በንጉሥ ወዳጅነው
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በብዙ ፈተናና ውጣ ውረድ ውስጥ ናቸው፡፡ የዓለሙን ሁኔታ እንተወውና በአገራችን የተፈጠረው የሰላም መደፍረስና የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በአጠቃላይ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚውን እንደተገዳደረው ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም ቅድሚያ ለሰላም፣ ለመረጋጋትና ለሰከነ ፖለቲካዊ ወይይት መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የምጣኔ ሀብት፣ የገበያና የንግድ አሠራርን ለማስተካከል መትጋት ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡
በዛሬው ቅኝቴ በወጉ መታየት ስለሚገባው አገራዊ የንግድ አሠራራችን፣ የሻጭና የሸማች የገበያ መስተጋብር መመልከት ወድጃለሁ፡፡ ሥርዓቱ አገራችን በምትከተለው የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዚሁ ላይ ተመሥርተው በሚወጡ ሕግጋት መሠረት እንዲተዳደር የማድረጉ መንግሥታዊ ጥረት ልዩ ትኩረት ማግኘት አለበት፡፡ በተለይ የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት ያዝ ለቀቅን ትተው፣ ቢያንስ በነጋዴውም ሆነ በሸማቹ ሕዝብ ዘንድ የንግድ መብትና ግዴታዎች ተገቢው ግንዛቤ ተይዞባቸው ከልብ እንዲተገበሩ ማደረግ አስፈላጊ ነው፡፡
በመሠረቱ የንግዱን ኅብረተሰብ ከፀረ ውድድርና ተገቢ ካልሆኑ የገበያ ተግባራት፣ እንዲሁም ሸማቹን ከሚያሳስቱ የገበያ ሁኔታዎች የመከላከል ጉዳይ ከብሔራዊ ደኅንነት ሥራዎች እንደ አንዱ የሚቆጠር ነው፡፡ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተፈጠረ ካለው የገበያ አሻጥር፣ የገንዘብ የመግዛት አቅም መዋዠቅና ኮንሮባንድን የመሰሉ ብልሽቶችን የሚከላከል ዕርምጃ ማጠናከር ተገቢና አስፈላጊ የሚሆነው፣ ከፖለቲካዊ ጥቃት ተለይቶም ስለማይታይ ነው፡፡
ለነፃ ገበያ ውድድር አመቺነት ያለው ሥርዓት ለማስፈን እንዲቻልም የወጣው የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ (ቁጥር 685/2002) ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች የማስፈጸሚያ መመርያና ደንቦችም ጭምር በተገቢው እንዲሠራባቸው ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በብሔራዊ ባንክና በገቢ መሥሪያ ቤቶች በቅርቡ የወጡ ጊዜያዊ መመርያዎችን በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግም ቢሆን መሠረታዊ የንግድ አዋጁን መከተል ይገባል፡፡
በንግድ ሥርዓቱ ላይ በቂ የሪፎርም ሥራዎችና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን የማበልፀግ ጉዳይ ይበልጥ መጠናከር ያለበት አገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ለነገሩ የነጋዴው የንግድ አሠራር ባህሪ ከሸማቹ ፍላጎትና ሰብዕና ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም መሆኑ የዘርፉን እርምት ይጠይቃል፡፡ በተለይ በዕለት ተዕለት ፍላጎት የችርቻሮ ገበያ ውስጥ ያለው የነጋዴው አሠራር ለተጠቃሚው አመቺ አለመሆኑ መንግሥትን ሊያሳስበው ግድ ይላል፡፡
የአገራችን አንዳንዱ ነጋዴ ሲፈልግ ይሸጣል፣ ሳይፈልግ አይሸጥም፡፡ ሱቅ ውስጥ ያለውን ዕቃ ይደብቃል፣ ‹‹ነገ ዋጋ ሊጨምር ይችላል›› በሚል ሥሌት ይሸሽጋል፡፡ ‹‹የተሻለ ገንዘብ ያስገኝልኛል›› ወደሚለው ገበያ በሕገወጥ መንገድ ያሸጋግራል፡፡ ሚዛን ያጎድላል፡፡ የዋጋ ዝርዝር አይለጥፍም፡፡ ሸማቹ የሚፈልገውን መረጃ አይሰጥም፡፡
ይህን አባባል በተጨባጭ ሊያስረዳልን የሚችለው በዋናነት የመርካቶ ገመና ነው፡፡ ሸማቹም ሆነ መንግሥት እንደሚያውቀው ከ60 በመቶ በላይ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት ይህ ግዙፍ የንግድ ሥፍራ፣ በርካታ ምርቶችን ጥቂት የጅምላ አቅራቢዎች በሞኖፖል የያዙበት ነው፡፡ በፍራንኮ ቫሎታም ሆነ በኤልሲ በተፈቀደ የውጭ ምዛንሪ ከውጭ የሚገባ ምርትን ትክክለኛ ዋጋ አያሳውቁም፣ ያሻቸውን ትርፍ እያስቀመጡ ቢሸጡ ከልካይ የላቸውም፣ ደረሰኝ ለመስጠት አይፈልጉም፣ መከራውን ሕዝብ ላይ ጭነው በግል ለመበልፀግ ያሴራሉ፡፡
እውነት ለመናገር አብዛኛው ሸማችም ስለሚገዛው ዕቃ (ሸቀጥ) ጥራት መጠየቅ አይችልም፡፡ በአንዳንዱ ሕገወጥ ነጋዴም፣ ሸማቹ ገበያው የሰጠውን ብቻ ተቀብሎ እንዲሄድ ሰብዕናን በሚነካ ሁኔታ ያንጓጥጣል፡፡ ሸማቹ በገዛ ገንዘቡ አማርጦ መግዛት አይችልም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰብዕና ደግሞ አብዛኛው ደሃ በሆነበት አገር ገንዘቡ በስንት ድካምና ልፋት እንደሚገኝም አይገነዘብም፡፡ ወይም ማስታወስ አይፈልግም፡፡
ሌላው ቀርቶ መንግሥት ለሕዝብ እንዲደርስ ያቀረበውን መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጥ (ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና ሲሚንቶም ቢሆን) ባልተገባ ሁኔታ ለማይገባው ተጠቃሚ ይሸጣል፡፡ ዛሬ የገባውን ስኳር ነገ ‹‹የለም›› ይላል፡፡ የተበላሸ ዕቃ ሸጦ ‹‹መልስ ወይም ቀይር›› ቢሉት እሺ አይልም፡፡ እንዲያውም ‹‹ከእኔ አልገዛህም›› ብሎ ሽምጥጥ አድርጎ ይክዳል፡፡ ይህ ዓይነቱን ዝንፈት ሊያርቀው የሚችለው ደግሞ አዋጁንም ሆነ ያሉትን የንግድ ሕግጋት በጥብቅ መተግበር ብቻ ነው፡፡
እንደ ሸማች ደግሞ ለእያንዳንዱ ሸቀጥ ሱቅ በተሄደ ቁጥር ምስክር ይዞ መሄድ አይቻልም፡፡ ከነጋዴው ጋር በቀና መንፈስ መግባባትም አይቻልም፡፡ ከሰው ሰው እየለየ፣ ከብሔር ብሔር እየለየ፣ ከሃይማኖት ሃይማኖት እየለየ የሚሸጥ መኖሩን መስማት ደግሞ በእጅጉ ያሳምማል፡፡ በእርግጥ ይህን ብልሽት ለማረም ማኅበረሰቡም በመንቃት ትግልና ተሳትፎ መጀመር አለበት፣ የግድ ነው፡፡
ስግብግቡ ነጋዴ የሚይዘውን ዕቃ/ምርት ዋጋ ካመጣበትና ከተመነው በላይ እንዲሁ ከፍና ዝቅ እያደረገ፣ ለአንዱ በ500 ብር የሸጠውን ለሌላው በ600 እና በ700 ብር እንዲሸጥ ሕጉ ብቻ ሳይሆን ሞራልና ሥነ ምግባራችንም ሊፈቅዱለት ባልተገባ ነበር፡፡ አንዳንዴ የአገሪቱ የደረጃዎች ሥርዓት ጥራቱ የተረጋገጠለት ምርት እያለ፣ ጥራት የሌለውን ዕቃ በተመሳሳይ ዋጋ እንዲያቀርብም ቸል ማለት አይገባምና ትግል መደረግ አለበት፡፡
አንዳንዱ ነጋዴ ደግሞ ስለንግድ አሠራር ምንነት አለማወቁና ቸልተኛ መሆኑ መካድ የለበትም፡፡ መንገድ ዳር ያለች ጠባብ ቤት ተከራይቶ አሮጌ መደርደሪያና ሚዛን አስቀምጦ፣ በዝቅተኛ ካፒታል የተመዘገበ ፈቃድ ለጥፎ ሥራውን ይጀምራል፡፡ በጎን ደግሞ ትልቅ መጋዘን ውስጥ ወይም ተዘግቶ በሚውል ግቢ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ሸሽጎ ያስቀምጣል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሻጥር ደግሞ ከየትኛውም ሕግ አስፈጻሚና የፀጥታ ኃይል የተሰወረ ሊሆን አይችልም፡፡ ያው አሻጥሩ በመበርታቱ እንጂ፡፡
በዚህ ጽሑፍ የነጋዴውና የቸርቻሪው የሕግ ጥሰት ላይ ብቻ በማተኮር እሱኑ ሰፋ አድርገን እንመልከት፡፡ አንዳንዱ የንግዱ ማኅበረሰብ የነጋዴነት መብቱ የት ድረስ እንደሆነ ለምን አይገነዘብም ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የሸማቹን ጥቅም አለመረዳት፣ ሸማቹ በነጋዴው አማካይነት በየጊዜው በሚደርስበት እንግልትና ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በአገሩና በመንግሥት ላይ ምሬት እንደሚፈጥርስ ማሰላሰል ለምን ይሳናል?
የንግድ ሕጉ በሥርዓቱና በአግባቡ አለመተግበሩ በተለይ አነስተኛ ነጋዴውን አደራጅቶ፣ በፍትሐዊ ፉክክር እንዲመራ አለማድረጉም መጠቀስ ያለበት ችግር ነው፡፡ አንዳንዱ ነጋዴ እኮ ከሸማቹ ጋር ብቻ ሳይሆን እርስ በርሱም አይስማም፡፡ የአንዱን ነጋዴ ዋጋ ሌላው ነጋዴ እየሰበረ ‹‹የእገሌ ሱቅ ይሻላል›› እያስባለ እሱ እየበላ፣ ሌላውን ፆም ለማሳደር ይኳተናል፡፡ አግባብ ባልሆነና የነፃ ገበያን የውድድር አሠራር ባልተከተለ አሻጥር ከገበያ እንዲወጣም ያደርገዋል፡፡
የንግዱ ማኅበረሰብ እየተናበበ ዋጋ የሚጨምርበት አድማ መሰል አሠራር ብዙ ነው፡፡ በአድማው መሠረት ዋጋ ያልጨመረ ነጋዴ ከተገኘ ብዙ አፍራሽ ወሬዎች ይነዙበታል፡፡ ለምሳሌ ሥጋ ነጋዴ ከሆነ ‹‹የሞተ ከብት እያስገባ ነው›› በሚል አሉባልታ ይዘምቱበታል፣ በጥራቱ ይወነጅሉታል፣ ሳይወድ በግድ የአድማው ተካፋይ ያደርጉታል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ በተለይ የምግብ፣ የሉካንዳና የመጠጥ ነጋዴው ቤቱን ቀለም ቀብቶ ሲጨርስ ሸቀጦቹ/ምርቶቹ ላይ ዋጋ መጨመሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በአጠቃላይ የንግዱ ኅብረተሰብ አሠራር በነፃ ገበያና በተወዳዳሪነት መርሆዎች ላይ የተመሠረተ አይደለም የሚያስብለው አንዱ ማሳያም ይኸው ነው፡፡ የሸማቾችን ጤንነትና ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን መስፋፋት ለመግታት የሚያስችል መሠረት ያለው የንግድ አሠራርም እየተተገበረ አለመሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በእነዚህና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች የንግዱ አሠራር ሥርዓት መያዝ አለበት፡፡ ሕግ ሊወጣለት የሚያስፈልግ በመሆኑም ሊከተላቸው የሚገቡ አሠራሮች በአዋጅ ተደንግገዋል፡፡ የሸማቹ መብትና ጥቅም ከብልሹ የነጋዴዎች ባህሪ ሊጠበቅ የሚችለው ደግሞ ሕጉን በፅናት በመተግበርና ሸማቹን በማንቃት ነው፡፡
ሸማቹም በንግዱ አሠራር ተፈጥሯዊ ባህሪና በአዋጅ የተሰጡትን የሸማችነት መብቶቹን ለማስከበር የራሱን ሚና መጫወት አለበት፡፡ ትናንት የገባ ስኳር፣ ዘይት፣ ወዘተ ዛሬ የለም ሲባል ‹‹የት ሄደ?›› ብሎ የመጠየቅ መብት ስላለው በመብቱ መጠቀም አለበት፡፡ ተደራጅቶም ሆነ በተናጠል መብቱን ለማስከበር መንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱ የሸማች አካል የሆነው ሕግ አስከባሪ እንዲተባበረው ማነሳሳትም ይኖርበታል፡፡
በንግድ ሥርዓቱ ላይ ዝንፈት፣ አለመታመን፣ ግዴታን አለመወጣት፣ ወይም አጭበርባሪነት ሲያጋጥመው፣ ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ አድልኦ ሲፈጸምበት ‹‹ለምን?›› ብሎ መጠየቅ አለበት፡፡ ለሚመለከተው አካል ወይም አጠገቡ ላለው ፖሊስ ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ ካልሆነ ደግሞ በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ድረ ገጽ ማጋለጥም ግድ ይለዋል፡፡
በአዋጁ እንደተመለከተው ሸማቹ ለፋብሪካ ወይም መልሶ ለመሸጥ ሳይሆን፣ ዋጋውን ራሱ ወይም ሌላ ሰው ከፍሎለት ለራሱ ወይም ለቤተሰቡ ፍጆታ የሚሆን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት የሚገዛ የተፈጥሮ ሰው ነው፡፡ ለራሱ በሚገዛው የፍጆታ ሸቀጥ አማካይነት ከነጋዴው በኩል የሚደርስበትን እንግልትና ጭማሪ፣ የሚዛን ጉድለትም ሆነ የመረጃ አለማግኘት ችግር የራሱን ጥቅም በራሱ የማስከበር ግዴታ እንዳለበት መረዳትም ያስፈልጋል፡፡
ነጋዴው ደግሞ የሙያ ሥራው አድርጎ ጥቅም ለማግኘት ሲል በንግድ ሕጉ የተዘረዘሩትን ሥራዎች የሚሠራ፣ ወይም አገልግሎት የሚሰጥ ወይም የንግድ ሥራ ነው ተብሎ በሕግ የሚወሰነውን ሥራ የሚሠራው ሰው በመሆኑ፣ በሕጉ መሠረት የመንቀሳቀስ ግዴታ እንዳለበት ማስታወስ ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ነጋዴ በግሉ ወይም ከሌሎች ጋር በመሆን በአንድ የገበያ ክልል ውስጥ ዋጋን ወይም ሌሎች የንግድ ውድድር ሁኔታዎችን የመቆጣጠር፣ ወይም ውድድርን የማጥፋት ወይም በግልጽ የመገደብ፣ በግልጽም ሆነ በሥውር ያላግባብ በመጠቀም የንግድ ሥራ ማካሄድ አይችልም፡፡ በንግድ ሕጉ መሠረት የገበያ የበላይነትን ያለአግባብ የመጠቀም ድርጊቶች የሚባሉት መጥቀስ ተጨማሪ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላልና ልጥቀሳቸው፡፡
ምርትን መገደብ፣ የንግድ ዕቃዎችን ማከማቸት ወይም መደበቅ፣ ወይም በመደበኛው የንግድ መስመር እንዳይሸጡ ማድረግ ወይም መያዝ፣ የንግድ ውድድርን ለመገደብ ወይም ለማጥፋት በማሰብ ከማምረቻ ዋጋ በታች መሸጥ፣ ወይም የተወዳዳሪን ወጪ ማሳደግ፣ ወይም ግብዓቶችን ወይም የሥርጭት መስመሮችን ቀድሞ በመያዝ ተወዳዳሪ ላይ ያነጣጠረ ጎጂ ድርጊት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ መፈጸም፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ፍትሐዊ ያልሆነ የመሸጫ ዋጋ ወይም የመግዣ ዋጋ መጠየቅ፣ ግልጽና ወቅታዊ የሆነ የገበያ አሠራርን በመቃረን ገበያን በበላይነት የያዘው ነጋዴ በልማድ የሚያደርገውን ወይም ሊያደርገው የሚችለውን እንደማይችለው ሆኖ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆን፣ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር ገበያን በበላይነት በያዘ ነጋዴ ቁጥጥር ሥር ያለን ተፈላጊ ግብዓት ተወዳዳሪ ለሆነው ወይም ሊሆን ለሚችል ነጋዴ መከልከል፣ የንግድ ውድድርን ለማጥፋት ወይም ለመገደብ በማሰብ በዕቃዎችና በአገልግሎቶች አቅርቦትና ግዥ ላይ በደንበኞች መካከል በዋጋና በሌሎች ሁኔታዎች ልዩነት መፍጠር፣ ወዘተ ናቸው፡፡
ከእነዚህ በተጨማሪ ቅጣታቸው ከባድ የሆኑና ፍፁም የተከለከሉ ድርጊቶች አሉ፡፡ እነሱም በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ዋጋን መወሰን፣ ተመሳጥሮ መጫረት (አሁን በሕዝብና በመንግሥት ንብረት ግዥ ላይ በፕሮፎርማና በገበያ ድርድር ስም ምን እንደሚፈጸም ይታወቃል)፣ ደንበኞችን ወይም የገበያ ክልልን ወይም ምርትና ሽያጭን በኮታ መመደብ፣ በነጋዴዎች መካከል ዓላማው ወይም ውጤቱ ዝቅተኛ የችርቻሮ ዋጋ መወሰን፣ ወዘተ በኅብረት አቋም መያዝ ወይም በማኅበር ውሳኔ ማሳለፍ ፍፁም የተከለከሉ ድርጊቶች ናቸው፡፡
ማንኛውም ነጋዴ የሌላውን ነጋዴ ወይም የነጋዴውን ተግባራት፣ በተለይም ነጋዴው ከሚያቀርበው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተገናኘ ሁኔታ ታማኝነትን ያሳጣ ወይም ሊያሳጣ የሚችል ማንኛውም ሐሰት የሆነ ወይም ማረጋገጫ የሌለው አገላለጽ ተገቢ ያልሆነ የውድድር ተግባር ክልከላ መሆኑ በአዋጅ ተረጋግጧል፡፡ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ዕቃዎቹንና የአገልግሎቶቹን የዋጋ ዝርዝር በንግድ ቤቱ በግልጽ በሚታይ ቦታ ማመልከት፣ ወይም በንግድ ዕቃዎቹ ላይ መለጠፍ እንዳለበትና የተጠቀሰው ዋጋ ከቀረጥ፣ ከታክስ ወይም ሌላ ሕጋዊ ክፍያ ያካተተ መሆን እንዳለበት ተደንግጓል፡፡
ማንኛውም ነጋዴ በሸማቾች መካከል ተገቢ ያልሆነ አድልኦ መፈጸም አይችልም፡፡ አንድን ዕቃ ወይም አገልግሎት ለመሸጥ ሸማቹ ያልፈለገውን ሌላ ዕቃ አብሮ እንዲገዛ ማስገደድም ነጋዴው አይችልም፣ መብት የለውም፡፡ ሕጋዊ ከሆነው ውጪ በሚዛን ወይም በመስፈሪያ ወይም በሌላ መለኪያ መሣሪያ ማጭበርበርም በአዋጁ ተከልክሏል፡፡ በንግድ ቤቱ ከተለጠፈው ዋጋ አስበልጦ መሸጥም ክልክል ነው፡፡ ደረሰኝ መስጠት የነጋዴው ግዴታ ነው፡፡
ይህ አዋጅ የሸማቾችን መብትና ጥበቃ የሚመለከቱ ድንጋጌዎችንም ይዟል፡፡ በዋናነት የሚከተሉትን እንመልከት፡፡ ማንኛውም ሸማች ስለሚገዛው ዕቃ፣ ወይም አገልግሎት ጥራትና ዓይነት በቂና ትክክለኛ መረጃ ወይም መግለጫ የማግኘት መብት አለው (በየጥጋጥጉ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀለና ጤናውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ምርት ለመግዛት ከመሞከሩ በፊቱ መብቱን ማወቅና መጠቀም ነው የሚበጀው)፡፡ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን አማርጦ የመግዛት መብት አለው፡፡ የዕቃዎችን ጥራት ወይም አማራጮችን በማየቱ ወይም የዋጋ ድርድር በማድረጉ ምክንያት እንዲገዛ አይገደድም፡፡
ሸማቹ በማንኛውም ነጋዴ በትህትናና በአክብሮት የመስተናገድና በነጋዴው ከሚደርስበት የስድብ፣ የዛቻ፣ የማስፈራራትና የስም ማጥፋት ድርጊት የመጠበቅ መብት አለው፡፡ በንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ግብይት ምክንያት ለሚደርስበት ጉዳት የመካስ (ካሳ የማግኘት) መብት አለው፡፡
ሸማቹ የገዛው ዕቃ (አገልግሎት) ጉድለት ያለበት (የተበላሸ) ሆኖ ሲገኝ አገልግሎቱን ከገዛበት ቀን ጀምሮ በ15 ቀናት ውስጥ በሸማቹ ምርጫ ነጋዴው አገልግሎቱን ለሸማቹ በድጋሚ ያለ ክፍያ ይሰጠዋል፡፡ ወይም ነጋዴው የተቀበለውን ዋጋ ለገዥው ይመልሳል (የተበላሸ ዕቃ ሸጦ ‹‹እኔም የገዛሁት እንዲሁ ስለሆነ አልቀይርም›› ወይም ‹‹ገንዘቡን አልመልስም›› ማለት ነጋዴው አይችልም)፡፡
ነጋዴው ሊያከብራቸው የሚገቡ ሌሎች ድንጋጌዎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ስሙን በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ አለበት፡፡ ነጋዴው ከሚሸጠው የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሸማቹ በሚያቀርብለት ጥያቄ መሠረት፣ በአጥጋቢ ሁኔታ ራሱን መግለጽና ሸማቹ የሚፈልገውን መረጃ እንዲወስድ መፍቀድ አለበት፡፡
ማንኛውም ነጋዴ በሚሸጣቸው ዕቃዎች ላይ መግለጫ መለጠፍ ወይም በተለየ ወረቀት ላይ ጽፎ ለሸማቹ መስጠት አለበት፡፡ ስለንግድ ዕቃዎች የሚለጠፈው መግለጫ፣ የሚከተሉትን ቁም ነገሮች የያዘ ወይም የሚያመለክት መሆን አለበት፡፡
የንግድ ዕቃው ስም፣ የተሠራበት ወይም የመጣበት አገር፣ የተጣራ ክብደት፣ መጠንና ብዛት፣ የዕቃው ጥራት፣ ዕቃው ከምን እንደ ተመረተ፣ የአሠራር ወይም የአጠቃቀም ዘዴ፣ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች፣ ነጋዴው ለገዥው ስለሚሰጠው ዋስትና፣ የተመረተበት ቀን፣ ከአገልግሎት ውጭ የሚሆንበትን ቀንና በኢትዮጵያ ደረጃዎች የተመለከቱት መሥፈርቶች ያሟላ ስለመሆኑ የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡ በዚህ ረገድ እንደ አገር ምን ላይ እንደቆምን መፈተሽ የሁላችንም ኃላፊነት ነው፡፡
በአጠቃላይ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በውድድር ላይ የተመሠረተና ከላይ የተጠቀሱትን ክልከላዎችና የመብት ጥበቃዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፡፡ ነፃ ገበያ ማለት ነጋዴ ያላንዳች ኢኮኖሚያዊ ምክንያት እየተቧደነ ወይም በማኅበር እየተደራጀ በየሸቀጡና ምርቱ ላይ የዋጋ ጭማሪ አድማ ማድረግ ማለት አይደለም፡፡
ንግድን በቡድን ሆኖ ገበያን በበላይነት መቆጣጠርና ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማግኘትም አይፈቀድም፡፡ በዚህ ረገድ አዋጁ የተሟላ ቢሆንም አተገባባሩ ላይ ያለብን ችግር ግን ሥር እየሰደደ መጥቷል፡፡ እናም ለተግባራዊነቱ ሕዝብና በየደረጃው ያለው አስፈጻሚው አካል ኃላፊነታቸውን በአንክሮ ሊወጡ ይገባል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡