Tuesday, December 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርብቶና አርሶ አደሮችን ያስታወሰው የፋይናንስ አካታችነት ሥርዓት

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የራሳቸው የቁጠባና ብድር ተቋም ወይም በጋራ የሚመሠርቱት የፋይናንስ ተቋም ካልሆነ በቀር እስካሁን ለግል አርሶ አደርና አርብቶ አደሩ በቂ ብድር የሚያቀርብ ባንክም ሆነ ወደ ተግባር የተቀየረ መመርያም ባለመኖሩ የግብርናው ዘርፍ በሚፈለገውን ልክ ድጋፍ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

በጎረቤት አገሮች ኬንያ፣ ዑጋንዳና ታንዛኒያ ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች የባንክ የብድር አገልግሎት መቅረብ ከጀመረ ዘለግ ያለ ጊዜያት እንደተቆጠረ የሚገለጽ ሲሆን፣ ለዚህም የመሬት ባለቤትነት ሥርዓታቸው እንደጠቀማቸው ይነገራል።

መንግሥት ባንኮች ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የብድር አገልግሎት የሚሰጡበትን ሁኔታ ማመቻቸቱ የፋይናንስ አካታችነት የማዳረስ ዕቅዱን ብቻ ሳይሆን በሔክታር የሚገኘውን ምርታማነት በእጥፍ ሊያሳድገው፣ ግብርናውን በጣም ወደ ፊት ሊያራምደው እንደሚችል የግብርና ዘርፍ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልጹ ይሰማል፡፡

አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ለምሳሌ ግብዓት ማግኘት ላይ ብድር ቢያገኝ፣ በዘር፣ በማዳበሪያ አቅርቦት እንዲሁም ምርቱ ሲደርስ ደግሞ ሳይበላሽ በመካናይዜሽን ማጨድና መውቃት ቢችል ምንም ሰብል ሳይባክን በቀጥታ ወደ ጎተራ የሚገባበት ሁኔታ እንደሚፈጠር የሚያስረዱት የግብርና ባለሙያዎች፣ በምርት መሰብሰብ ወቅት ሊኖር የሚችልን ብክነት ማስቀረት ማለት ምርታማነትን መጨመር ማለት እንደሆነም አመላክተው፣ ይህም ከገንዘብ አቅርቦት ጋር የሚያስተሳስር እንደሆነም ጨምረው ያስረዳሉ፡፡ 

በኢትዮጵያ በጠቅላላው በገጠርና ከተሞች መካከል ያለው የፋይናንስ አካታችነት ሰፊ ልዩነት ያለው ሲሆን፣ ከብድርም ሆነ ቁጠባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ ያለው ሥርጭት በተለይም የአርብቶ አደር አካባቢ መገኛ በሚባሉት ክልሎች ዝቅተኛ ነው፡፡

ለአብነትም ዓምና ባንኮች ከዘርፍ አንፃር ከሰጡት ብድር ውስጥ ለግብርና የተሰጠው ድርሻ መቀነሱን መረጃዎች የሚያመላክት ሲሆን፣ ግብርና ከኢንዱስትሪ፣ ከአገር ውስጥና የውጭ ንግድ ዘርፍ ያነሰ ብድር ቀርቦለታል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ለ1,490 ሰዎች አገልግሎት ሲሰጥ፣ ነገር ግን የአርብቶ አደር አካባቢዎች መገኛ በሆነው የሶማሌ ክልል 53 ሺሕ ለሚጠጉ ሰዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ የአርብቶ አደሮች ፎረም ምሥረታ በተካሄደበት መድረክ ላይ ባቀረበው የዳሰሳ ጥናት ላይ ተገልጿል፡፡

ዓምና በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት ባንኮች ጠቅላላ ከሰጡት ብድር 80 በመቶ የሚሆነው የተወሰደው በርካታ የባንክ ቅርንጫፍ ባለበት አዲስ አበባ ሲሆን፣ በአንፃሩ የአርብቶ አደር አካባቢ መገኛ በሆኑት ክልሎች የተወሰደው የብድር ድርሻ በአማካይ 1.6 በመቶ መሆኑ ይገለጻል፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ መጠን ያለው ብድር የተወሰደው በአዲስ አበባ ቢሆንም፣ ይህ ገንዘብ በሌሎች አካባቢዎች ልማት ላይ ሊውል እንደሚችል ታሳቢ ሊደረግ ይገባል የሚል ሐሳብ ይነሳል፡፡

በሌላ በኩል ማይክሮ ፋይናንሶች ለግብርናው ዘርፍ የሚያቀርቡት ብድር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ዕድገት ቢታይበትም፣ ነገር ግን በተለይም ለአርብቶ አደር አካባቢ ነዋሪዎች ያላቸው የተደራሽነት ድርሻ ዝቅተኛ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡

ማይክሮ ፋይናንሶች እንደ ባንኮች ሁሉ ቅርንጫፎቻቸው በሕዝብ ብዛት ያላቸው ተደራሽነት በተለይም በአርብቶ አደር አካባቢዎች ዝቅተኛ ነው፡፡ ተቋማቱ ለግብርናው ዘርፍ የሚሰጡት ብድር ከቀደሙት ዓመታት ቢጨመርም አጠቃላይ ከሰጡት ብድር ውስጥ የሚሸፍነው ግን 28 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙት 43 የሚደርሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 9.8 ሚሊዮን የሚደርስ የቆጣቢዎች ማኅደር አላቸው፡፡ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት እነዚህ ተቋማት ለ2.5 ሚሊዮን አጠቃላይ ተበዳሪዎች ብድር እንዳቀረቡ ብሔራዊ ባንክ ያስረዳል፡፡

የአርብቶ አደር አካባቢ ክልሎች ከሚባሉት ውስጥ አፋር አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ የባንክ ቅርንጫፍ ቁጥር 63 ብቻ ነው፡፡ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ ከ31 ሺሕ በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች አገልግሎት ይሰጣል ማለት ነው፡፡ ሌላኛው ክልል በሆነው የሶማሌ ክልል 120 ቅርንጫፎች ሲገኝ፣ በክልሉ የሚገኝ አንድ የባንክ ቅርንጫፍ  ከ52 ሺሕ በላይ ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በድሬዳዋ የከተማ አስተዳደር እንዲሁ 97 የባንክ ቅርንጫፎች ሲገኝ እያንዳንዱ ባንክ ከአምስት ሺሕ በላይ ለሆኑ ዜጎች አገልግሎት ይሰጣል ማለት ነው፡፡ 

ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ፣ ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን በፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ሚና የለውም ብሎ በመረዳት፣ የፋይናንስ አገልግሎት የሚቀርብባቸው ቅርንጫፎች በተለይም በገጠርና የአርብቶ አደር አካባቢዎች በረዥም ርቀት ላይ መገኘት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎች፣ የሚጠየቁ የሰነድ ቅድመ ሁኔታዎች፣ በአገልግሎቱ ላይ ዕምነት ማጣት እንዲሁም ሃይማኖታዊ ጉዳዮች አካታች የፋይናንስ ሥርዓቱን በመተግበር ሒደት ውስጥ ዋነኞቹ ቁልፍ ችግሮች ተደርገው ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ፎረም በተመሠረተበት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ፍሬዓለም ሽባባው እንደገለጹት፣ አካታች የፋይናንስ ሥርዓት እንዲሁም የፖሊሲ ማዕቀፎች አገሪቱን ወደ ተሻለና የሚናበብ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚወስድ ሥርዓት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ለአርብቶ አደር ክልሎች አካታች የሆነ የብድር ሥርዓት (ወለድ አልባ ብድር) ለማመቻቸት ያደረገውን በርካታ የመመርያ ማሻሻያ የተናገሩት ኮሚሽነሯ፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አተገባበሩ ግን ብዙ ሥራዎች የሚፈልግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግሥት በዚህ ወቅት እየሄደበት ያለው መንገድ ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚናገሩት የግብርና ባለሙያዎች፣ አሁንም ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ብድር የሚቀርብበት መንገድ እንደ ሌሎቹ ዘርፎች የማስያዣ ንብረትና የመሳሰሉት የሚጠይቅ እንደማይሆን፣ የመበደሪያ መሥፈርቶቹ ቀለል ያሉ ሊሆኑ እንደሚገባ በመግለጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ እንደሚናገሩት፣ ምርት ወደ ውጭ የሚልኩ ኅብረት ሥራ ማኅበራት የምርት መጠን መቀነስና መቆራረጥ ምክንያትን ለመለየት 25 በሚደርሱ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ላይ በኮሚሽኑ የዳሰሳ ጥናት የተካሄደ ሲሆን፣ ከተገኙ ውጤቶች መካከል ማኅበራቱ መሰብሰብ ከሚችሉት ምርት መካከል 65 በመቶ ብቻ እንደሚሰበስቡና ለዚህም በምርት መሰብሰቢያ ወቅት በቂ ፋይናንስ አለማግኘት፣ አስተማማኝ የገበያ መዳረሻ ችግርና የዋጋ መዋዠቅ ተጠቃሾቹ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡

በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚያጋጥም የፋይናንስ እጥረት አንዱ የገበሬውም ሆነ አባል የሆነበት የኅብረት ሥራ ማኅበር ችግር መሆኑን ያስረዱት አቶ አብዲ፣ ባንኮች ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ቅድሚያ እንደሰጡ ማድረግ አንዱ ተግባር ስለሆነ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በተለይም የቡና የውጭ ግብይት ድርሻን ማሳደግ ዓላማው ያደረገ የባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የቡና ሲምፖዚየም በተያዘው ሳምንት መዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ለኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚያደርጉት ድጋፍ በምን ዓይነት መንገድ ሊጠናከር ይገባል በሚለው ላይ ኮሚሽኑ ከፋይናንስ ተቋማቱ ጋር ሲመክር መቆየቱን የሚናገሩት አቶ አብዲ፣ ቡና ብቻም ሳይሆን በሌሎች የግብርና ውጤቶችም በስፋት እየተመረተ የሚገኘውን ስንዴ ጨምሮ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ድርሻ ስላላቸው እንዴት አድርገው የፋይናንስ ችግራቸውን ያቃልላሉ? በሚለው ላይ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቀጣይ ሳምንት ትልቅ የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ ይገልጻሉ፡፡

አቶ አብዲ እንደሚሉት፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራት የአርሶ አደሩ ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን በሠለጠነ የሰው ኃይል ከመመራት፣ በቴክኖሎጂ ከመደገፍ አንፃር በሚፈለገው ደረጃ ላይ አልደረሱም፣ ትልቅ ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሱን የቻለ ፖሊሲ ያስፈልጋል በሚል ኮሚሽኑ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚታየው ለግብርና ራሱን የቻለ ባንክ እንዲሁም ድጋፍ አለው፡፡ በንግድ ባንኮች ድጋፍ ላይ ተመርኩዙ በሚገኝ ድጋፍ ብቻ የተሻለ ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡

በኢትዮጵያ በአርብቶ አደርነትና ከፊል አርብቶ አደርነት ተለይተው የሚታወቁ 220 ወረዳዎች ሲኖሩ፣ ከእነዚህ ውስጥ 173 ወረዳዎች በአፋር፣ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። ከዚህ ባሻገር 47 የሚደርሱት ደግሞ በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ ብሔርና ብሔረሰቦች ሕዝቦች፣ በጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ይገኛሉ።

ከላይ የተገለጹት ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሆነው ከሰሞኑ የተሰማው ዜና በተለይም ለአርብቶ አደርና አርሶ አደር ዜጎች በበጎ መልኩ የሚነሳ ሲሆን፣ ይህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሦስት ዓመት የሆነውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥን ብድር በይፋ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን የተመለከተው ነው፡፡

 ብሔራዊ ባንክ 2012 ዓ.ም. በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድርን አስመልክቶ ባወጣው መመርያ ላይ፣ የእርሻ ሰብል፣ እንስሳት፣ የአዕምሮአዊ ንብረት ባለቤትነትንና የመሬት ተጠቃሚነት መብት ምዝገባ ተደርጎባቸው ለማስያዣነት እንደሚቀርቡ ዘርዝሯል፡፡ እንደ ቦንድና የአክሲዮን ድርሻ ያሉ ገንዘብ ነክ ሰነዶችም ለብድር ማስያዣነት መቅረብ ይችላሉ፡፡

በ2011 ዓ.ም. የወጣው በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ የሚመሠረት የዋስትና ንብረት መብት አዋጅም ሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ በተከታዩ ዓመት ያወጣቸው ሁለት መመርያዎች በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት ለሚሰጥ ብድር የሕግ ማዕቀፍ ቢዘረጉም፣ ለንብረቶቹ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባ ሥርዓት ሥራ ባለመጀመሩ እስካሁን አገልግሎቱ ሳይጀመር መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አንድ የብሔራዊ ባንክ ኃላፊ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ባንኮች የቁም እንስሳትን ይዛችሁ አበድሩ ማለት አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል፣ ከዚያ ይልቅ በየዓመቱ ከሚያበድሩት ብድር ውስጥ የተወሰነውን ወደ ግብርናው ይሂድ የሚል ሐሳብ ገዥ ሆኖ ተገኝቷል (በመመርያው መሠረት አምስት በመቶ ያህሉን)፡፡ ነገር ግን ሲያበድሩ በራሳቸው ቅድመ ሁኔታ እንደሚሆን መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ 

የፋይናንስ አካታችነት ሲባል የተገለሉትን ወደ ዘርፉ ማምጣት ሲሆን፣ ተገለዋል ከሚባሉት ውስጥ አርብቶ አደሮች ዋነኞቹ እንደመሆናቸው መጠን በተረጋጋ ቦታ ላይ ሁኔታዎችን ማመቻቸት የሚለው ዕሳቤ የመንግሥት ልዩ ትኩረት መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ እንስሳት ብቻን ሳይሆን ሰብልንም አስይዞ መበደር የሚቻል ሲሆን፣ ይህ ሲሆን ወቅትን ያማከሉ ጉዳዮችን ሁሉ ከግንዛቤ በመክተት ተፈጻሚ የሚሆን ይሆናል፡፡ አርሶ አደሮች በዘመናዊ መሣሪያዎች (መገልገያዎች) ወይም በትራክተር እንዲያርሱ ተደርጎ የሚተው ብቻ ሳይሆን ምርት ሲበስብስም እንዲሁም ዘመናዊ መሳሪያዎች መጠቀሙ አይቀሬ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የተበደሩትን መክፍል የሚችሉት ከሚያገኙት ውጤት ስለሆነ ነው፡፡

አርብቶ አደሩንም ሆነ አርሶ አደሩን የመደገፍ ሥራ በአንድ ተቋም ብቻ ተግባራዊ የሚደረግ ስላልሆነ ብሔራዊ ባንክ፣ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን በተለይም ኮሚሽኑ ብዙኃኑን በግብርና የተሰማሩ ከ26 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉበት እንደመሆኑ በቅንጅት እየተሠራበት እንደሚገኝ ይገለጻል፡፡ ማኅበራቱ የገበሬ (አርሶ አደር)፣ የአርብቶ አደር ኅብረት ሥራ ማኅበራት በመሆናቸው በእነርሱ ላይ መሥራት የተጠቀሰውን ቁጥር ያላቸውን ተገልጋዮች ማግኘት መሆኑን የሚናገሩት ኃለፊው፣ በዚያው ልክም ውጤት የሚገኝበት ይሆናል፡፡

በተንቀሳቃሽ ንብረት ማስያዣነት የሚሰጥ ብድር በቅርቡ ይፋ ከሚደረግበት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መዲና ጅግጅጋ በተጨማሪ ኦሮሚያ፣ ደቡብና አማራ ክልሎች በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱ የሚጀመርባቸው ተከታይ ክልሎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

እንደ ብሔራዊ ባንክ መረጃ በአገሪቱ ውስጥ በመንግስት እንዲሁም በግል ዘርፉ ባለቤትነት የሚመሩ 30 ባንኮች ይገኛሉ (ሁለት የመንግሥት (የሕዝብ)፣ 23 የግል እንዲሁም አምስት ከማይክሮ ፋይናንስ ወደ ባንክ ደረጃ ያደጉ)፡፡

እስከ ተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የባንኮች ቅርንጫፍ ብዛት 8,944 የደረሰ ሲሆን፣ 87 ሚሊዮን የቁጠባ አካውንቶች ተከፍተው፣ 2.2 ሚሊዮን የሚደርሱ ዜጎች ብድር እንዳገኙ የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል፡፡ በ2013 ዓ.ም. ከባንክ ብድር ያገኙ ዜጎች ቁጥር 344,320 የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክነት ከመቀየር ጋር ተያይዞ አምና የነበረው የተበዳሪ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዳንሰራራ ይገለጻል፡፡ ያም ሆኖ ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥር ባላት አገር ለሁለት ሚሊዮን ዜጎች ብቻ የብድር አገልግሎት መቅረቡ የብዙ ጉዳዮችን ቀርነት የሚያሳይ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች