Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በኮንትሮባንድ የሚገባውና የሚወጣው ካልተገታ ልፋታችን ትርጉም አይኖረውም!

ኢትዮጵያ ከምታመርተው የበለጠ የምትሸምተው ይልቃል፡፡ ኑሮአችን ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ የተመሠረተ ሆኗል። በአጠቃላይ እንደ አገር አምራች አይደለንም፡፡ ማምረት ተስኖን ሳለ ቅንጡ የሚባሉ የውጭ ምርቶችን በማስገባት የምንታማ አለመሆናችን ደግሞ ያስገርማል፡፡ አገራችን እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ ምርቶችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ዕጦት እያንገላታት፣ ቅንጡ የሚባሉ መገልገያዎችን ለማስገባት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ የማይቸግራት ናት ኢትዮጵያ፡፡

ዓመታዊ የገቢ ንግድ ወጪያችን ከ18 ሚሊዮን ዶላር በላይ ልቋል፡፡ ይህ በሕጋዊ መንገድ በባንክ በኩል ሌተር ኦፍ ክሬዲ ተከፍቶ ለሚገቡ ዕቃዎች የምናወጣው ወጪ ነው፡፡ የሕገወጥ ንግድ በመረጃ ተደግፎ የሚቀርብበት ሁኔታ የለም እንጂ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች ግምት እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በይፋዊ መረጃ የምንሰማው የገቢና የወጪ ንግዳችን ሥሌት ሕጋዊ መስመሩን ጠብቆ የተሠራ ነው የሚባል በመሆኑ እንጂ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ገብቶ ገበያውን የሚያጥለቀልቀው ምርት ስፍር ቁጥር የለውም፡፡ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚያሳርፈውም ተፅዕኖ ቢሆን በዚሁ አንፃር የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ በአገር ደረጃ የምንሸምተው የውጭ ምርት እጅግ ብዙ መሆኑን የምናውቀው በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር የሚገቡ ምርቶችም ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

በኮንትሮባንድ ወይም በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ያላቸው ሥፍራ በቀላሉ ለማወቅ በተለይ በጠረፋማ የአገራችን ክፍሎች ያሉ ክፍሎችን መቃኘት ብቻ ይበቃል፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ባሉ መደብሮችና ሰፋፊ የገበያ ቦታዎች በሙሉ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በሙሉ በኮንትሮባንድ የሚገቡ መሆናቸውን መታዘብ ብቻ ይበቃል፡፡ እነዚህ ምርቶች በሕጋዊ መንገድ አለመግባታቸው እየታወቀ ግብይታቸው እንዲፈጸም ይደረጋል፡፡ 

በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች በብዛት የሚታይባቸው አካባቢዎች በሕጋዊ መንገድ የሚገቡ ምርቶች አይታይባቸውም፡፡ ነገር ግን በጠረፋማ አካባቢዎች በኮንትሮባንድ ገብተው ገበያውን የያዙት ምርቶች ግን መጠናቸው ይለያይ እንጂ አሳብረው ወደ መሀል አገር ገብተው ሲቸበቸቡ ይታያሉ፡፡ በአጭሩ በሕጋዊ መንገድ ይሁን በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶች ‹‹ማራገፊያ›› ሆነናል፡፡ በየጊዜውም እየጨመረ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ስንል ወደ አገር የሚገባውን ብቻ ሳይሆን ወደ ውጭ የሚወጣውንም ያጠቃልላልና በገቢና በወጪ የኮንትሮባንድ ንግድ በአገር ደረጃ የሚታጣውን ስንደማምር ጉዳዩ በዋዛ የማይታይና መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በኮንትሮባንድ እየተነዱ የሚወጡት የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት፣ ወርቅ ቡናና ሌሎች ምርቶች አገርን እያራቆቱ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ እያስከተለ ያለውን ጉዳት ያህል ግን ቁጥር እየተደረገበት አይደለም፡፡

ኮንትሮባንድ ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ ብቻም ሳይሆን እንደ አገር በውጭ ምርቶች ላይ ከተንጠለጠለ ሸመታችን እንዳንወጣ እያደረገም ነው፡፡ በኮንትሮባንድ የሚገቡ ምርቶች ጤንነታቸውና ደኅንነታቸው የተጠበቁ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ስለሌለ ከጤና አንፃር የሚያስከትለው ጉዳት ከባድ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም እንዳልታየ እየታለፈ ነው፡፡ በተለያዩ የገበያ ሥፍራዎች መድኃኒት ሳይቀር በኮንትሮባንድ እየገባ ይቸበቸባል፡፡ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች በፀአዳ ፋርማሲዎች ውስጥ በኮንትሮባንድ ገብተው የሚደረደሩ መድኃኒቶችን ከየት መጣ የሚል የለም? ብንፈትሽ ብዙ እናገኛለን፡፡

በአጭሩ የኮንትሮባንድ ንግድ እየሰፋ መጥቷል፡፡ የምርት ዓይነቶቹ በዝተዋል፡፡ የሕፃናት ምግቦች ሳይቀሩ በኮንትሮባንድ እየገቡ ነው፡፡ ምርቶችንም የሚቀበሉ በሕጋዊ መንገድ እንሠራለን በሚሉ መደብሮች ውስጥ እያየናቸው መሆኑ  በእጅጉ ሊያሳስብን ይገባል፡፡ በኮንትሮባንድ የገባውና በትክክል ጤናማነቱና ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ምርት ለመለየት አለመቻሉ ደግሞ ሁኔታውን የበለጠ አሸናፊ ያደርገዋል፡፡ በአጠቃላይ ኮንትሮባንድ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖው ከፍተኛ ነው፡፡ ችግሩ እንዳይሰፋ ከልብ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ አሁን ላይ አንዳንድ ምርቶችን ከውጭ ወደ አገር ላለማስገባት የተወሰነው ውሳኔ ለኮንትሮባንድ ንግድን ሊያባብስ እንደሚችል ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ 

ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን ከተፈለገ መንግሥት እየተገበረ ካለው ሰሞናዊ ውሳኔዎቹ ጎን ለጎን በኮንትሮባንድ ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ ሊወሰድ ካልቻለ ለመልካም ያሰባቸው መመርያዎች በጎን ሌላ ጣጣ ሊያመጡበት ይችላል፡፡ ከውጭ ኮንትሮባንድ አንፃርም አገር የውጭ ምንዛሪ ገቢዋ እንዲወርድ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚወጣው የወጪ ንግድ ምርቶች በመሆናቸው እዚህ ላይም ከልብ መሥራት ካልተቻለ አሁንም ከገባንበት አዙሪት ለመውጣት አንችልም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት