Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሰቀቀን!

የዛሬው ጉዞ ከጦር ኃይሎች ወደ ፒያሳ ነው፡፡ ታክሲ መሳፈሪያው ሠልፍ ላይ አንዱ፣ ‹‹እንባና ሳቅ ሰው የመሆን ዕዳ ነባር ምሰሶዎች ናቸው። ይኼው እዚያ ታክሲ ጎማ ሥር አንድ ጠኔ ያደባየው ወድቆ እጆቹን መዘርጋት አቅቶት፣ ያው መንገዱን ተሻግሮ አንዱ ሕይወት አልጋ ባልጋ ሆኖለት፣ ጭረት የማያውቀው የሚመስል ጎልማሳ ሥጋ ቤት በር ላይ ቁረጡ እንቁረጥ ሲል፣ የመሸብን ሳይነጋልን የነጋላቸው የንጋታቸው ብርሃን ዓይን ወግቶ ይገላል። ሕይወት በአድሏዊነት ስትታማ ደግሞ መልሳ የወደቀውን አንስታ፣ ከፍ ከፍ ያለውን ዝቅ አድርጋ ስሟን እያደሰች ግራ ገብቷት ግራ ታጋባለች። እንጀራን ተገን አድርጎ የሚያጣድፈን ኑሮ ሞልቶ ሳይሞላና ጎድሎ ሳይጎል ለምናይ አተኳሪዎች የጎዳናው ጥልቅ ዓላማ ከትርምሱ ጀርባ ለምን? ለማን? እንዴት? ከየት? ወዴት?›› እያለ ብሶት በጥያቄ የሚደረድር ሐሳብ ሰነዘረ። አንዳንዱ እኮ ይናገረዋል፡፡ ሰውየው ታክሲ ወረፋ ላይ ሳይሆን የሆነ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ክፍል ውስጥ “ሌክቸር” የሚያደርግ ይመስል ነበረ፡፡ ነበረ ነው እንግዲህ!

በስንት መከራ የተገኘ ሚኒባስ ጭኖን ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ወጣቶች በስልክ እያወሩ ነው። ‹‹እሺ እባክህ እናንተ በውስኪ እኛ ደግሞ በጠላ እያዘገምን ነው…›› ሲለው ይኼኛው፣ ‹‹ክብሩ ይስፋ እርሱ መድኃኔዓለም…›› ይላል በወዲያ በኩል በማይክራን ድምፁ የሚሰማው። ‹‹ምናለበት ለብቻቸው ቢያወሩ። ‘ላውድ’ ላይ አድርገው ሲያደነቁሩን ዝም ትላለህ?›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ። ወያላው በፈገግታ እያያቸው ሸሸት አለ። ‹‹እኔ የምለው? ለንደን እንዴት ነው ዌዘሩ?›› አለ እዚህ ሸገር ታክሲ ውስጥ ያለው። ‹‹ፋይን ነው። ምን ኑሮማ ያለው አዱገነት አይደለም እንዴ? እኔማ ከእንግዲህ ቆይ ታየኛለህ ያለችኝን ሰባስቤ ሮጬ መምጣት ነው…›› ይለዋል። ‹‹እኛ በየት በኩል ሮጠን እንውጣ እንላለን እሱ ሮጬ እመጣለሁ ይላል። አይ አለማወቅ።  ከራርመው ሲለዩዋት ለካ አገር ታባባለች…››  ይላል ጎልማሳው። ለምን አታባባ!

‹‹የሚናገረውን አያውቅምና ይቅር በሉት ብሎ ማለፍ ነው…›› ባዩዋ ደግሞ ከጀርባ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ቢጫ የአንገት ልብስ የጠመጠመች ተሳፋሪ ናት። ‹‹እህም…›› ይላል ጎልማሳው ዓይን ዓይኗን እያየ። ‹‹እኔ የምልህ እስኪ ሚስትም ፈልጉልን እንጂ። እኛማ እንዳያያዛችን ማጥመድ የምንችል አልመሰለኝም…›› ሲል የለንደኑ ይኼኛው፣ ‹‹ዕድሜ ለዳያስፖራ ተንከባካቢው መንግሥታችን ከየሄዳችሁበት ሰብስቦ አምጥቶ መሀላችን በተናችሁ፣ ይኼው ለመድናችሁ። እንዳንተ ይኼን ያህል ዘመን ለንደን የኖረ አይደለም አንድ ሦስት ሚስት አታገባም ነበር?›› አለውና ተሳሳቁ። በዚህ መሀል ጨዋታቸው ተቋረጠ። ‹‹አሁንም የቴሌ ኔትወርክ እንደባሰበት ነው አይደል…›› ከማለቱ አንዱ ተሳፋሪ፣ ‹‹ይኼ የቴሌ ኔትወርክ ሳይሆን የሳፋሪኮም ነው፡፡ ችግሩ የኔትወርክ ሳይሆን የእኔ የአየር ሰዓት አልቆ ነው…›› ብሎ ከአዲሱ ወሬ አሟቂ ገላገለን፡፡ ሰበብ ለመደርደር ነገር የሚያፈላልጉ እንዲህ ወሽመጣቸው ሲበጠስ ደስ ይላል፡፡ በጣም እንጂ!

ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታው ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ መነታረክ ክልክል ነው…›› እያለ የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። የስፖርት ትንታኔ እናደምጣለን። ‹‹ክርስቲያኖ ሮናልዶ 700ኛውን የክለብ ጎል ማግባቱ በጣም የሚያስደንቀን ታሪክ ነው…›› ይላል ተንታኙ፡፡ ‹‹ስለራሱ ታሪክ አያወራም እንዴ? ለምን የእኛን ይጨምራል?›› ይላል መጨረሻ ወንበር። ‹‹የእውነት ግን ሮናልዶ አንጀት ይበላል። አበቃለት ሲባል ታሪክ እየሠራ ያስደምመናል…›› ስትል ባለ አንገት ልብሷ፣ ‹‹ታሪክ መሥራትማ እኛን የሚያህል አልነበረም፡፡ ግን ምን ያደርጋል በገዛ እጃችን መጫወቻ ሆንን…›› ብሎ ጎልማሳው አፈጠጠባት። ‹‹በኳስ ወሬ መፋጠጡን ትታችሁ ለአገር የሚጠቅም ልማት ላይ ለምን አታተኩሩም…›› ብሎ አንዱ ከጋቢና ወሬ አስገለበጠ። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየመች ወይዘሮ ‹‹በስንቱ እንፋጠጥ?›› አለች። ወዲያው ጋቢና የተሰየመው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ ወሰደው። ጉድ እኮ ነው!

አፍታም አልቆየ ሜሲ ይበልጣል ሮናልዶ የሚለው ክርክር ጦፈ። ‹‹ደግሞ ሜሲ ተጫዋች ነው? በስንቶቹ ላብና ደም እኮ ነው እዚህ የደረሰው…›› ሲል አንዱ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ስለኳስ ተጫዋቹ ሜሲ ነው የሚያወራው ወይስ ጦርነት ውስጥ የሚዋጋ ሌላ ሜሲ አለ?›› ይላል ሌላው። ‹‹ሮናልዶንማ የሚያክለው የለም። ምናልባት ራሱ ስለራሱ ችሎታ አዳንቆ ሜሲን እበልጠዋለሁ ማለቱ ቢያስተቸውም…›› ብሎ ሌላው ንግግሩን ሳይጨርስ ደግሞ ወዲያ ገቢና ያለው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹እኔ እኮ የእኛ ሰው ብቻ ይመስለኝ ነበር በእኔ እበልጥ በእኔ እሻል የሚዳማው? የእኔ አስተዳደር፣ የአገር ግንባታ፣ የኢኮኖሚ ልማት፣ ወዘተ ካለፈው ከሚመጣው ይለያል የሚል ሐበሻ ብቻ ይመስለኝ ነበር። ለካ ፈረንጅም ራሱን ያንቆለጳጵሳል?›› ብሎ ታኬታ የሚጫማውን ዘውድ ከሚጭነው ያመሳስላል። ‹‹በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት እንዲቀሰቀስ ያደረጉ ምዕራባውያን ደንቆሮዎች የኑክሌር ጦርነት ለማስነሳት መከራቸውን እያዩ፣ እኛ የሁለት ቅሪላ አልፊዎች ጉዳይ ምናችን ሆኖ ነው የምንነታረከው…›› ብሎ አንዱ ገላገለን፡፡ ይሻላል!

 ጉዟችን ቀጥሏል። የታክሲያችን ፍጥነት እየጨመረ ሲሄድ ጆሮ የሚያደምጠው ዓይን የሚታዘበው ነገር አብሮ ጨምሯል። ሁለት ሴቶች እየተንሾካሾኩ የደወለላቸውን ደንበኛ ያስለፈልፋሉ። አንደኛዋ፣ ‹‹እኔ የምለው? ካርድ በነፃ የሚሞላልህ ኢትዮ ቴሌኮም ነው ወይስ ሳፋሪኮም? ምናለበት ስልኩን ባትጫወትበት?›› ስትል እሱ የሚላትን አንሰማም። ‹‹እኛ በቀላሉ አንገኝማ፣ ልማት ላይ ነን…›› ጓደኛዋ በይው ያለቻትን ትለዋለች። ስለብቸኝነት አነሳባት መሰል ደግሞ፣ ‹‹ሁሉም ብቸኛ በሆነበት አገር የአንተ ብቸኝነት ምኑ  ይገርማል? ፓርላማችን ብቸኛ፣ ሕዝቡ ብቸኛ፣ አገራችን በበጎም በክፉም አንደኛና ብቸኛ፣ ታዲያ ያንተ ብቸኛ መሆን ምኑ ላይ ነው የሚያሳዝነው? እያሾፍኩብህ ከመሰለህ ‘ኔትወርኩን’ ለሠርቶ አዳሪዎች ለቀቅ አድርግላቸው…›› ትለዋለች። ተሳፋሪዎች የመድረክ ጭውውት እንደሚያዳምጡ አንዳንዴ ሴቶቹን ዞር ብለው እየገላመጡ፣ ዘና እያሉ፣ አንዳንዴም እያዘኑ ለብቻቸው ይነጋገራሉ። ትርዒቱ ቀጥሏል!

ጥቂት እንደተጓዝን ስል ተቋረጠና ስልኩ ተዘጋ። ‹‹እንዲህ መቆራረጥ ባይኖር ምን ይውጠን ነበር? ሥራ ፈት ሁላ…›› ብላ ስታናግር የነበረችው ልጅ ተቆናጠረች። ጓደኛዋ፣ ‹‹ቆይ ግን እሱን የሚያህል ሰውዬ? በዚህ ዕድሜው ነውር አይደለም? ትንሽ ዕፎይ ብንል ነገር ተረሳና ንስሐም የአስተዋሽ ያለህ ማለት ጀመረ? እምዬ ኢትዮጵያ ስንት ጉድ በሆዷ እንዳላመቀች? ሆ…ሆ…›› ብላ አንባረቀች። ‹‹አይገርምሽም? ደግሞ ብቸኝነት አሰቃየኝ ይለኛል። ስንትና ስንት በወረራ የተያዘ መሬት ሸጦ ብሩን እየበተነ ከስንቶች ጋር እየማገጠ ብቻዬን ነኝ ሲል ትንሽ አያፍርም? በዚህ ላይ አምስት ኮንዶሚኒየሞች ተከራይቶ ቅምጦች ማስቀመጡን የማናውቅ መሰለው እንዴ…›› እየተባባሉ ወደ ግል ጨዋታቸው ዞሩ። የኮንዶሚኒየም ነገር ሲነሳ ምስኪን ቆጣቢዎች ናቸው መሰል እየተጠቃቀሱ ‘ስለቁጠባ ቤቱ ጉዳይ የሰማችሁ እስኪ እንያችሁ’ መባባል ያዙ። አሥር ዓመት ሙሉ ቆጥበው አስታዋሽ ያጡ ምስኪኖች አንጀት ይበላሉ፡፡ በጣም!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ኡ…ሁ…ሁ…ሁ…›› ብሎ አንዱ ከመጨረሻ ወንበር  በረጅሙ ተነፈሰ። ‹‹ምነው? ታፍነህ ነበር እንዴ?›› አሉት አጠገቡ የተሰየሙት። ‹‹የለም በነፃ መኖር አምሮኝ ነው…›› ብሎ መለሰ። ‹‹ሲያምርህ ይቅር እንዳንልህ አንተም እንደ እኛ ብዙ አምሮህ የቀረ ነገር ስለሚኖር ሌላ ዕጦት አንመኝልህም…›› አለችው ቆንጂት። ‹‹ደግሞ በነፃ መኖር ያማረው ማን በነፃ ሲኖር ዓይቶ ነው? እንኳን በሰው በአህያም አልተቻለ…›› ጎልማሳው ገባበት። ‹‹አህያ? የምን አህያ?›› ጠየቀች ወይዘሮዋ። ‹‹አልሰማችሁም ይህንን ቀልድ። ሰውዬው በቃ ኑሮ ከበደውና የእኔ ቢቀር አህያዬን በነፃ ማኖር አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። ከዚያ ቀስ እያለ የዕለት ምግቧን ሲቀንስ፣ ቀስ እያለ ሲቀንስ… ሲቀንስ… ሲቀንስ… መጨረሻ ላይ አህያው ፍግም አለች። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘ወይኔ በነፃ ላኖራት ትንሽ ሲቀረኝ አህያዬ ሞተች’ ጉድ እኮ ነው…›› ሲል ተሳፋሪዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ተናደዱ። ‹‹እህም… ቀልድ… እንኳን በነፃ ተከፍሎስ መኖር ተቻለ እንዴ ዘንድሮ?›› ብላ ወይዘሮዋ ነገር ስትጀምር፣ ‹‹ክፍያውም ዋጋ ስላጣ እኮ ነው እኔም በነፃ መኖር ያማረኝ…›› ብሎ ያ አጉል ቀልደኛ ወጣት ጣልቃ ገባባት። ‹‹መጨረሻ…›› ብሎ ወያላው ሲያወርደን የነፃና የዋጋ ነገር ከየልቦናችን ጋር አነጋገረን፡፡ ኧረ በስንቱ እንነጋገር? በስንቱስ እንሳቀቅ? ሰቀቀን በዛ እኮ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት