Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

የዘመናችንን ነገር ሳስብ ወደኋላ ተመልሼ አንዳንድ ነገሮችን እንዳስታውስ ያደርገኛል፡፡ የዘመኑን ወፈፌዎችን ማስቆም የሚቻለውም በዚህ መንገድ ስለሆነ እንዲህ አንብቡልኝ፡፡ በፊውዳሎቹ ዘመን ‹ልጅህን ለልጄ› በመባባል የጋብቻ ቁርኝት የሚደረገው ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ የሀብት መጠንን፣ ማኅበራዊ ትስስርንና ጥቃትን ለመመከት የሚያስችል ጉልበትን ታሳቢ እንደነበር አሁንም የሚያስታውሱ ሲኖሩ፣ የተለያዩ የጽሑፍና የቃል ውርሶች ያስረዳሉ፡፡ በቤተ መንግሥት አካባቢ ደግሞ ጋብቻ ከፍ ብሎ ለፖለቲካ መሣሪያነት ስለሚያገለግል፣ ከተለያዩ ብሔረሰቦች ጋር ተጋብቶ መዋለድ ዙፋኑን ለማርጋትና በዘለቄታነት ለማስቀጠል ይረዳ እንደነበር ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት ‹የቤተ መንግሥት ጋብቻ› ወደ ታች ዝቅ እያለ መሣፍንትና መኳንንት ከተለያዩ ብሔረሰቦች አቻዎቻቸው ጋር በጋብቻ እየተቆራኙ፣ መስተጋብሩን ሲያሰፉት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ የሕዝብ እንቅስቃሴ ስለነበር፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የብዙ ብሔረሰቦች ቅይጥ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በጋብቻ መተሳሰራቸው፣ ጉዲፈቻን በመሳሰሉት መዛመዳቸውና በሚያስገርም ውህደት ተቃቅፈው መኖራቸው በዘመናት ቅብብሎሽ በትውልዶች ውስጥ በተደጋጋሚ የታየ የሰው ልጆች የከፍታ ማመላከቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የተገነባው በዚህ ታላቅ እሴት ነው፡፡

በአንድ ወቅት ሁለት በዘመናቸውም ሆነ በአኗኗር ዘይቤያቸው የማይመሳሰሉ፣ ነገር ግን በኢትዮጵያዊነት የጋራ እሴት ላይ ተመሳሳይ ምልከታ ያላቸው ብርቱ ኢትዮጵያዊያን የተናገሯቸው ቁምነገሮች መቼም ቢሆን አይዘነጉኝም፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ሊቃውንት የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ከበቀሉ ምርጥ ምሁራን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚታወሱ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ በርካታ መጻሕፍት በመጻፍና በመተርጎም ምዕመናንን በዕውቀት ሲያንፁም ይታወቁ ነበር፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል፣ ለጊዜው ስሙን ከዘነጋሁት መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አስገራሚ ነገር ተናግረው ነበር፡፡ በወቅቱ የብሔር ፖለቲካው ጦዞ ስለነበር ስለዚህ ጉዳይ ተነስቶላቸው፣ አንድ ምሳሌ አነሱ፡፡ ለሆነ ጉዳይ መታወቂያ አስፈልጓቸው የሚኖሩበት ቀበሌ ይሄዳሉ፡፡ ያገኙት ሹም መታወቂያቸውን ሊሰጣቸው መረጃ እየጠየቃቸው ሳለ ብሔር ጋ ሲደርስ ምንድነዎት ሲላቸው፣ ኢትዮጵያዊ ይሉታል፡፡ እሱም ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ብሔር ነው የሚሞላው ብሎ ጠንከር ሲልባቸው፣ ‹‹በል እንግዲህ ሙላው፣ እኔ ዝቅ ሲል ጎጃሜ ከፍ ሲል ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ ካልሆነ ግን ተወው…›› ብለው እንደሄዱ ገልጸው፣ ኢትዮጵያዊነትን ዝቅ በሚያደርግ ነገር እንደማይደራደሩ መናገራቸው ትዝ ይለኛል፡፡

ሌላው አይረሴው ኢትዮጵያዊ ዝነኛው የሕግ ባለሙያ፣ ፖለቲከኛና ጸሐፊ አቶ አሰፋ ጫቦ ናቸው፡፡ አቶ አሰፋ በሽግግሩ ቻርተር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች እንዲካተቱ፣ በብርቱ ተሟግተው የተሳካላቸው ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ በተባ ብዕራቸው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የጻፏቸው በበርካቶች ዘንድ በፍቅር የተነበቡላቸው የዘመናችን ዕንቁ ነበሩ፡፡ በአንድ ወቅት ‹‹ጋሞነቴና ኢትዮጵያዊነቴ ተምታተውብኝ አያውቁም›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ በበርካቶች ከፍተኛ አክብሮት አጎናፅፏቸው ነበር፡፡ እኚህ ምሁር የበቀሉበት የጋሞ ማኅበረሰብ በአገራችን ውስጥ እየተለገሰው ያለውን ክብር ስናይ፣ የጋሞ አባቶችና እናቶች ለኢትዮጵያዊነት የሰጡትን ዋጋ ስናስተውል፣ እንዲሁም ልጆቻቸውን እንዴት አድርገው በአገር ፍቅር ስሜት ኮትኩተው እንዳሳደጉ ስናስብ አቶ አሰፋና መሰሎቻቸው መቼም ቢሆን ከህሊናችን አይጠፉም፡፡ አለቃ አያሌውና አቶ አሰፋ ዛሬ በአፀደ ነፍስ ቢሆኑም፣ ታሪክ ሲዘክራቸው ከሚኖሩ ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን ተርታ እንደሚሠለፉ አልጠራጠርም፡፡

ኢትዮጵያዊነት ክብር ነው ስንል ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ተጋምደው የኖሩባቸው እሴቶች እጅግ በጣም አኩሪ በመሆናቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘናት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ ታፍራና ተከብራ የኖረችው፣ እነዚህ ኢትዮጵያዊያን እጅግ አስገራሚ በሆነ መስተጋብር ድርና ማግ ሆነው ስለሚኖሩ ነው፡፡ አንድ ቤተሰብ ውስጥ ቄስ፣ ሼኪና ፓስተር ወንድማማች ሆነው የሚኖሩባት ብርቅዬ አገር ኢትዮጵያ መሆኗ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ክርስቲያን፣ እስላም፣ ዋቀፈና፣ አይሁድና ሌሎች ልዩነቶቻቸው እስከማያስታውቁ ድረስ አብረው የሚኖሩባት ድንቅ አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህ ለዘመናት እንደ ሠርገኛ ጤፍ ተደባልቆ የሚኖር ሕዝብ በአስተዋይነቱ፣ በአርቆ አሳቢነቱና በሥነ ምግባሩ ምሥጉን ለመሆኑ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ይህንን እንደ ቅኔ ሰምና ወርቅ የሆነ ሕዝብ እንኳንስ ለመነጣጠል ቀርቶ ለማሰብ በጣም አዳጋች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ማለት ይህች ናት፡፡

የጣሊያን ፋሽስቶች በዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች፣ ታንኮች፣ መድፎች፣ በቡድንና በነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች በመታገዝ በዘመኑ ውትድርና ጥበብ የሠለጠነ ሠራዊታቸውን ይዘው፣ ይህም አልበቃ ብሏቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከለከለ የመርዝ ጋዝ ተጠቅመው ቢወሩንም፣ በአስደናቂ ጀግንነት በአርበኞቻችን ተጋድሎ ፋታ አሳጥቶ በመጨረሻም ማባረር የተቻለው በኅብረ ብሔራዊነታችን ነው፡፡ ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን ሲቀራመቱ ከቅኝ ተገዥነት የተረፍነው ከዳር እስከ ዳር ድንበራችንን በጋራ ስለጠበቅን ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ እንኳንስ ኢትዮጵያዊነታችን የዋሆች በዚህ ወቅት የሚመኩበት ብሔረሰባዊ ማንነት በቅኝ ገዥዎች ተፍቆ ነበር፡፡ ስያሜዎቻችን ሳይቀሩ አልቤርቶ፣ ስሚዝ፣ ጆንሰን፣ ማርጋሬት፣ ጁሊ፣ ሉቺያ፣ ወዘተ ሆነው በበታችነት ስሜት እንኖር ነበር፡፡ ጥንታዊያኑ ኢትዮጵያዊያን በአስተዋይነታቸውና በጀግንነታቸው ያቆዩልንን ክብርና ማዕረግ ማስጠበቅ የምንችለው፣ አሁንም ታፍረንና ተከብረን እየኖርን አገራችንን ተባብረን ስናሳድግ ብቻ ነው፡፡

ከዚያ ውጪ በማንነት ቀውስ ወይም በበታችነት ስሜት እየናወዙ ይህንን በልዩ ጥበብ የተሸመነ ኢትዮጵያዊ ማንነት መገዳደር ለጊዜው የሞኞችን ጭብጨባ ቢያስገኝም፣ ይዋል ይደር እንጂ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ለሥልጣን፣ ለገንዘብና ለዝና ሲሉ አገር የሚያውኩ በብሔርተኝነት ያበዱ ጅሎች ለጊዜው ቢያሽካኩም፣ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ ወገኖች ግን ካሁኑ ለካ እንዲህ ነው ነገሩ እያሉ የሴራውን ምንጭ እያማተሩ ነው፡፡ ውስጥ ለውስጥ ተዶልቶ የዋሆችን ወይም ጅሎችን በአደባባይ ማስለፍለፍ ሚሊዮኖችን ምን ያህል እንዳሳመመ፣ በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያዊያንን ለማሸማቀቅ የተዶለተ ሴራ እንደሆነ መታወቁ ግንዛቤ ካልተገኘ፣ ከዚህ ሴራ በስተጀርባ ያሉ ፖለቲከኛ ነን ባዮች በእርግጥም ጊዜያዊ የበላይነት ስሜት ወፈፍ አድርጓቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ወፈፌነት ግን አይዘልቅም፡፡ አገሪቱ ኢትዮጵያ ናትና፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከዚህ በፊት የተከበሩ ሳይቀሩ በሕዝብ ተጠልተው እንዴት ፅዩፍ እንደሆኑ ለሚታዘብ ነገሩ ግልጽ ነው፡፡ በሕዝብ መተፋት መዘዙ ከባድ ነው፡፡ የደረሰባቸው ምን ያህል ተሰብረው እንደተጣሉ እናውቃለን፡፡ አንገታቸውን ደፍተው፣ ለሥነ ልቦና ቀውስ ተጋልጠውና ከማኀበረሰቡ ተገልለው ቀፎ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ትናንት ሕዝብ ያከበራችሁ ዛሬ ቀትረ ቀላል ሆናችሁ ብቻችሁን እየቆማችሁ ነው፡፡ ጥቅም ፈላጊ አጃቢዎቻችሁ ታኝኮ እንደተጣለ ሸንኮራ መሆናችሁን ሲያዩ ተሸብልለው ወደ አዲስ ተጫራች ይሄዳሉ፡፡ ያኔ ምነው በቀረብኝ እያሉ ጥርስን ማፋጨት ዋጋ የለውም፡፡ የእናንተ ቢጤዎች ከዚህ በፊት ከስረው ማንም አይዞህ ወይም አይዞሽ አላላቸውም፡፡ አሁን ልብ መባል ያለበት ግን ኢትዮጵያዊያን ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከትግራይ፣ ከጉራጌ፣ ከወላይታ፣ ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከሐረሪ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ወዘተ. ብሔር ብሔረሰቦቻችን የተደበላለቅን ነን፡፡ ማንም ተላላኪ ወፈፌና ከበስተጀርባው ያለ ከታሪክ የማይማር አፍለኛ፣ ይህንን መስተጋብር መሻርም ሆነ መቀልበስ አይቻለውም፡፡ እሞክራለሁ ብሎ የሚገፋ ካለም የሚያተርፈው ውርደት ነው፡፡ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ውርደት፡፡

(አጥናፉ ቢረጋ፣ ከወልቂጤ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...