Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተመረጡ ኢንተርፕራይዞች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከኪራይ ነፃ መሬት ሊቀርብላቸው ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተሻለ ፕሮጀክት ቀርፀው ለመሥራት ፍላጎት ላላቸው አምራች ኢንተርፕራይዞች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በጊዜ የተገደበ ከኪራይ ነፃ የለማ መሬት ሊያቀርብላቸው ነው፡፡  

ኮርፖሬሽኑ ይፋ ያደረገው ዕድል በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ በእንጨትና የእንጨት ውጤቶች፣ በኅትመትና ፓኬጅ፣ በምግብና መጠጥ፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽን፣ እንዲሁም በኢንጂነሪንግ መሰል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የተሰማሩ አምራች ኢንተርፕራዞች የሚያቀርቧቸው ፕሮጀክቶችን የሚያወዳድር ነው፡፡ የተመረጡ ኢንተርፕራይዞችን በአዲስ አበባ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አሥር ሔክታር የለማ መሬት ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በኮርፖሬሽኑ የቀረበው ዕድል የቢዝነስ ሐሳብ ያለው ሳይሆን ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት አንድ ተግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

በአገር ውስጥ ያሉ የሥራ ፈጣሪዎችና አነስተኛ አቅም ያላቸው ኢንተርፕራይዞች በቂ ቴክኖሎጂና ዕውቀት፣ አንዳንዴም ፋይናንስ ይዘው በመሬት አቅርቦት ችግር ወደ ሥራ ሳይገቡ ይቀራሉ ብለዋል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ ኮርፖሬሽኑ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በተለይም ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙና ሙሉ የመሠረተ ልማት በተሟላላቸው ፓርኮች ውስጥ የተወሰነውን መሬት ዘርፉን ለማገዝ ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

ፍላጎቱ ያላቸው ድርጅቶች ፕሮፖዛላቸውን እስከ መጪው ሐሙስ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ለኮርፖሬሽኑ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ፕሮፖዛላቸውን መሠረት በማድረግ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ከክፍያ ነፃ የሆነ መሬት ይቀርብላቸዋል ተብሏል፡፡

ኢንተርፕራዞቹ በቀረበላቸው ጊዜ ውስጥ የተሻለ አቅም ከፈጠሩ ከኮርፖሬሽኑ መሬት ሊዝ ማድረግ (መከራየት) የሚችሉ መሆናቸውን፣ በአማራጩ ካልተስማሙ ደግሞ ለሌሎች ኢንተርፕራይዞች እንዲያገለግል የተረከቡትን መሬት ለቀው የሚወጡ እነደሆነ አቶ ሳንዶካን አስረድተዋል፡፡ ዕድሉን የሚያገኙ ኢተርፕራይዞች በለማው መሬት ላይ ኮርፖሬሽኑ በሚያዘጋጀው ስታንዳርድ መሠረት ሼዶችን መገንባት ይጠበቅባቸዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዘርፍን ለመደገፍ ካቀረበው ዕገዛ ጎን ለጎን፣ ሌሎች የልማት አጋሮች እነዚህ አካላትን በሼድ ግንባታ እንዲሁም የፋይናንስና ቴክኒካል ድጋፍ እንዲሰጧቸው ትብብር እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞች ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው የሚሠሩትን ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን ምንነት፣ የሥራ ዕድል ሁኔታ፣ የገበያ መዳረሻዎችን (የአገር ውስጥ ሆነ የውጭ) የተመለከቱ መመዘኛዎችን ተጠቅሞ ምርጫውን የሚያደርግ ይሆናል ተብሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ይህ ያቀረበው ዕድል ውጤት የሚያስገኝ ከሆነ በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ቀስ በቀስ የሚሄድበት ዕድል እንደሚኖር ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ መለሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የመሥሪያ ቦታ አቅርቦትና እንቅስቃሴ በተለያየ አካባቢዎች በተበታተነ ሁኔታ የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል፡፡

የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለብቻቸው ፓርክ ተገንብቶላቸው በክላስተር ሆነው ማምረት የሚችሉበት ዕድል እንዲፈጠር ተቋሙ ለባለድርሻ አካላት ያቀረበው አማራጭ መኖሩን የተናገሩት አቶ አሸናፊ፣ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቀረበው ዕድል ኢንተርፕራይዞችን በፓርክ ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ የማለማመድ ዕርምጃ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ50 እሰከ 60 ሺሕ ብር በሚደርስ ወጪ የመሥሪያ ቦታዎችን እንደሚከራዩ ያስታወሱት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ ኢንዱስትሪዎቹ ተጨማሪ ኢንቨስት ለማድረግ፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ለመገንባት እንዳይችሉ ገድቧቸዋል ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ውስጥ ለኢንተርፕራይዞቹ የቀረበው ዕድል መሬት ብቻ ሳይሆን ከመሬት ጋር ተያያዥ የሆኑ የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን የሚመልስ በመሆኑ፣ በትልቅ ዕድልነቱ የሚወሳ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች