Sunday, April 14, 2024

ጦርነቱ እንዴት ሊቋጭ ይችላል?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁሉም አቅጣጫዎች የበላይነቱን በያዘበት በዚህ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና ሌሎችም የውጭ አካላት በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቁ ነው፡፡ ጦርነቱ በሰላም ብቻ ነው ሊፈታ የሚችለው ሲሉ የሚደመጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ተፋላሚዎቹ የአፍሪካ ኅብረት ወደ ሚመራው ድርድር እንዲመለሱ ጠይቀዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት  ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማሀማት ይህን የሚደግፍ መግለጫ ያወጡ ሲሆን፣ ያለ ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም ተደርጎ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት እንዲጀመርም ጠይቀዋል፡፡

የቱርክ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት መራሹ ድርድር ብቸኛው የጦርነቱ መቋጫ መሆኑን ገልጿል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማትና ተራድኦ ድርጅት (USAID) ኃላፊ ሳማንታ ፓወር፣ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች ጦርነቱን አስመልክቶ በርካታ አስተያየቶች ሲሰጡ ነው የከረሙት፡፡ ከአሜሪካ ውጭ ግንኙነት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ጀምሮ፣ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ የአፍሪካ ጉዳይ ቢሮ፣ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ጦርነቱ እንዲቆም የሚጠይቅ መግለጫዎችን አከታትለዋል፡፡

የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ግሪጎሪ ሚክስ፣ እንዲሁም የሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ ከጦርነቱ መቆም ባለፈ በኤርትራና በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጣል የሚጎተጉት መግለጫ ሲሰጡ ነበር፡፡

አሜሪካ በዚህ ብቻ ሳይሆን ከእንግሊዝ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከዴንማርክ፣ ከጀርመንና ከኔዘርላንድስ መንግሥታት ጋር በጋራ በመሆን ጦርነቱን ለማስቆም የሚረዳ ያለችውን ግፊት ስታደርግ ነው የከረመችው፡፡

የአውሮፓ ኅብረትም ይህን ጫና የማድረግ ዕርምጃ የተቀላቀለ ሲሆን፣ የኅብረቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ጠንካራ መግለጫዎችን በተከታታይ ሲሰጡ ነበር፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA)፣ እንዲሁም የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና ሌሎች የሰብዓዊ ረድኤት ተቋማት በየፊናቸው ጦርነቱ በአስቸኳይ ካልቆመ የሚል ግፊቶችን ሲያካሂዱ ነው የሰነበቱት፡፡ ካናዳና ኖርዌይን ጨምሮ በየአቅጣጫው ጦርነቱ ይቁም የሚለው ግፊት ጨምሯል፡፡

በየአቅጣጫው ጦርነቱ ይቁም የሚለው ግፊት ቢያይልም፣ ሆኖም ጦርነቱ እንዴት እንደሚቋጭ የሚያረጋግጥ መረጃ ማግኘት አሁን ከባድ የሆነ ይመስላል፡፡ ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ ድርድርና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲጀመር የሚወተውተው ኃይል በዝቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድርድሩ ዳግም መመለስ ስለሚችልበት ዕድል ማረጋገጫ የሚሰጥ ወገን ማግኘት አይቻልም፡፡

የሕወሓት ኃይሎች አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀዋል፡፡ ግጭቱ በአስቸኳይ ቆሞ የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ ክልል ከወጡ ድርድሩን ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ነው ሕወሓቶች በመግለጫ የተናገሩት፡፡

ይህ በምዕራባውያን ሚዲያዎች፣ ተቋማትና መንግሥታት ሲወደስ የቆየ የሕወሓቶች አቋም ግን መንግሥት ከያዘው አቋም ጋር የሚታረቅ መሆኑን የሚጠራጠሩ በርካታ ናቸው፡፡ መንግሥት ሰኞ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው መግለጫ መሠረት በትግራይ የሚገኙ የፌዴራል ተቋማትን መከላከያ ተቆጣጥሮ እንደሚቆይ ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንደግፋለን ሲሉ የቆዩት ምዕራባውያኑ ሕወሓትን ደግፈው የኢትዮጵያ ጥምር ጦር ከትግራይ ካልወጣ የሚል አቋም ያንፀባርቃሉ? ወይስ ሲሉት እንደቆዩት የኢትዮጵያን ሉዓዊነትና የግዛት አንድነት እናከብራለን በሚለው አቋማቸው ይፀናሉ? የሚለው ጥያቄ ምላሽ  በጉጉት እየተጠበቀ ነው፡፡

መንግሥት በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ሕጋዊ መብቱን ተጠቅሞ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱ ተገማች ብቻ ሳይሆን እርግጥ የሆነም ይመስላል፡፡ መንግሥት ትናንት ባወጣው መግለጫ እንደ ሽሬ፣ አላማጣና ኮረም የመሳሰሉ ከተሞች በመከላከያ ሥር መግባታቸውን አረጋግጧል፡፡ ይህ የመከላከያ ግስጋሴ በምዕራባውያኑ ተከታታይ መግለጫ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫናና ግፊት ይገታ ይሆን ወይ የሚለው ጥያቄ ብዙ እያነጋገረ ነው፡፡ ጫናው የመከላከያን ግስጋሴ ማስቆም ብቻም ሳይሆን፣ የሕወሓትን የመጨረሻ እስትንፋስ ይታደግ ይሆን ወይ የሚለው በሰፊው እያጠያየቀም ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ተቋም ተመራማሪ ሳሙኤል ተፈራ (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ጦርነቱ አሁን ከሕወሓቶች ቁጥጥር ውጪ መውጣቱን ይናገራሉ፡፡ የሕወሓቶች እጅ መስጠትም ሆነ አለመስጠት፣ ለመደራደር ዝግጁ መሆንም ሆነ አለመሆን የጦርነቱን ገጽታ እንማይቀይረው ይገልጻሉ፡፡ በእሳቸው እምነት የምዕራባውያኑ ጫናና ግፊትም ቢሆን የጦርነቱን የኃይል ሚዛን ፈፅሞ አይቀይረውም፡፡

‹‹ወደ ድርድር ቢመጣ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ለመደራደር ተደራዳሪዎች አንዳቸው በሌላኛው እጅ ላይ የሚፈልጉት ነገር መኖር አለበት፤›› ሲሉ የሚያስረዱት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ በሕወሓት እጅ መንግሥት የሚፈልገው ነገር ያለ አይመስልም ይላሉ፡፡

‹‹ያኔ ቆቦን በያዙ ወቅት ወይም ከዚያ በፊት ቢሆን ኖሮ ድርድር መባሉ ትርጉም ይሰጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር አልቆ በተከበቡበት ሁኔታ እንደራደር ማለቱ ትርጉም የለውም፤›› ሲሉ ነው ተመራማሪው የሚናገሩት፡፡ የደቡብ አፍሪካው ድርድር ሊካሄድ ነበር በተባለ ወቅት የሕወሓት ደጋፊ ናቸው የሚባሉት ኸርማን ኮህን ጻፉት የተባለውን ያስታወሱት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር) ‹‹ሕወሓቶች ያኔም ከድርድሩ ሊያገኙ የሚችሉት ሰላማዊ መውጫ መንገድ ነው ብለው ነበር፤›› በማለት ይጠቅሱታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም፣ ‹‹ድርድሩ ምን ሰጥቶ ለመቀበል ነው የሚደረገው?›› በማለት የሚጠይቁት  ተመራማሪው፣ የጦርነቱ ሚዛን ፍፁም ወደ መንግሥት ያጋደለና የጨዋታውንም ሕግ የሚወስነው እሱ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡

የጦርነቱን ሒደት በቅርበት የሚከታተሉት በሱዳን የቀድሞ የዩኤንዲፒ ባልደረባና የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ተሟጋች አቶ ተስፉ የሺወንድም በበኩላቸው፣ ሕወሓቶች ከእንግዲህ ውጊያ በማድረግ የሚያቆሙት ኃይል እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ጦር በሁሉም ግንባር እየገሰገሰ ነው፣ የመልቀም ሥራ እንጂ የቀረው ሊያቆሙት አይችሉም፤›› ብለዋል፡፡

የጦሩ አገባብም ያለፈውን ስህተት በማይደግም መንገድ ነው የሚሉት አቶ ተስፉ፣ ‹‹ጦሩ ከራሱ ኮሸሮ (ብስኩት) ጀምሮ ለሕዝቡ ድጋፍ እየሰጠ ነው፡፡ ከየከተማው ወጥቶ የነበረው ሕዝብ መመለስ ጀምሯል፡፡ ሕወሓትን የሚቃወመውም ሰው እየበረከተ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

መንግሥት ማክሰኞ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫም መከላከያ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች አስቸኳይ የረድኤት አቅርቦት እንደሚጀመር መግለጹ ይታወሳል፡፡ የመንግሥት መግለጫ አክሎም በተያዙ ቦታዎች መሠረታዊ አገልግሎት ለመጀመር መታቀዱንም ይጠቅሳል፡፡

ጦርነቱ በሁለቱም ወገን ቀላል የማይባል ጉዳት እንደሚያደርስ ያመለከቱት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ‹‹በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሕዝቡ ሕወሓትን ሲቃወምና በቃን ሲል እንሰማ ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡ ይህን ደጋፊ ሐሳብ ያንፀባረቁት አቶ ተስፉ በሕወሓት ላይ ሕዝባዊ እምቢተኝነት መጠናከሩን ነው ያመለከቱት፡፡

የጦርነቱ ሒደት ይህ እንደሆነ ቢነገርም ምዕራባውያኑ ግን ጫናቸውን መቀጠላቸው ነው የሚታየው፡፡ ይህን በተመለከተ የተጠየቁት አስተያየት ሰጪዎቹ ግን የምዕራባውያኑ ጫና ሕወሓትን ከሽንፈት የመታደግ አቅም እንደማይኖረው ነው ግምታቸውን የሚናገሩት፡፡

‹‹የጦርነቱ ትኩሳት እየጨመረ ሲመጣ ምዕራባውያኑ ጩኸታቸውን መጨመራቸው የተለመደ ጉዳይ ነው፤›› የሚሉት ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ይህ ደግሞ ሕወሓትን የመታደግ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ የማድረግ ፕሮጀክታቸው አካል እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ምዕራባውያኑ በኢትዮጵያ የእነሱን አቋም የሚያስፈጽም መንግሥት እንዲቀመጥ መፈለጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

አቶ ተስፉ በበኩላቸው፣ ‹‹ምዕራባውያኑ ከዲፕሎማሲ፣ ከሚዲያና ከፖለቲካ ጫና ባለፈ በቀጥታ ጣልቃ ገብተው ሕወሓትን ከሽንፈት ሊታደጉ የሚችሉበትም ሆነ የጦርነቱን ሚዛን የሚቀይሩበት ዕድል የለም፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

ምዕራባውያኑ ለማድረግ የሚፈልጉት ጫና የኢትዮጵያን ችግር ከማባባስ ባለፈ የፈጠረው በጎ ተፅዕኖ አለመኖሩን ነው በብዙዎች የሚነገረው፡፡ ከሰሞኑ በባህር ዳር ከተማ ለሦስት ቀናት በተካሄደው የጣና ፎረም ላይ ይኸው ስሜት ነበር የተንፀባረቀው፡፡

በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና የአሜሪካ  የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር በተከራከሩበት የፓናል ውይይት ላይ የምዕራባውያን ጫናና ጣልቃ ገብነት ላለፉት 40/50 ዓመታት በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ያመጣው አንዳችም በጎ ለውጥ አለመኖሩን አቶ ኃይለ ማርያም ለማይክ ሐመር በቀጥታ መናገራቸው ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ነበር የከረመው፡፡

‹‹የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊ መፍትሔዎች መፈታት ይችላል›› የሚለው ብሂል ጎልቶ እየተደመጠ ባለበት በዚህ ወቅት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአፍሪካ ኅብረት ያደራድረን የሚለውን አቋሙን አለመቀየሩን ነው የገለጸው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ‹‹የአፍሪካ ኅብረት የድርድሩን ቀን እስኪያሳውቀን እየጠበቅን ነው፤›› በማለት ማክሰኞ ዕለት መግለጻቸው ይህንኑ የመንግሥትን የድርድር ፍላጎት አለመለወጥ ያመለክታል ተብሏል፡፡

አሁን ለትግራይም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያ የሚበጀው ሰላም እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ጦርነቱ በአስቸኳይ ካልቆመ አገሪቱ አደጋ ውስጥ እንደምትወድቅ የሚናገሩ በበረከቱበት በዚህ ወቅት ደግሞ፣ ሕወሓትም ሆነ መንግሥት ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው፡፡

መቀመጫቸውን በጋና አክራ ያደረጉት የሰላምና የደኅንነት ባለሙያ አዲብ ሳኒ፣ ‹‹ሁለቱ ወገኖች ማለትም መንግሥትም ሆነ ሕወሓት ለሰላም ቁርጠኛ እስካልሆኑ ድረስ፣ አሥር ሺሕ ጊዜ ስለሰላም ቢወራ በኢትዮጵያ ሰላም ሊፈጠር አይችልም፤›› ሲሉ ነበር ለዶቼ ቬሌ እንግሊዝኛው የተናገሩት፡፡ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዩክሬን እንዳደረጉት ሁሉ ለኢትዮጵያም ትኩረት ሰጥተው ግፊት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ለሁሉም ጥሩ ሰላም ነው›› ሲሉ የሚናገሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ሳሙኤል (ረዳት ፕሮፌሰር) ግን፣ ሰላም ሁልጊዜ በምዕራባውያን ጫና ወይም በድርድር ብቻ ይገኛል ማለት እንዳልሆነ አመልክተዋል፡፡

‹‹ልለው ባልፈልግም ጦርነቱን በአስቸኳይ መቋጨትና በየትኛውም መንገድ ሰላምን የማስፈን መንግሥት ኃላፊነት አለበት፤›› ሲሉ የገለጹት ምሁሩ፣ ዲፕሎማሲያዊ ጫናውን ለመቋቋምም ከዚሁ ጎን ለጎን ከባድ ትግል እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር እንደ መሆኗ መጠን፣ በሰብዓዊነትና ሰላም በማስፈን ስም በውስጥ ጉዳይዋ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ የምዕራባውያን ሙከራዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ብዙዎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አቋማቸውን በግልጽ እያሳወቁ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -