Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  የትውልድ መሠረትን የማነፅ ትልም

  በኢትዮጵያ በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍጠር ወላጆች፣ ትምህርት ቤቶችና በየአካባቢው የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወጡ ይታመናል፡፡ ልጆችም ሆኑ ወጣቶች በመልካም ሰብዕና አገር እንዲረከቡ መንግሥት እየሠራሁ ነው ቢልም፣ ክፍተቱ ግን አሁንም ቢሆን ሊፈታ አልቻለም፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ችግር ታሳቢ በማድረግ የአልታ ምርምርና ሥልጠና ካውንስሊንግ ወጥ የሆነ አሠራር ዘርግቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ አቶ ወንድወሰን ተሾመ የአልታ ካውንስሊንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የተቋሙን ሥራ አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- የአልታ ምርምርና ሥልጠና ካውንስሊንግ እንዴት ተመሠረተ?

  አቶ ወንድወሰን፡- አልታ ካውንስሊንግ ከተመሠረተ ዘጠኝ ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ድርጅቱም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ‹‹የትውልድ መሠረት ቤተሰብ›› በሚል መርሕ መጥቶ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ በተለይም ሕፃናት፣ ልጆችና ወጣቶች በመልካም ሥነ ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ሥልጠዎችን ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸውን በምን ዓይነት ሁኔታ አሳድገው ለቁምነገር የሚያበቋቸው የሚለውን እንዲያውቁ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ልጆችም የወደፊት ሕይወታቸውን የተሻለ እንዲሆን፣ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህን ሁሉ አሠራሮች መተግበር ከተቻለ ቤተሰብ ከመገንባት ባለፈ አገርን መገንባት ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡ በ2014 ዓ.ም. ክረምት ላይ ለ114 ልጆች የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 56 ልጆች በነፃ ሥልጠናውን እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ ወላጆቻቸው ከፍለውላቸው ሥልጠናውን ሊያገኙ ችለዋል፡፡ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ሲባል አብዛኛውን ሰዎች ግር ሊላቸው ይችላል፡፡ ማንኛውም ሰው በየቀኑ የሚገጥመውን ተግዳሮት ሆነ መልካም ነገር እንዴት መጠቀምና ችግሩን እንዴት መፍታት እንዳለበት የሚያውቅበት የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተቋሙ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥልጠናውም በየወሩ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ሥልጠናውም ከወላጆች ጋር በመነጋገር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡   

  ሪፖርተር፡- ልጆችም ሆኑ ወጣቶች የሕይወት ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ከወላጆች ጋር በምን መልኩ እየሠራችሁ ነው?

  አቶ ወንድወሰን፡- ከሁሉም በላይ ለዚህ ሥራ ወላጆች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይታመናል፡፡ በተለይም ከአንድ እስከ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ልጆች ከሥልጠናው ባለፈ ወላጆቻቸው በቂ የሆነ የሕይወት ክህሎት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ ተቋሙም ከወላጆች ጋር ቁርኝት በመፍጠር ልጆቻቸው የተለያዩ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል፡፡ ትውልድን በመቅረፅ ሒደት ውስጥ ወላጆች ከፍተኛ ሚና ስለሚጫወቱ እስካሁን ከወላጆች ጋር በቅርበት በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ወላጆችም በስልክ፣ በቴሌግራም ቻናል ሆነ ቢሮ ድረስ በመምጣት ልጆቻቸው ሥልጠናውን እንዲያገኙ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ተቋሙም ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ጋር ስለሚሠራ፣ ከወላጆች ጋር በቅርበት እየተነጋገረ ሥልጠናውን እየሰጠ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለወላጆች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሥልጠናውም ልጆቻቸውን በምን ዓይነት ሁኔታ ማሳደግ እንዳለባቸው የሚረዱበት ይሆናል፡፡ ሥልጠናውም ለአራት ሳምንታት ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ በእነዚህ ሳምንት ውስጥ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በምን ዓይነት ሁኔታ ተግባቦት መፍጠር እንዳለባቸው የሚረዱበት ሥልጠና ይሆናል፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ለሁለት ሰዓታት ያህል ሥልጠናውን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ሥልጠናውንም ከወሰዱ በኋላ ሳምንቱን ሙሉ የሚሠሩትን ሥራ ለእያንዳንዱ ወላጅ የቤት ሥራ የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ያጋጠሟቸውን ችግሮች በጋራ ይፈታል፡፡   

  ሪፖርተር፡- ተቋሙ ከተመሠረተ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ምን ዓይነት ተግዳሮት ገጥሟችኋል?

  አቶ ወንድወሰን፡- በሥራችን ላይ ይህን ያህል የሚባል ችግር አልገጠመንም ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ትልቅ ችግር የሆነብን ማኅበረሰቡ ጋር የሚታየው የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ በተለይም ተቋሙ የሚሠራው ሥራና ማኅበረሰቡ ጋር ያለው የአረዳድ ችግር ሥራችን ላይ ሰፊ የሆነ ክፍተት ፈጥሮብናል፡፡ አንዳንዶች ተቋሙ በዋናነት የሚሠራው ሥራ የአዕምሮ ሕሙማን የሥነ ልቦና ምክር እንዲያገኙ ማድረግ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን ተቋሙ እንደዚህ ዓይነት ሥራ እየሠራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወደ እኛ ተቋም የሚመጡ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባው ነገር፣ እኛ የምንሠራው  ‹‹የሕይወት ክህሎት›› እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ችግር በትንሹም ቢሆን ሥራችን ላይ ተግዳሮት ፈጥሮብናል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቤተሰብን ማዕከል ያደረገ ሥራ እየሠሩ አለመሆኑ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ ቤተሰብና ልጆች ላይ መሥራት አገር መገንባት መሆኑን በማመን፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ይህ ከሆነ አገርን ማዳን ይቻላል፡፡ ቤተሰብ ላይ መሥራት ማኅበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያመጣል፡፡ ስለዚህ ተቋማችን በዚህ ጉዳይ ላይ ወጥ የሆነ አሠራር ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ማለት ይቻላል፡፡    

  ሪፖርተር፡- ተቋሙ በዋናነት የሚሠራው አዲስ አበባ ከተማ ላይ ነው፡፡ በክልሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ምን ዓይነት አሠራር ወጥናችኋል?

  አቶ ወንድወሰን፡- በእርግጥ ለጊዜው መቀመጫችንን አዲስ አበባ ከተማ ላይ አድርገን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን በያዝነው ዓመት ሐዋሳ ላይ ሌላ ቢሮ ከፍተን የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት አጠናቀናል፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ክልሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን የምንሠራ ይሆናል፡፡ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የወጣቶች፣ የሕፃናት ልጆችና የወላጆችን የሕይወት ክህሎት ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ ይህንን ያልኩበት ዋነኛ ምክንያት አብዛኛውን ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡ በቂ የሆነ ግንዛቤ ስለሌለው አገር ሲያጠፋ ይታያል፡፡ በተለይም ትምህርት ቤቶች ላይ እንዲህ ዓይነት አሠራሮች አለመኖሩ በሥነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለማግኘት ይቸግራል፡፡ መንግሥትም እንዲህ ዓይነት አሠራሮችን ባለመዘርጋቱ ዘርፉ ላይ ሰፊ የሆነ ክፍተት ሊታይ ችሏል፡፡ ወላጆችም ልጆቻቸውን በምን ዓይነት ሁኔታ ማሳደግ እንዳለባቸው የሚደግፍ አሠራር አለመኖሩ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?

  አቶ ወንድወሰን፡- ተቋሙ በቀጣይ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ወጣቶችን የሚያገግሙበት ማዕከል ለማቋቋም ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ማዕከሉንም ለመገንባት ከመንግሥት ቦታ እየጠየቅን እንገኛለን፡፡ ቦታውንም ካገኘን በኋላ፣ በ2016 ዓ.ም. ማዕከሉን የምናቋቁም ይሆናል፡፡ በቀጣይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ኦን ላይን ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ለመስጠት እየሠራን ነው፡፡ በ2015 ዓ.ም. የሚያስፈልጉ መሥፈርቶችን በማሟላት በዋሽንግተን ዲሲ አንድ ቢሮ ለመክፈት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ቢሮውም የኢትዮጵያና የኤርትራ ዜጎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ ይህ ከተሳካም ዲሲ ላይ የሚኖሩ አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን አገልግሎቱን የሚያገኙበት መንገድ ይኖራል፡፡ ይህ ከሆነ በርካታ ሕፃናት፣ ልጆችንና ወጣቶችን መታደግ ይቻላል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከሌሎች ተቋሞች ጋር ቅንጅት ፈጥሮ ከመሥራት አኳያ ምን ሠርታችኋል?

  አቶ ወንድወሰን፡- ተቋሙ ከተለያዩ ተቋሞች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል ከኤስኦኤስ፣ ከሰላም ችልድረን ቪሌጅ፣ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሌሎች የውጭ አገር ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከእነዚህም ተቋሞች ጋር በምንሠራበት ወቅት የተለያዩ ልምዶችን አካብተን ሥራችንን በተገቢው መንገድ እንድንሠራ ረድቶናል፡፡ ይህም ያሉብንን ክፍተቶች እንድናይና አማራጭ መንገድ እንድንጠቀም ረድቶናል ማለት ይቻላል፡፡

  ሪፖርተር፡- በተቋማችሁ በኩል አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎችን በምን መንገድ ነው ክህሎታቸውን የምትፈትሹት?

  አቶ ወንድወሰን፡- የካውንስሊንግ አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች ሥልጠናውን የወሰዱና የተማሩ ናቸው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ወደ ተቋሙ በሚመጡበት ጊዜ የስድስት ቀናት ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ አልታ ካውንስሊንግ በዚህ ሥራ ለተሠማሩ ለበርካታ ሰዎች መሠረታዊ የሆነ ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፣ አሁንም የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በተቋሙ ሥርም የሚገኙ ሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ሥልጠናውን እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል፡፡ ይህም በዘርፉ ላይ ትልቅ የሆነ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል መንገድ ከፍቶልናል፡፡

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰሜኑ ጦርነት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ አይነሱም ተባለ

  ልማት ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ታማሚ ብድር እንዲነሳለት ጠይቋል የኢትዮጵያ...

  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

  በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

  ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ለማጣጣም የተነሳው ተቋም

  በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት...

  የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት የመቀየር ጉዞ

  ብርሃን ለሕፃናት የማኅበረሰብ ተሃድሶ መርህን መሠረት በማድረግ፣ በዋናነትም አካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለማገዝ ከ25 ዓመታት በፊት በጥቂት በጎ ፈቃደኞች የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...

  ‹‹ኅብረተሰቡ አስፈሪ ብሎ የፈረጃቸውን ልጆች በመደገፍ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ እያሳየን ነው›› የቢቢአር ኤፍ የውባንቺ ፕሮጀክት ኃላፊ ፀደይ ተፈራ    

  የብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን  (ቢቢአር ኤፍ) በሕጋዊ መንገድ ከመመዝገቡ ከአራት ዓመታት በፊት አገልግሎት የሚሰጡት በበጎ ፈቃደኝነት ነበር፡፡ ለውባንቺ ፕሮጀክት መከፈት ምክንያት የሆነውም እነሱ በበጎ...