Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየውጭ ባንክና የገንፎ ድስት - የምጣኔ ሀብታችን ለውጭ የገንዘብ ተቋማት ክፍት መሆኑ...

የውጭ ባንክና የገንፎ ድስት – የምጣኔ ሀብታችን ለውጭ የገንዘብ ተቋማት ክፍት መሆኑ አንድምታ (ክፍል አንድ)

ቀን:

በዕፁብድንቅ ስለሺ (ዶ/ር)

የትኛውም ስለሚጠቅም ነገር የሚደረግ የግለሰብም ይሁን የድርጅት ወይም አገራዊ ውሳኔ፣ ሁልጊዜ ይዞት የሚመጣ ተጓዳኝ የሚከፈል ዋጋ አለው። እንደ ምሳሌ  አንድ ለአካለ መጠን የደረሰ ሰው ጊዜውን ትምህርት ላይ ለማሳለፍ ሲወስን ለትምህርት ገንዘብ ከማውጣቱ በተጨማሪ፣ ጊዜውን በሌላ ሥራ (የትምህርት ዓይነት) ላይ አውሎት ቢሆን ኖሮ የሚያገኘውን ገቢና የሚያፈራውን ሀብት ያጣል። በሥራ የተሠማራው በፈንታው ሊያካብት የሚችለው መደበኛ ዕውቀት ያልፈዋል። የሰው ልጅ እንደ ግል፣ አገር እንደ ማኅበር የጊዜ ውስንነትና የሀብት እጥረት አለባቸውና በአንድ ጊዜና በጥቂት ሀብት ብዙ ተግባር ለማከናወን ስለማይቻል፣ ሁልጊዜ ውሳኔዎች በሌሎች አማራጮች መስዋዕትነት የሚቆሙ ናቸው።

ይህን ጉዳይ ማንሳቴ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀባይነት ያገኘው የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ከሚፈቅደው ረቂቅ ጋር ተያይዞ፣ ሐሳቦች እዚህም እዚያም ሲነሱ በማየቴና በመስማቴ ነው። የውጭ ባንኮች የሚኖራቸው የባለቤትነት ድርሻና የሚሰጧቸው የአገልግሎት ዓይነቶች ውስን እንደሆኑ፣ የረቂቁን ዝርዝር ጽሑፍ ያዩ ሰዎች ጽፈዋል። ያም ሆነ ይህ በጊዜ ሒደት የኢትዮጵያ ገበያ ሳቢ ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ባንኮች በልበ ሙሉነት ለመወዳደር ሲበቁ፣ የአክሲዮንና የውጭ ምንዛሪ ገበያው ሲዳብር፣ ገንዘባዊው ክፍለ ምጣኔ ሀብት በደንብ መከፈቱ አይቀርምና ከዚህ ጋር ተያይዞ ያሉትን አተያዮች፣ ሙግቶችና ተሞክሮዎች  ለመዳሰስ እሞክራለሁ (በክፍል አንድ አተያዮችን ብቻ እዳስሳለሁ)፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ለውጭ የገንዘብ ተቋማት ክፍት መሆኑ አንድምታው ምንድነው? የገንዘብ ዘርፉ ለውጭ ዓለም ክፍት ይሁን ዝግ የሚለው የሚያከራክር ጉዳይ ሆኖ ይገኛል።  

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ክርክሩ የፖሊሲ አርቃቂና አፅዳቂዎችን፣ እንዲሁም የልማት ሐሳብ አፍላቂዎችን የሚያካትት ነው። ጉዳዩ ባለፉት አርባ ዓመታት በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የክርክርና የውይይት ርዕስ ሆነው ከቆዩት ከአጠቃላይ የመንግሥት ምጣኔ ሀብታዊ ሚና ቅነሳ (Economic Liberalization)፣ ድርጅቶችን ከመንግሥት ይዞታ ወደ ግል ማዘዋወር (Privatization) እና የተንዛዛና ለግሉ ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴ መሰናክል የሚፈጥሩ ደንቦችንና አሠራሮችን የመቀነስና የማሻሻል (Deregulation) ሐሳቦች ጋር የተዛመደ ነው። እነዚህ ዕርምጃዎች በአንድ በኩል  የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ከመንግሥት ጫና መላቀቅና መንግሥትም ራሱ ሕግ አውጭና ራሱ የገበያ ተዋናይ እንዳይሆን የሚከለክሉ ሲሆኑ፣ በሌላ በኩል ደግሞ  ምርትና አገልግሎት፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ያለ ብዙ መሰናክል ከአገር ወደ አገር እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል የታሰቡ ናቸው።

ይሁንና በአደጉ አገሮች የሚገኙ ጠብደል ያሉ ጠብደል ድርጅቶች ለብዙ ዓመታት ልምድ ያካበቱና ለመቆጣጠር በሚያስቸግር ሁኔታ (የግብር አከፋፈል፣ የፖለቲካ ተፅዕኖ…) ስለሚንቀሳቀሱ፣ የደሃ አገሮች ምጣኔ ሀብት ለእነዚህ ጠብደሎች መክፈት ተገቢ አይደለም የሚል ክርክር ሲቀርብ ቆይቷል። ይህ እንግዲህ ስለአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት ዘርፉ ሲሆን፣ በገንዘብ ነክ ተቋማት መግባት ወይም አለመግባት ላይ ያለው ሙግትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ዙሪያ ያሉ አተያዮችን እንደሚከተለው በሦስት ፈርጆች አቀርባለሁ። ይህም ካልደፈረሰ አይጠራም፣ ጎመን በጤናና ጎመን በሥጋ (ት) ይሆናሉ።

   ሀ) ካልደፈረሰ አይጠራም፡- እነዚህ ጫፍ ረገጥና ወደ ሥርዓተ አልበኝነት ማዕዘን የሚጠጉ ሲሆኑ፣ በፖለቲካ ዝንባሌያቸው የመንግሥትን ከግለሰቦች ቀጣና መራቅ፣ በማኅበራዊ ፍልስፍናቸው የግለሰብን ለማኅበረሰባዊ ወግ ደንታ ቢስነት፣ በምጣኔ ሀብት አተያያቸው ምርትና አገልግሎት ድንበር ሳይገድባቸውና ማነቆ ሳይበዛባቸው ከቦታ ቦታ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀሱ የሚሹ ናቸው። አምራችና ሸማች ያለ መንግሥታዊ ሳንካ በፈቃዳቸው ቢገናኙ ሕይወት ይሰምራል ባይ ናቸው።

ከባንኮች መግባት አለመግባት ጋር የሚያያዝ ሐሳባቸው የሚቀዳው ከዚህ ነው። በእነሱ አተያይ ነፃ ንግድ ብቸኛው የሀብትና የድሎት መንገድ ነው። በገበያ የሚከሰቱ የገንዘባዊ ክፍለ ኢኮኖሚ ቀውሶች፣ የገበያ መናጋትና አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ ምስቅልቅሎች ምንጫቸው የመንግሥታት ጣልቃ ገብነት እንጂ፣ ገበያ ራሱ አይደለም ብለው ይከራከራሉ። በነፃ ገበያ ሥርዓት በራሱ የሚፈጠሩ ቁስሎችና ሕመሞች ግን በራሱ በገበያው አካል ውስጥ ባሉ የበሽታ ተከላካይ ኃይሎች (አቅርቦትና ፍላጎት) ታክመው ይድናሉ። የሚወስዱት ጊዜም አጭር በመሆኑ “የውሻ ቁስል” ዓይነት ነው  ባይ ናቸው። መንግሥት ጋውኑን ለብሶ መድኃኒት ልዘዝ ቢል  እንዳታምኑት፣ የሚያዝዛቸው መድኃኒቶች ሁሉ ከበሽታው የባሰ ጉዳት የሚያስከትሉ ናቸው ይላሉ።  

በእነሱ መነፅር የውጭ ባንኮች ሲገቡ ይህን ተከትሎ የሚመጡትን የገንዘብ ዘርፉ መደርጀት፣ ብድርና ቁጠባ ስለሚስፋፋ ንግድ እንዲሳለጥ፣ ምርት እንዲበረክት ስለሚያደርጉ የአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ያድጋል የሚል መሞገቻ ያቀርባሉ። በገንዘብ ተቋማት መካከል ውድድር ስለሚጦፍ አንድም ተገልጋዩ ይጠቀማል (ቆጣቢ ከፍተኛ ወለድ በማግኘት፣ ተበዳሪ ዝቅ ያለ ወለድ በመክፈል) አንድም ቀልጣፋና አትራፊ ያልሆኑ ባንኮች ከገበያው ገለል ስለሚሉ  የሀብት ብክነት ይቀንሳል። ከባንኮች አንፃር ሲታይ ደግሞ የተሻለ ትርፍ ወደ የሚያገኙበት አገር እንደ ልብ መንቀሳቀስና መወዳደር ስለሚችሉ አትራፊነታቸውን ይጨምርላቸዋል የሚል ሙግትም ይታከልበታል። የውጭ ባለ ሀብቶች  ሲገቡ የውጭ ምንዛሪ ይዘው ስለሚመጡ ከዚህ በተጨማሪም ከእነሱ ጋር ትስስር ወይም አመኔታ ያላቸው በአምራች ዘርፍም ይሁን በሌላ፣ በአገልግሎት ዘርፍ ሊሠማሩ የሚችሉ ድርጅቶች አብረዋቸው ይተማሉና ዕድገት ይመጣል ብለው ይሞግታሉ።

እንዲህ ዓይነት አስተሳሰቦች የሚቀነቀኑት ቀድመው ሀብት በሰበሰቡ አገሮች ውስጥ የሚነሱ፣ የትም አገር ሄደን ብንወዳደር ወይም ሌላው እኛ ዘንድ ቢመጣ ማሸነፋችን አይቀሬ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው። ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ብዙም ተቀባይነት የላቸውም። ከእነሱ በተቃራኒ ደግሞ የወ/ሮ ምጣኔ ሀብትን “ያዝ እጇን፣ ዝጋ ደጇን” ብለው መንግሥትን የሚያማክሩ ምሁራንና የፖሊሲ ሰዎች አሉ። እነዚህን “ጎመን በጤና” ልንላቸው እንችላለን።

ለ) ጎመን በጤና፡- በማደግ ባሉ አገሮች ደግሞ (መቼ ይሆን ዕድገታቸውን የሚጨርሱት?) የአጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱን ቧ ብሎ መከፈት፣ በተለይ ደግሞ እንደ ባንክ ያሉ ተቋማትን ለውጭ ባለ ሀብቶች መክፈትን ከፖለቲካ፣ ከፀጥታና ከምጣኔ ሀብታዊ  ሉዓላዊነት አግባብ እያዩ “አናስገባም የውጭ ባንክ፣ እንዳንታወክ” ብለው ሲያንስ በመንግሥት ሥር ባሉ ባንኮች፣ ሲበዛ አገር በቀል በሆኑ የገንዝብ ተቋማት ኃይል ብቻ ምጣኔ ሀብቱን ማሳለጥ እንችላለን የሚሉ ይገኙበታል።  

ከሙግቶቻቸው መካከልም፣ ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር ተያይዞ የገንዘብ ነክ ቀውስ፣ የምንዛሪ ገበያ ቀውስ፣ የገበያ አለመረጋጋትና የአጠቃላይ ምጣኔ ህብታዊ ምስቅልቅል በተደጋጋሚ ይከሰታል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። በተጭማሪም ከውጭ የሚገቡ ባንኮች ብድር የሚያቀርቡት ከፍ ከፍ ላሉና ከውጭ ዓለም ጋር  ግንኙነት ያላቸው ወይም ምርታቸው በቀላሉ ከአገር አገር ሊንቀሳቀስና ትርፍ ሊያመጣ የሚችሉት ላይ ሲሆን፣ ትንንሽ ድርጅቶችና   ምርታቸው ለውጭ ንግድ ሊውል የማይችል ድርጅቶች ከውጭ የገንዘብ ተቋማት መግባት እምብዛም በቀጥታ አይጠቀሙም። ባለሙያዎችን ከአገር ውስጥ ባንኮች በማስኮብለል የሚያጋብሱት ትርፍ ውጭ ላሉ ባለድርሻዎቻቸው ስለሚያከፋፍሉ፣ የተማሩ ሰዎች ለአገራቸው “የቅርብ ሩቅ/የአገር ውስጥ ስደተኛ” እንዲሆኑም ያደርጋሉ። ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለሙያ ፈልሶባቸው፣ ደንበኛ ቀርቶባቸው ከእነ ጭራሹ የሚዘጉ ወይም በሌሎች ጠንካራ ባንኮች ዕቅፍ ውስጥ የሚገቡ የአገር ውስጥ ባንኮች አይጠፉም። ምናልባት ለጊዜው ሊጠቅም የሚችል የውጭ ምንዛሪ ወደ ገበያው ቢያፈሱም፣ በጊዜ ሒደት ለባለ ድርሻዎቻቸው  ትርፍ ማከፋፈል ሲፈልጉ የውጭ ምንዛሪ ስለሚፈልጉ፣ የዶላር እጥረትና የካፒታል ሽሽት የሚፈጥሩበት ዕድልም ይኖራል።

ሐ)   ጎመን በሥጋ (ት)፡- ይህ አስታራቂው መንገድ ነው። እንደ መጀመሪያው ጎራ ልቅነትና  ሥርዓት አልበኝነት እንዳይበዛ  በተቋማዊ ልጓም፣ እንደ ሁለተኞቹ ጎራ ቆሞ ቀርነት ሥር እንዳይሰድ በውድድር አለንጋ ሸንቆጥ በማድረግ ምጣኔ ሀብትን ከመክፈት የሚገኙ በረከቶችን ማብዛትና ጦሶችን መቀነስ ይቻላል ባይ ናቸው። እንደ ሁለተኛው የጎመን ድስት ታቅፈው ክረምቱን ከርመው በጋውን ለመባጀት አይዳዳቸውም።

እንደ መጀመሪያውም “የጎመን ድስት ይውጣ፣ የገንፎ ድስት ይግባ” ብለው በወረት አይገለበጡም። የገንፎ ድስት ሲገባ የጎመን ድስት መውጣት አይጠበቅበትም። ቢያሻው ቫይታሚኑን ለሚፈልጉ በዓይነትነት፣ ካልሆነ ዘይት ለሚሹ በጎመን ዘር መልክ ህላዌውን ይቀጥላል። ገንፎም የድርሻውን ድስትና ቦታ ያገኛል። “ጠርጥር፣ ከገንፎ ውስጥ ይኖራል ስንጥር” እንደሚባለው መንግሥታዊ የምዘናና የቁጥጥር  አሠራሮችን በጥንቃቄ በማዘመን፣ ዘርፉን ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ አጠቃላይ የአገር ሀብት እንዲዳብር፣ የሚፈጠረው ምርትና አገልግሎት በጥራትም በዓይነትም እንዲበዛ፣ አሠረጫጨቱ እንዲሳለጥ፣ ተወዳዳሪ ሐሳብ ያላቸው ድርጅቶች የወረት እጥረት እንዳያጋጥማቸው የብድር አቅርቦትን በማስፋፋት የጎላ አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት።

በወረቀት ላይ የአንድ አገር ምጣኔ ሀብት ወይ ዝግ ወይ ክፍት ሊሆን ይችላል። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁነታ ግን ከሌላው ዓለም ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ ሳያደርግ የሚኖር ምጣኔ ሀብት የለምና ፍፁም ዝግ የሚባል የለም።  እንዲህም የተወሰኑ ዘርፎችን ለአገር ውስጥ ይዞታነት በሕግ ስለሚገድብ ቧ ብሎ የተከፈተ ምጣኔ ሀብት በዓለም አይገኝም። ምንም እንኳን ደረጃው ቢለያይም ሁሉም የዓለም አገሮች ምጣኔ ሀብታቸው ገርበብ ተደርጎ የተከፈተ ነው። ከዚህ አንፃር ካየነው፣ ካልደፈረሰ አይጠራም የሚሉትም ሆኑ ጎመን በጤና የሚሉት ሩቅ የሚያስኬዱ አይደሉም።

በአብዛኛው ባዶ ድምር የጀማሪ ጨዋታ ነው። ጠጋ ብለን ካየነው ብዙው ነገር በብስለት ከተያዘና ከተስተናበረ የአንዱ መኖር የሌላውን ህላዌ እንዲያከትም  አያደርገውም። ለስሙ ‹‹የጎመን ድስት ይውጣ፣ የገንፎ ድስት ይግባ›› ቢባልም፣  ብልጥ ሰው ገንፎውንና ጎመኑን ወይ በአንድ ድስት በየተራ ያበስላል ወይም ምድጃውን አስፍቶ ድስቶቹን አብዝቶ ልዩ ልዩ ወጥ ይሠራል እንጂ፣ አንዱን ሲሸኝ አንዱን ሲቀበል አይኖርም። በ“ሐ” ጎራ ከሚነሱ አተያዮች አንፃር ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር አብረው የሚመጡ ጦሶች ቢኖሩም፣ እነሱን ተቋቁሞ በፍጥነት የሚያድግ የገንዘብ ዘርፍና ለአጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ማበብ፣ በተለይም በጊዜ ሒደት ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው። ከውጭ የሚመጣውን ጫና ተቋቁመው ገበያው ላይ መቆየት የሚችሉ አገር በቀል የገንዘብ ተቋማት የሚቀስሙትን ተጨማሪ ልምድ ይዘው ወደ ሌላ አገሮች አገልግሎታቸውን የማስፋፋት (በተናጠል ወይም ከየአካባቢው ባንኮች ጋር ሽርክና በመፍጠር) እና ተጨማሪ ገበያ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። ጊዜያዊ ቢሆንም እንኳ የውጭ ባለ ሀብቶች  ሲገቡ  የውጭ ምንዛሪ ፈሰስ ስለሚያደርጉ ለአጭር ጊዜም ቢሆን የምንዛሪ እጥረት ይቀርፋሉ።

በጊዜ ሒደት ግን እነሱ በትርፍ መልክ የውጭ ምንዛሪ ወደ አገራቸው ስለሚወስዱ፣ የነጠረ ጥቅማቸው የሚመዘነው አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱን አሳድገው የምንጭ ምንዛሪ የማመንጨት አቅሙን እንዲጎለብት አስተዋጽኦ ካደረጉትና ከአገር ውስጥ እየመጠጡ ወደ መቀመጫቸው ከሚልኩት ሀብት ተመዛዝኖ የሚገኘው ነው።

ነገሩን ለመቋጨት አንድ ድርጊት ጎጂም ጠቃሚም የሚሆነው መጥኖ በመጠቀምና  ባለመጠቀም ነው። እሳት ሲመጠን ያበስላል፣ ሲበዛ ያቃጥላል። ውኃ ሲመጠንና ሲጠራ ይጠጣል፣ ለመስኖ ለኃይል ማመንጫ ይውላል። ከገደብ ሲያልፍ ጎርፍ ሆኖ ይወስዳል፣ ጥልቅ ሆኖ ያሰምጣል። በዚህ ትይዩ የውጭ ባንክ ስለገባና ስላልገባ የሚፈጠር በጎ ፍሬ የሚወሰነው አጠቃቀሙን ያወቅን እንደሆነ ነው፡፡ ባይገባ የአገር ውስጥ ባንኮች ገበያው ውስጥ ተግተው ሠርተው ሊለወጡ ይችላል። ቢገባ  አብዛኛው ቆጣቢና ተበዳሪ አማራጭ ያገኛል። ቆጣቢ ሻል ያለ ወለድ፣ ተበዳሪው ዝቅ ያለ ወለድ ሊያገኙ ይችላሉ። በቀጣይ የትኞቹ አገሮች፣ መቼና በምን ደረጃ ምጣኔ ሀብታቸውን ለውጭ የገበያ ተዋንያን በመክፈት ተጠቀሙ (ተጎዱ) የሚለውን እናያለን።

ቸር ያሰንብተን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...