Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አስገዳጅ ደረጃዎችን ለመቆጣጠርና ተፈጻሚ ለማድረግ ሕግ ሊወጣ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

አስገዳጅ ደረጃዎች የወጣላቸው ምርቶችና አገልግሎቶችን ለመቆጣጠርና ለማስፈጸም የአስገዳጅ ደረጃዎች ማስፈጸሚያ ሕግ እስካሁን ባለመኖሩ ትልቅ ችግር ሆኖ በመቆየቱ የአስገዳጅ ደረጃዎች አዋጅ ሊወጣ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እስካሁን የደረጃዎች ኢንስቲትዩት ለተለያዩ ምርትና አገልግሎቶች አስገዳጅ ደረጃዎችን ያወጣ ቢሆንም፣ ይህንን ወደ ተግባር የሚለውጥና አስገዳጅ ደረጃዎችን የሚያስፈጽም ሕግ ሳይወጣ ቆይቷል፡፡ አስገዳጅ ደረጃዎችን ለማስፈጸም የሚያስችለው ሕግ ያለመውጣቱ ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱንም የመሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡  

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የስትራቴጂክ ጉዳዮች ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዑርጌሳ ባይሳ ባለፈው ቅዳሜ በአዳማ ከተማ ከጋዜጠኞች ጋር በነበረው የውይይት መድረክ ላይ እንደገለጹት፣ ‹‹ደረጃዎች የሚወጡላቸው ምርትና አገልግሎቶችን ለማስፈጸም የሚደረግ ሕግ ሳይኖር መቆየቱ ትልቅ ችግር ነበር፤›› በመሆኑም ይህንን ክፍተት ለመድፈንና አስገዳጅ ደረጃዎች የወጣላቸው ምርቶችን የመቆጣጠር አቅም ለማሳደግ የአስገዳጅ ደረጃዎች ማስፈጻሚያ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን አመልክተዋል፡፡ ይህ የተዘጋጀው አዋጅም በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ዑርጌሳ  ገልጸዋል፡፡ አስገዳጅ ደረጃዎች ያሏቸው ምርቶችና አገልግሎቶች በሕግ የተቀመጠውን ዝቅተኛ መሥፈርት ካላሟሉ ወደ ገበያ ሊወጡ አይችሉም፡፡ አስገዳጅ ደረጃዎች የወጣላቸው ምርቶች ገበያ ውስጥ ከተገኙ እንዲሰበሰቡና እንዲወረሱ የሚደረጉ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዑርጌሳ፣ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስገዳጅ ደረጃዎችን በማውጣት ተፈጻሚነታቸውን በአግባቡ ለመከታተልና ለመቆጣጠር ይህ አዋጅ ትልቅ ዕገዛ እንደሚኖረው ጠቅሰዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የገቢና የወጪ ንግድ ምርቶችን የጥራት ደረጃ የመቆጣጠር ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ በተለይ ኅብረተሰቡን ብዙ ጊዜ የሚያማርሩ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ገበያ ውስጥ እንዳይኖሩ ያደርጋል፡፡ ተገቢውን መሥፈርት የማያሟሉ የንግድ ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከአገር እንዳይወጡም ሥልጣን የተሰጠው ይህ መሥሪያ ቤት፣ ከኢትዮጵያ የሚወጡትንም ምርቶች በተመሳሳይ የሚቆጣጠር ይሆናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃዎች የወጣላቸው ምርቶች ከ330 በላይ ናቸው፡፡ አስገዳጅ ያልሆኑ ግን ደረጃ የወጣላቸው ምርትና አገልግሎቶች ደግሞ ከ12 ሺሕ በላይ ናቸው፡፡ አስገዳጅ ደረጃዎች ከወጣላቸው ምርቶች መካከልም ሲሚንቶ፣ የታሸገ ውኃ፣ የምግብ ዘይት፣ ክብሪት፣ አምፖል፣ የአርማታ ብረት፣ ብሎኬትና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡

አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶችንና አገልግሎቶችን ጥራታቸው፣ ደኅንነታቸውና ትክክለኛነታቸው ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውሉ የመከታተል ኃላፊነቱን ለመወጣትም በበጀት ዓመቱ ሰፋ ያለ ዕቅድ መያዙን የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡  

ከዚህ አንፃርና ዋና ተግባራት ተብለው ከተጠቀሱ ውስጥ 390 ፋብሪካዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በተቀመጠው የጥራት ደረጃ መሠረት እያመረቱ ነው ወይ? በማለት የሚመዘኑ ይሆናል ተብሏል፡፡ በ42 የምርት ዓይነቶች ላይም ኢንስፔክሽን ሥራ እንደሚሠራ የሚያመለክተው የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ 2.17 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የገቢ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር የሚያደረግ መሆኑንም አመልክቷል፡፡ 752 ሺሕ ሜትሪክ ቶን የውጭ ምርቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ከደረጃ በታች የሆኑ ጥራታቸውን ያልጠበቁ ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው የአገር ገጽታ ላይ ችግር እንዳያስከትሉ ወይም ወደፊት ኤክስፖርት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖር የሚሠራ መሆኑንም ይኼው መረጃ አመልክቷል፡፡

ከምርቶችና አገልግሎቶች ጥራት ጋር በተያያዘ በበጀት ዓመቱ ይከናወናሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጨማሪ ተግባራት ውስጥ ሕጋዊ ሥነ ልክን በተመለከተ የሚካሄዱ ቁጥጥሮች ተተቃሽ ናቸው፡፡ በዚህም ረገድ 30 የታሸጉ የምርት ዓይነቶች የተጣራ መጠን ትክክለኛነት የማረጋገጥ፣ 2,000 የጤናና የደኅንነት መለኪያ መሣሪያዎችን ትክክኛነት ማረጋገጥ፣ 1.29 ሚሊዮን የሚሆኑ እንደ ሚዛንና የመሳሰሉት መለኪያዎች ትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራ በበጀት ዓመቱ ይሠራል ተብሏል፡፡ በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የንግድና ቁጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ደኤታ አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው፣ የጥራት ጉዳይ ወሳኝ በመሆኑ መንግሥት በዚህ ላይ ከፍተኛ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡ ‹‹ጥራት የአገር የጀርባ አጥንት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ በጥራት በማምረት በየትኛውም የገበያ መዳረሻ መሸጥ ካልተቻለ ችግር ስለሚሆን፣ እንዲሁም የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ማስተካከል ስለማይቻል በጥራት ላይ ጠንከር ብሎ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡  

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን አንፃር፣ ከተለያዩ አገሮችና ተቋማት ጋር የሚፈጽማቸው ስምምነቶች የሚጠቀሱ ሲሆን፣ ከዚህ ክዋኔ አንፃር ከስድስት አባል አገሮች ጋር ባይላተራል ድርድር ማድረግ፣ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ጋርም እንዲሁ የአገልግሎትና የንግድ ዕቃዎች ኦፈርና 22 ድርድሮች ብሔራዊ የትግበራ ስትራቴጂ ማዘጋጀትና በኢትዮጵያ የሌሉ ግን ለንግድ ቀጣናው የሚያስፈልጉ ሦስት ትልሞችን ረቂቅ ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙን አመልክቷል፡፡

ከቀጣናዊ ትስስርን በሚፈልጉ አጎራባች አገሮችና ሌሎች የኢትዮጵያ ምርቶችን ከሚቀበሉ አገሮች ጋር ግንኙነት ከመፍጠር አንፃርም ከኬንያና ከሶማሊያ ጋር አራት የተቀላጠፈ የንግድ ስምምነትን በማካሄድ የሚፈራረም ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡  ከሶማሊያ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ጋር ከዚህ በፊት ነበረውን ድርድር በመቀጠል ዕቅድ መያዙንም በዚህ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡ የሚኒስቴሩ ሌላው የትኩረት መስክ በውድድር ላይ የተመሠረተ ፍትሐዊና ዘመናዊ የንግድ አሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት ንግድን ማስፋፋት እንደሆነ የሚገልጸው የመሥሪያ ቤቱ ዕቅድ ዋጋን ማረጋጋትና የሸቀጣ ሸቀጦች አቅርቦትና ሥርጭት በተመለከተ፣ የበጀት ዓመቱ ትኩረት የምሰጠው ሥራዬ ነው ብሏል፡፡ ከዚህ አኳያ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን አቅርቦትና ሥርጭት ውጤታማነት ለማረጋገጥ እሠራዋለሁ ያለው ሥራ በመድረኩ ማብራሪያ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡  

ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና የመሳሰሉትን ምርት ችግሮችን፣ በተለይ በአብዛኛው ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል እንዲያገኝ በማድረግ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተሰጠው ማንዴት መሠረት ከሦስት ምንጮች መንግሥት ከሚመድበው የውጭ ምንዛሪ፣ ከልማት ድርጅቶች ከሚቀርቡ ምርቶችና ከፍራንኮ ቫሉታ ነጋዴዎች ቀረጥ እንዲያስገቡ ተደርጎ ሥርጭቱ እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡  

ይህ ሥርጭት ፍትሐዊ እንዲሆነ የሚከታተል መሆኑንም ገልጿል፡፡ በመሆኑም በበጀት ዓመቱ ወደ 147 ሚሊዮን ሌትር የምግብ ዘይትና 3.3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር በፍትሐዊ መንገድ እንዲሠራጭ ክትትል አደርግበታለሁ ብሏል፡፡

ሌላው የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ከተያዙ ዕቅዶች ውስጥ አንዱ አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ የቅዳሜና የእሑድ ገበያዎችን ማስፋፋት ነው ተብሏል፡፡ ከቀረበው ገለጻ መረዳት እንደተቻለው በ2014 ዓ.ም. በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተፈጠሩትን 160 የቅዳሜና የእሑድ ገበያዎች ቁጥር በዚህ ዓመት 1,000 ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን አቶ ዑርጌሳ ገልጸዋል፡፡

ይህ ክንውን ዝቅተኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በቀጥታ ከሻጩ ጋር እየተገናኘ ግብይቱን እንዲያካሂድና በተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችላል ተብሎ የሚተገበር እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ እነዚህንና ሌሎች ለመሥራት በዕቅድ የያዛቸውን ሥራዎች ለመተግበር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የውስጥ አሠራሩን በማስተካከል ጭምር የሚተገብራቸው ናቸው፡፡ የአገልግሎት አሰጣቱን ማሻሻል፣ የመሥሪያ ቤቱን የአሠራር ውጤታማነት በማሻሻል ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመለወጥ እየሠራ ነው ተብሏል፡፡ ውጥኑንም ዕውን ለማድረግ ሦስት ፖሊሲዎች እንደ ስትራቴጂ እንዲፀድቁ ክትትል ማድረግ፣ ሰባት አዋጆች፣ ሰባት ደንቦች፣ 13 መመርያዎች ደግሞ በሚኒስቴሩ የሚፀድቅና በፍትሕ ሚኒስቴር ተመዝግቦ ተግባራዊ እንዲሆኑ የመከታተል ሥራ ይሠራልም ተብሏል፡፡

ሚኒስቴሩ ዘመናዊ አሠራር ከማጎልበት አንፃር እየሠራቸው ካሉ ሥራዎች መካከል የኦንላይን የንግድ መዝገባ አንዱ ነው፡፡ ይህ የኦንላይን የንግድ ምዝገባ አገልግሎት በ2013 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ 7,000 አካባቢ የሚሆን የንግድ ኅብረተሰብ በኦንላይን ምዝገባ አካሂዶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ ሚኒስትር ደኤታው እንደገለጹት ደግሞ፣ አሁን ግን የአገልግሎቱ ቁጥሩ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ኅብረተሰቡ ከሲስተም ጋር እንጂ፣ ከሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረው፣ እንዲሁም የአሠራር ብልሽቶችን ለመቆጣጠር ሰው ባለበት ቦታ ሆኖ ንግድ ፈቃድ ማውጣትና ማደስ እንዲችል ጭምር ታስቦ የተዘረጋ አሠራር መሆኑንም ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በተሠራው ሥራ በ2014 ዓ.ም. በአንድ ዓመት በኦንላይን ምዝገባ ያካሄዱትን 27,000 ማድረስ ተችሏል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ሩብ ዓመት ደግሞ ከ215 ሺሕ በላይ በኦንላይን ሲስተም እንዲመዘገቡ ማድረግ መቻሉን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸዋል፡፡ ይህንን ዘመናዊ አሠራር የሚያሳደጉ ሥራ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የኦንላይን ምዝገባን በተመለከተ በተያዘው ዕቅድ መሠረት በዚህ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚሰጠው 2.74 ሚሊዮን ምዝገና ፈቃድ ከአገልግሎት ውስጥ 50 በመቶውን 1.37 ሚሊዮን የሚሆነውን በቀጥታ በኦንላይን የፈቃድና ምዝገባ አገልግሎትን እንዲያገኝ ታቅዷል፡፡ ይህ ቀደም ብሎ ሦስት በመቶ ነበር፡፡ በዚህ በጀት ዓመት ግን ወደ 50 በመቶ ማድረስ እንደሚቻል ታምኖ ይህንን ለመተግበር እየተሠራ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ አገልግሎት ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ዑርጌሳ፣ በወረደ ኔት ያልተሳሰሩ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ መስጪያ ጣቢዎችን ከወረደ ኔት ጋር በማስተሳሰር ሙሉ ለሙሉ አቶሚክ እንዲሆኑ በማድረግ አገልግሎት ፈላጊዎች ካሉበት ቦታ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚሠራ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከዋና ዋና ተግባሮቹ መካከል የወጪ ንግድን ለማስፋፋትና ለማሳደግ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአሥር ዓመት ዕቅዱን በተመለከተ የተሰጠው ማብራሪያ በ2022 የአገሪቱ የወጪ ንግድ 17.8 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ዕቅድ ተይዟል፡፡

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተቋማት ለውጥ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ባይከዳኝ እንዳመለከቱት፣ በወጪ ንግድ ረገድ በአሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ በመሥሪያ ቤቱ እንደታቀደው ለማስፈጸም አጋዥ ይሆናሉ የተባሉ ተግባራት ይፈጸማሉ ብለዋል፡፡

የወጪ ንግድ ገቢውን ለማሳደግ መሥሪያ ቤቱ እተገብራቸዋሁ ብሎ ከያዛቸው መካከል የወጪ ምርት መዳረሻ አገሮችን አሁን ካለበት 40 አገሮች በዘጠኝ ጨምሮ 49 ማድረስ የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ አራት አዳዲስ ምርቶች ወደ ዘመናዊ ግብይት ማስገባት፣ ሦስት የወጪ ንግድ ምርቶችን በቀጥታ ግብይት ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ የመሳሰሉ ተግባራት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኃላፊነት እንዲከናወኑ በማድረግ የወጪ ንግድ ገቢ እንዲያድግ እንደሚደረግ ተጠቅሷል፡፡ በዕቅዱ መሠረት በ2022 ይደረስበታል ከተባለው የወጪ ንግድ ገቢ 6.68 ቢሊዮን ዶላሩ ከግብርና ዘርፍ ይገኛል ተብሎ የታቀደ ነው፡፡

በ2015 የበጀት ዓመትም አገሪቱ ከወጪ ንግድ ታገኛለች ተብሎ የታቀደው 5.24 ቢሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሲሳይ በበኩላቸው፣ በ2015 የመጀመርያ ሩብ ዓመተ 959.7 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አመልክተዋል፡፡

ከዋጋ ቁጥጥር አንፃር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያለበትን ኃላፊነት በተለያየ መንገድ ይወጣል ተብሏል፡፡

አንዳንዴ አንደር ኢንቮይሰ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኦቨር ኢንቮይስ በማድረግ ሥራዎች የሚሠሩ በመሆኑ፣ ይህንን በትክክለኛ ዋጋ መሸጣቸውን ሥርዓት በመዘርጋት የመቆጣጠሩን ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ቁጥጥር ይሠራል፡፡ ይህንንም የማስተባበር ሚና አለው ተብሏል፡፡ ዕቃዎች በትክክለኛ ዋጋቸው መሸጣቸውን ብቻ ሳይሆን ለኅብረተሰቡ ወሳኝ የሆኑ የፍጆታ ዕቃዎች ዕጥረት ካለባቸው ደግሞ እያጠና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የማቅረብና ሲወሰን ዋጋ ወስኖ በዚያ ዋጋ መሸጡንና የመቆጣጠር ሥራ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስለመሆኑም በመድረኩ ላይ ተጠቅሷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች