Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለገበያ ከሚቀርበው እየተቀነሰ መጠባበቂያ ዘር የሚያዝበትን ሥርዓት የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘር አምራቾች በየዓመቱ ከሚያባዙትና ለገበያ ከሚቀርበው የሰብል ዘር ውስጥ እየተቀነሰ፣ አጣዳፊ የዘር እጥረት በሚያጋጥምበት ጊዜ የሚሠራጭ፣ ክምችት የሚያዝበትን ሥርዓት የሚዘረጋ የዕፅዋት ዘር ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

አዋጁን ያዘጋጀው የግብርና ሚኒስቴር በረቂቁ ላይ የተቀመጠውን ሥርዓት በመዘርጋት፣ ከዚህ ቀደም እጥረት በሚያጋጥም ጊዜ ለምግብነት የሚውል እህል ከገበያ እየተገዛ አርሶ አደሮች እንዲዘሩት የሚቀርብበትን አሠራር ለማስቀረት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ሚኒስቴሩ የመጠባበቂያ ዘር ክምችት ሥርዓትን ሲዘረጋ መንግሥት በየዓመቱ ለአገር ውስጥ ገበያ ከሚቀርበው ዘር ውስጥ በቀጣይ በደንብ የሚወሰነውን መጠን ያህል ዘር እየገዛ እንደሚያስቀምጥ፣ በሚኒስቴሩ የዝርያ ለቀቃና ምዝገባ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መደምደሚያው ነቅንቄ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሚዘረጋው ሥርዓት አሁን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለአደጋ ጊዜ በሚል በየዓመቱ እህል ከሚገዛበት አሠራር ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው፤›› ያሉት አቶ መደምደሚያው፣ ለዘር ክምችቱ ግዥ የሚውለው በጀት ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚመደብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛ ባለሙያው እንደሚያስረዱት በአገሪቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የዘር እጥረት የሚያጋጥም ሲሆን፣ ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመከሰቱ ምክንያት የዘር እጥረት “በከፍተኛ መጠን” ተፈጥሯል፡፡ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያትም በምዕራብ ኢትዮጵያ የተዘራው የበቆሎ ዘር አለመሰብሰቡንም አክለዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም. የወጣውና አሁን ሊተካ የተዘጋጀው የዕፅዋት ዘር አዋጅ በአገሪቱ ውስጥ አጣዳፊ የዘር እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት፣ የግብርና ሚኒስቴር እጥረት ባጋጠመባቸው አካባቢዎች “የአስቸኳይ ጊዜ ዘር” እንዲቀርብ ፈቃድ እንደሚሰጥ ተደንግጓል፡፡

አቶ መደምደሚያው እንደሚያስረዱት፣ የዘር ዕጥረት አጋጥሞ በሚታወጅበት ጊዜ ለገበሬው ለማቅረብ የሚሰበሰበው ዘር ከገበያ የሚሰበሰብና ለመዘራት ሳይሆን ለእህልነት የሚዘጋጅ ነው፡፡ ከገበያ ተሰብስቦ ለዘርነት ሚውለው እህል ምንጩ ከየት እንደሆነ መታወቅ ያለበት ቢሆንም፣ ዘሩ ለገበሬዎች ከመቅረቡ በፊት በቤተ ሙከራ የሚደረግለት ፍተሻ የሚበቅል መሆኑና አለመሆኑን ለማረጋገጥ ብቻ መሆኑን ከፍተኛ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚሠራጨው ዘር የሚፈለገውን ምርታማነትና ጥራት እንደማያሟላ ገልጸው፣ ‹‹አስቀድሞ የጥራት ደረጃው ያላሟላ ተብሎ የወደቀ ቢሆንም ከበቀለ ብቻ ተሰብስቦ ይሠራጫል፤›› ሲሉ አሁን በሥራ ላይ ያለው አሠራር ያለበትን ችግር አስረድተዋል፡፡

የጥራት፣ የምርታማነትና በሽታ የመቋቋም ደረጃዎችን ያለፈ ዘርን በመጠባበቂያነት የሚከማችበትን ሥርዓት በመዘርጋት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ያቀረበው የግብርና ሚኒስቴር፣ ሐሙስ ጥቅምት 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ወደ ግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተመራው ረቂቅ አዋጅ ላይ “የመጠባበቂያ ዘር ሥርዓት” እንደሚዘረጋ አሥፍሯል፡፡

ለምክር ቤቱ የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የነበሩ ግምገማዎች በአገሪቱ የዘር እጥረት መኖሩን ከመጠቆም ይልቅ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል አገራዊ አቅም መገንባት አላስቻለም፡፡

“በመልካም ዓመታት የተትረፈረፈ ምርጥ ዘር” የሚገኝበት ሁኔታ መኖሩን የሚገልጸው ረቂቅ አዋጁ፣ በዓመት እስከ 400 ሺሕ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ሳይውል ለቀጣይ ዓመት ያደረበት ጊዜ መኖሩን በማሳያነት ይጠቅሳል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜያት የሚያድር ምርጥ ዘር በአብዛኛው እንደሚሸጥ የተወሰነው መጠን ደግሞ፣ በወረዳና በኅብረት ሥራ ማኅበራት መጋዘን ውስጥ ተበላሽቶ እንደሚወገድ ማብራሪያው ያስረዳል፡፡

‹‹ሥርዓት አበጅተን ዘሩ በአግባቡ ቢያዝ እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ቀዝቃዛ ቦታ በማስቀመጥ የዘር አቅርቦት ዋስትናን ማረጋገጥ ይቻላል፤›› ሲል የረቂቁ ማብራሪያ የሥርዓቱ አስፈላጊነትን ይገልጻል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ሥርዓት ለመዘርጋት ከሌሎች ሚኒስቴር ተቋማት ጋር የሚቀናጅ ሲሆን፣ ለሥርዓቱ ዝርጋታ ከአንድ በላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ሥርዓቱ የሚዘረጋው በሚኒስቴሮች ምክር ቤት በሚወጣ ደንብ ነው፡፡ ገንዘብ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለድርሻ እንደሚሆኑ አቶ መደምደሚያው ተናግረዋል፡፡

በዓመት ውስጥ ከሚቀርበው ዘር ውስጥ ምን ያህል በመቶው ለመጠባበቂያ ይያዝ የሚለው በደንቡ እንደሚወሰን ያስረዱት ከፍተኛ ባለሙያው፣ ብዙዎቹ አገሮች ከአጠቃላዩ ውስጥ አሥር በመቶ በመጠባበቂያነት የመያዝ ልምድ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡

በዓመት ውስጥ የተያዘው መጠባበቂያ በቀጣዩ ዓመት የዘር እጥረት ሳያጋጥም ቀርቶ ጥቅም ላይ የማይውል ከሆነ፣ ለእህልነት እንዲቀርብ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን አስረድተዋል፡፡ 

አቶ መደምደሚያው ሥርዓቱን የሚመራ ራሱን የቻለ ተቋም ሊቋቋም እንደሚችል ተናግረዋል፣ ሚኒስቴሩ ግን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መጠባበቂያ ዘር የመያዙን ሥራ እንዲሠራ ጊዜው ሲያልፍ ተቋሙ ራሱ በእህልነት እንዲያሠራጨው ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች