Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ልናገርበስኳር ፋብሪካዎቻችን በመስኖ እየለማ ያለው ከአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚተርፍ ይታወቃል?

  በስኳር ፋብሪካዎቻችን በመስኖ እየለማ ያለው ከአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚተርፍ ይታወቃል?

  ቀን:

  በፉፉ ሞጆ

  በቅርቡ ‹መንግሥት ከውጭ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ሊያስገባ መሆኑ ተገለጸ› የሚል ዜና ስሰማ፣ ‹‹መላ የአገሪቱን ሕዝብ በምግብ ራስን ለመቻል ይረዳ ዘንድ በመስኖ መልማት ያለበት የትኛው ሰብልና ምን ያህል መሬት ያስፈልጋል?›› በሚል ርዕስ የጀመርኩትን ጽሑፍ አስቀምጬ ይህንን ለማለት ወደድኩ፡፡ የሌሎች ሰብሎችን ዓይነትና እያንዳንዱ ሰብል በመስኖ መልማት የሚኖርበት የመሬት ስፋትን በተመለከተ፣ ወደፊት በግርድፉም ቢሆን የምመለስበት ይመስለኛል (ግድ ሳይሆን አይቀርም)፣ እናም ወደ ስኳራችን እንግባ፡፡

  የስኳር ጉዳይን ካነሳን የአገራችንን የምርት ፍላጎት ለማሟላት ስንሠራ ምን ያህል ምርት ያስፈልገናል? ምንድነው በእጃችን የያዝነው? ችግራችን የቱ ጋ ይሆን? የሚሉ ቀላል ጥያቄዎች ላይ መሠረት አድርገን አለመንቀሳቀሳችንን ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ሌሎች ጉዳዮቻችንንም ቢሆን በዚህ መንገዱ ይሆን እንዴ የምንሠራው? ብለን እንድንጠይቅ ብሎም ስኳር ወቅታዊ አገራዊና የህልውና ችግር እንደ መሆኑ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው በር ይከፈታልና ነገሩ ሰፊ ቢሆንም ቅሉ፣ አኃዛዊ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ በአጭሩ አንባቢ በቀላሉ ለመረዳት እንዲያመቸውና እንዳይሰለች የራሱን አስተያየት መስጠት እንዲያስችለው አድርጌ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ አልደመድመውም፡፡

  የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (Ethiopian Public Health Institute, 2022) አንድ ኢትዮጵያዊ ሊከተል የሚገባውን የምግብ ሥርዓት በተመለከተ ዓለም አቀፋዊ መርሆችን መሠረት አድርጎ በቅርቡ ባሳተመው መመርያ ውስጥ ስኳርን በተመለከተ እንዲህ ይላል፡፡ ዕድሜው ሁለትና ከዚያ በላይ የሆነ ኢትዮጵያዊ ራሱን በቀን ከ30 ግራም በላይ ስኳርና ስኳር ነክ ነገሮችን ከመውሰድ መቆጠብ አለበት (Two years and above adults to limit intake of sugar, sweets, and soft drinks below 30 g per day)፡፡ በዓመት ሲሰላ እጅግ ከበዛ ለአንድ ሰው 10 ኪሎ ግራም ስኳር ያስፈልገዋል ማለት ይሆናል፡፡

  ሥሌታችን የሚከተሉትን ዕሳቤዎች ጭምር መሠረት ያደረገ ሲሆን፣ ይህም ምን ያህል ጥንቃቄ እንደተደረገበት ለመገንዘብ ይረዳናልና ተመልከቷቸው፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስኳርን የሚያገኘው በአገር ውስጥ ስኳር ፋብሪካዎች አማካይነት ተመርቶ ከሚወጣው የስኳር ምርት ብቻ ነው፣ ወይም ስኳርን የሚያገኘው ከሸንኮራ አገዳ ምርት በፋብሪካዎቻችን አማካይነት ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ምግቦች ውስጥ የሚያገኘውን የስኳር ምንጭ ለጊዜው እንርሳው፡፡ ሁሉም ሰው በማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተቀመጠውን ከፍተኛ የስኳር መጠን 10 ኪሎ ግራም በዓመት ይወስዳል እንበል፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዕድሜው ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ ነው ብለን እንጨምርበት፡፡

  የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን እ.ኤ.አ. 2013 ያሳተመው የወደፊት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ትንበያ መረጃን መሠረት አድርገን፣ በ2014 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 2022) 106 ሚሊዮን ሕዝብ አካባቢ እንደምንደርስ ይናገራል፡፡ ካስፈለገ በተለምዶ ሁሉም የሚመዘውን 120 እና 110 ሚሊዮን ሕዝብ ብዛትንም መጠቀም ይቻላል፡፡ ስኳር ወደ ውጭ አንልክም የሚለውን እንጨምርበት፡፡ እንዲህ ያለ ቸር ዕሳቤ ላይ ተመሥርቶ አገራዊ የምርት ግመታ ማድረግ ይበጃል ወይ ብሎ የሚጠይቅ ጠንቃቃ አንባቢና ታዛቢ፣ ግዴለም ሥሌቱን በየዋህነት ጀምሮ ባይሆን በኋላ ላይ እንደ ማሳሰቢያ እመለስበታለሁ ብዬ ልቀጥል፡፡

  እንግዲህ በ10 ኪሎ ግራም ስኳርና በ105 ሚሊዮን ሕዝብ ሥሌት መሠረት፣ አገራችን በየዓመቱ 1,050,000 ቶን ስኳር ያስፈልጋታል ማለት ነው፡፡

  ወደ ሸንኮራ ማሳዎቻችን ስንገባ ደግሞ የሚከተሉትን አኃዛዊ መረጃዎችን መሠረት አድርገን እንቀጥል፣ ብሎም እናስላው፡፡ በኢትዮጵያ ስኳር ፋብሪካዎች ታሪካዊ መረጃዎቻቸው መሠረት እያንዳንዱን 100 ኪሎ ግራም ስኳር ለማምረት አንድ ፋብሪካ በአማካይ 9,090 ኪሎ ግራም ሸንኮራ አገዳ መፍጨት ይኖርበታል፡፡ በሌላ አነጋገር አማካይ የስኳርና የሸንኮራ አገዳ ክብደት ምጣኔ በግርድፉ 1 ለ 9 (አንድ ለዘጠኝ) እንደ ማለት ነው (Average Cane to Sugar Recovery Ratio of 11%)፡፡ ይህ የፋብሪካዎች የረዥም ዓመታት መረጃን መሠረት ማደረጉን እርግጠኛ ሁኑ እላችኋለሁ፣ ደግሞም ነው፡፡ ይህ እንዲህ ከሆነ ታድያ 1,050,000 ቶን ስኳር ለማግኝት በየዓመቱ እስከ 9,545,455 ቶን አገዳ መፍጨት ይጠበቅብናል፣ ወይም ፋብሪካዎቹ መፍጨት አለባቸው ማለት ነው፡፡

  የመስኖ እርሻ ማሳዎች የሸንኮራ አገዳ አማካይ ምርታማነት በፊት ከነበረበት ከ200 እና ከ180 ቶን በሔክታር እየተምዘገዘገ ወርዶ፣ አሁን እስከ 130 ቶን በሔክታር አካባቢ ላይ ይንገዳገዳል ብቻ ሳይሆን እስከ 90 ቶን በሔክታር የወረዱም አሉ፡፡ ለእኛ ሥሌት 150 ቶን በሔክታር ወስደን ዓመታዊ የስኳር ፍላጎታችንን ለመሸፈን፣ በየዓመቱ ታጭዶ ወደ ፋብሪካ የሚላክ ሸንኮራ አገዳ የሚቆረጥበት በግርድፉ 63,636 ሔክታር ማሳ ያስፈልገናል፡፡ እንደሚታወቀው ደግሞ ሁሉም ማሳ በየዓመቱ አይታጨድም፡፡ መረጃዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ፋብሪካዎቹ በአግባቡ የሚሠሩ ከሆነ የአጠቃላይ እርሻ መሬቱን እስከ 80 ከመቶ የሚደርስ ማሳ በየዓመቱ እያጨዱ ወደ ፋብሪካ ማሽኖች መላካቸውን ነው፡፡

  እንግዲህ በመላ አገራችን ለሚገኘው እያንዳንዱ ሰው በየዓመቱ 10 ኪሎ ግራም ስኳር ለማቅረብ በአጠቃላይ 79,545 ሔክታር በመስኖ የሚለማ በሸንኮራ አገዳ የተሸፈነ እርሻ (የዝናብ እርሻም ሊሆን ይችላል) ሊኖረን ግድ ይለናል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ባለንበት ጊዜ በአገራችን በሚገኙ ስድስት ስኳር ፋብሪካዎች ሥር በመስኖ እየለማ የሚገኘው የሸንኮራ አገዳ መሬት ስፋት አጠቃላይ ድምር 72,700 ሔክታር ነው፡፡ ከሚፈለገው ወይም መሸፈን ከነበረበት 91 ከመቶ አካባቢ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

  ሰንጠረዥ፡- የአገራችን የስኳርና የሸንኮራ አገዳ ማሳ ስፋት ፍላጎትና አሁን እየለማ ያለ የመስኖ ማሳ ሽፋን

  በ2014 ዓ.ም.

   

   

  ሕዝብ ብዛት በሚሊዮን

  105

  ኢማስ (2006 ዓ.ም.)

  ከፍተኛ የስኳር መጠን፣ ኪሎ ግራም በሰው በዓመት

  10

   

  ጠቅላላ ስኳር ፍላጎት፣ በቶን

  1,050,000

   

  የስኳርና ሸንኮራ አገዳ ምጣኔ (Cane to Sugar Recovery Ratio) በመቶኛ

  11

  የፋብሪካዎች ታሪካዊ ግን አማካይ አኃዝ

  ጠቅላላ መታጨድ ያለበት ሸንኮራ አገዳ መጠን በቶን

  9,545,455

   

  የሸንኮራ አገዳ ምርታማነት በአማካይ ቶን በሔክታር

  150

  በትንሹም ቢሆን በአግባቡ ከተያዘ ማሳ

  መታጨድ ያለበት የሸንኮራ አገዳ ማሳ ስፋት፣ በሔክታር

  63,636

   

  ጠቅላላ የሸንኮራ አገዳ የተሸፈነ ማሳ ስፋት በሔክታር

  79,545

  80 ከመቶ ማሳ ከታጨደ

  አሁን እየለማ ያለ ወይም በሸንኮራ አገዳ የተሸፈነ ማሳ ስፋት በሔክታር

  72,700

   

   

  አሁን

  ሙሉ አቅሙ ከተተገበረ

  ወንጂ

  10,000

  10,000

  መተሀራ

  10,200

  10,200

  ፊንጫ

  19,500

  19,500

  ከሰም (ከግለሰብ ማሳ ጋር ተደምሮ)

  9,000

  15,000

  ኩራዝ

  19,000

  60,000

  በለስ

  5,000

  20,000

  ድምር

  72,700

  134,700

  በ2013 ዓ.ም. አገር ውስጥ የተመረተ ስኳር መጠን 240,000 ቶን ቢሆንም መሬቱ 959,640 ቶን ምርት የመስጠት አቅም ነበረው፡፡

   

  ቀደም ሲል ያነሳናቸውን የዋህና ቸር ታሳቢዎችን ከግምት አስገብተን ዝርዝሩ በሰንጠረዥ ውስጥ በግልጽ እንደተመለከተው፣ ከዚህ 72,700 ሔክታር የመስኖ ማሳ ላይ መገኘት የነበረበት አጠቃላይ የስኳር መጠን 959,640 ቶን ነበር፡፡ የሚገርመው በ2013 ዓ.ም. የተመረተው የስኳር መጠን 240,000 ቶን ብቻ ሲሆን፣ ይህም የአገሪቱን አጠቃላይ ፍላጎት 23 በመቶ ከእርሻ መሬቱ መገኘት ከነበረበት አጠቃላይ ምርት ውስጥ ደግሞ 25 ከመቶ ብቻ የሚሸፍን መሆኑ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ሰው ሲሰላ በዓመት 2.29 ኪሎ ግራም ይዳረሳል፡፡ እስከ 75 በመቶ የሚደርሰውን የእርሻ መሬታችን አቅም የት ደረሰ ወይም የት ገባ ታድያ? ምን ዋጠው?

  ምናልባት 72,700 ሔክታር ከ 79,545 ሔክታር ያንሳል እኮ ብሎ የሚጠይቅ ካለ ወደ የተጋነኑ ብቻ ሳይሆን የዋህነት የሞላቸው ብለን የዘረዘርናቸውን ታሳቢዎቻችንን መከለስ ይቻላል፡፡ ሌላውን እንተውና እንደው ቀለል አድርገን አንድ ሰው 7.5 ኪሎ ግራም ስኳር በዓመት ማግኘት ቢችል እንበል (አሁን ቢበዛ እየተጠቀመ ነው ተብሎ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚታወቀው እኮ ቢበዛ አራት ኪሎ ግራም በዓመት ብቻ ስለመሆኑ ላስታውሳችሁ)፡፡ ስኳር ተጠቃሚ ሕዝብ 80 ሚሊዮን ሕዝብ ነው ብለን ስናሰላው የሚያስፈልገን የሸንኮራ አገዳ መስኖ እርሻ በግማሽ ቀንሶ ወደ 45,454.5 ሔክታር ይወርዳል፡፡ ስለዚህ በአግባቡ ከሠራንባቸው አሁን እየለማ ያለው መሬትና ስድስቱ ፋብሪካዎች አገራዊ የስኳር ፍላጎትን በአስተማማኝ ሁኔታ ሸፍነው፣ ጥቂትም ብትሆን ወደ ውጪ ለመላክ ጭምር ይበቁ ነበር ማለት ነው፡፡

  በፊት እስከ 500,000 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ የሚያበቅሉ አሥር ፋብሪካዎች አቅደን እንደነበር ስትገነዘቡ ምን ተሰማችሁ? ቀደም ባሉ የሪፖርተር ጋዜጣ መጣጥፎቼ በአንዱ ውስጥ መረን የለቀቀ ዕቅድ ስል ገልጬዋለሁ፡፡ ከአገር ውስጥ ፍላጎቱን አሟልቶ ከአሥር እጥፍ በላይ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ ታስቦ ነበር ማለት አይደለምን?

  ሰበብ ሳናበዛ 75 ከመቶ ምርት የት ገባ ብለን መጠየቃችንን እንቀጥል፡፡ ለዚህ እጅግ የወረደ ምርታማነት እንደ ምክንያት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት መካከል ዝቅተኛ የእርሻ ማሳ፣ ምርታማነት ከፍተኛ ድኅረ ምርት ብክነት፣ የፋብሪካዎች ከአቅም በታች ሸንኮራ አገዳ እየፈጩ መሆኑ፣ የፋብሪካዎቹ በተደጋጋሚ ብልሽት ምክንያት ከሥራ መስተጓጎልና ዝቅተኛ ከሽንኮራ አገዳ የስኳር ግኝት (ደካማ የፋብሪካ ምርታማነት ከአሥር በመቶ በታች መሆን)፣ ወዘተ ናቸው ተብለው ሲጠቀሱ ይስተዋላል፡፡ በእርግጥም ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእርሻዎቹን ምርታማነት ከቀነሱት ምክንያቶች መካከል የመስኖ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር ሥርዓቱ እጅግ መበላሸትንና እየተበላሸ መቀጠሉ ከቀዳሚ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ፣ በርካታ ጥናቶችና ትዝብቶች ይመሰክራሉ፡፡ ለማንኛውም የእኔ ዓላማ ስለእነዚህ ጉዳዮች ለመዘርዘር ሳይሆን፣ ታዲያ ራሳችንን በስኳር ምርት የምንችለው መቼ ነው የሚለውን ጥያቄ በእናንተ ውስጥ ለመጫር ነው፡፡ በእርግጥ የተዘረዘሩት ምክንያቶች የአንድን ኢንዱስትሪ ምርታማነት በዚህ ልክ ሊያወርዱትና ዝቅ ሊያደርጉት ይችላሉን? አቅምስ አላቸውን? ወይስ ሌላ ምክንያት ይኖር ይሆን? ጉዳዩ መመርመር ያለበት አይመስላችሁምን?

  ከውጭ የሚገባው ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማለት እኮ 200,000 ቶን ማለት ነው፡፡ ፋብሪካዎቹ  በ2013 ዓ.ም. ካመረቱት 240,000 ቶን ስኳር ጋር እኩል ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንግዲህ በድጋሚ ከስድስት ወራት በኋላ ቢያንስ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል እንጨምራለን ማለት ነው? እስከ መቼ እንዘልቃለን? ያሉንን ስኳር ፋብሪካዎች አቅም ማሻሻል ይመረጣል? ወይስ እንደ ሲሚንቶ ፋብሪካዎቻችን አዳዲስ ፋብሪካዎችን እየከፈትን እንቀጥላለን? በእጃችን ያሉት የአቅማቸውን 25 በመቶ በታች የሚሰጡን ከሆነ፣ አዲስ የምንከፍታቸው ፍላጎታችንን ስለማሟላታቸው ዋስትናችን ምንድነው? በዚህ አያያዝ ምን ያህል እርሻና ፋብሪካ ሊኖረን ወይም መጨመር እንዳለብን እንዴት እናውቃለን? መጨረሻውስ የት ይሆን? ከውጭ በዶላር የሚገዙ ነገሮች የሚፈጥሩት ትልቅ ቀዳዳ ተመራጭ በሆኑባት አገራችን፣ የፋብሪካዎቹና የእርሻዎቹን አቅም የማሻሻል ነገረ ሥራ የህልም እንጀራ ሆኖብኝ ተስፋ እንዳልቆርጥ እፈራለሁ፡፡

  ማስረዘም አልፈለኩም፣ ከቻልኩና ከበረታሁ ገና ስለሌሎች ሰብሎቻችን ለመጻፍ አስባለሁ፡፡  ‹‹ያለ መስኖ ንቁ ተሳትፎ…›› በሚል ያቀረብኩት መጣጥፍ ቀጣይ ይሆናል፡፡ ጉዱ ስለማያልቀው ስለስኳራችን ይህችን ያህል ከተነፈስኩ ጉዳዩን አድርሻለሁና ተካፈሉት፡፡ ምን ይሻላል ትላላችሁ? እናንተ ጨምሩበት፡፡ ቸር እንሰንብት!

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡        

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...