፋት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከጠቀሜታዎቹም መካከል ሕፃናቱ ለወደፊቱ ዕድገታቸው የሚረዳቸውን የትምህርት ፕሮግራም በመጀመርያው የሕይወት ዘመናቸው ላይ ለመረዳት የሚያስችላቸው መሆኑ ነው፡፡
ከዚህም ሌላ ሴቶች በምድብ ሥራዎቻቸው ላይ ከወንዶች እኩል የሚሳተፉበትን ሁኔታ በማመቻቸት ረገድ፣ ለሴቶቹ አዲስ የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግና ከገንዘብ ጥገኝነት የሚላቀቁበትን አካሄድ በመቀየስ ረገድ ማዕከል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ መዘንጋት እንደሌለበት ነው የተገለጸው፡፡
መንግሥታዊ ተቋማቱ ከዓለም አቀፉ ድርጅት ጋር የመግባቢያ ሰነዱን በተፈራረሙበት ጊዜ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ዓለሚቱ አሙድ ባደረጉት ንግግር የሕፃናት የቀን ማቆያ ማዕከል መቋቋሙ ለሴቶች ምቹ ሁኔታን፣ ለሕፃናቱ ደግሞ ጥሩ እንክብካቤ ለማድረግ የሚያስችል መደላድሎችን ይፈጥራል ብለዋል፡፡
በአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ ውስጥ የሕፃናትን የቀን ማቆያ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የቀዳማይ ልጅነት የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የአዲስ አበባ ከተማ የሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተሳተፈበትና ዓምና በተደረገው የነባራዊ ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት እንደተጠቀሰው፣ በከተማዋ ከሚኖረው 6.8 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ ከ25 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ከጽንሰት ጀምሮ በቂ ምግብ አለማግኘት አካላዊና አዕምሮአዊ ዕድገት ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ በመሆናቸው የነገውን ትውልድ ለመገንባት መሠረታቸውን መሥራት ተገቢ ነው፡፡
ሕፃናት በተለይም ከ0-3 ዓመት ያለው ዕድሜያቸው ላይ አዕምሮአቸው የማደግ አቅሙ 80 በመቶ የሚደርስ በመሆኑ በዚህ የዕድሜ ክልል ላይ የሚሠራው ሥራ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡
ቢሮው ወቅቱ እ.ኤ.አ. በ2026 ከ330 ሺሕ በላይ እናቶች ሁሉን አቀፍ ተደራሽ የሆነ የቀዳማይ ልጅነት ዕድገት አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሠራ እንደሆነም መግለጹ ይታወሳል፡፡