Tuesday, November 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የጦርነቱ አስከፊ ምዕራፍ በአስተማማኝ ሰላም ይቋጭ!

የጦርነት አንደኛው አስከፊ ገጽታ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያስከትለው ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ መራብና መጠማት፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች አስከፊ ወንጀሎች ከብዙ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ በሰላማዊ ወገኖች ላይ የተፈጸሙ አሳዛኝ የመብት ጥሰቶችና ፆታዊ ጥቃቶች ያስከተሉት ጠበሳ አይረሳም፡፡ በጦርነቱ ምክንያት በሦስቱም ክልሎች ውስጥ በርካቶች ሲሞቱ፣ ሲፈናቀሉ፣ ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ስብራት ሲዳረጉም ተስተውሏል፡፡ በእነዚህና በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ የደረሰባት መዋከብም አይዘነጋም፡፡ እስካሁን ድረስም ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ ጫናዎችም እየተደረጉባት ነው፡፡ መሰንበቻውን መንግሥት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል የመንግሥት ተቋማትን፣ አውሮፕላን ማረፊያዎችንና መሠረተ ልማቶችን በመቆጣጠር ሰብዓዊ ዕርዳታዎችንና አገልግሎቶችን ለክልሉ ነዋሪዎች ለማቅረብ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከአፋር ክልል በተጨማሪ በአማራ ክልል በጎንደር – ሽሬ መስመርና በወልዲያ – ኮረም መስመር የዕርዳታ አቅርቦቱን ለማቀላጠፍ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጿል፡፡ ሰሞኑን በትግራይ ክልል መንግሥት በያዛቸው አካባቢዎች ዕርዳታ ማከፋፈል ጀምሯል፡፡ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ባንክና መሰል አገልግሎቶች እንደሚጀመሩም ይጠበቃል፡፡

መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት የበላይነት ይዞ በትግራይ ክልል ውስጥ ከተሞችን እየተቆጣጠረ መሆኑ ይፋ ከተደረገ በኋላ፣ የተለያዩ የውጭ አካላትም ሆኑ መንግሥትን የሚቃወሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ማስታወቅ ጀምረዋል፡፡ መንግሥት በበኩሉ ሠራዊቱ በጥብቅ ዲሲፕሊን እየተመራ የትግራይ ክልልን ከሕወሓት ኃይሎች ነፃ እንደሚያወጣ በማስታወቅ፣ በተለያዩ አካላት የሚወጡ መረጃዎችን መሠረት ቢስ መሆናቸውን እያስገነዘበ ነው፡፡ ጦርነቱ ከጦር መሣሪያ በተጨማሪ በፕሮፓጋንዳ ጭምር የሚከናወን በመሆኑ፣ መንግሥት በተቻለ መጠን በየደረሰባቸው አካባቢዎች ያለውን እውነታ በግልጽ ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በዘለለም በችግር ውስጥ ላሉ ወገኖች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕርዳታ እንዲያቀርብ በማድረግ፣ እንዲሁም ሰላማዊ ሰዎች ማናቸውም ዓይነት ጥቃቶችና የመብት ጥሰቶች እንዳላጋጠማቸው ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በተለይ መንግሥት በተቆጣጠራቸው ሥፍራዎች ሚዲያዎች፣ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በአካል እንዲገኙና ትዝብታቸውን እንዲያካፍሉ መፍቀድ ይጠበቅበታል፡፡ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ውል በሌላቸው መረጃዎች ተገቢ ያልሆነ ድምዳሜ ላይ እንዳይደርስም፣ በአገር ውስጥ ያሉ ዲፕሎማቶች ነባራዊውን ሁኔታ እንዲገነዘቡ ማድረግም ይገባል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የምዕራባውያን ኮርፖሬት ሚዲያ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ዓይኖቻቸው ኢትዮጵያ ላይ ስለሆኑ ለዜጎች ደኅንነት የሚሰጠው ትኩረት በጣም መጨመር አለበት፡፡ ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት የቀሩት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በቅርቡ ሊጠናቀቅ ይችላል ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት፣ ከዚህ ቀደም ያጋጠሙ የዘፈቀደ ዕርምጃዎችና ጥሰቶች እንዳይከሰቱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ዓለም ከሩሲያና ከዩክሬን ቀጥሎ ዓይኖቹን የጣለው ኢትዮጵያ ላይ ስለሆነ፣ በከፍተኛ ጨዋነትና ዲሲፕሊን የጦርነቱን አስከፊ ምዕራፍ መዝጋት የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ አስከፊ ጦርነት ምክንያት በተደጋጋሚ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተጠርታለች፡፡ በተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ተወንጅላለች፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች ገጽታዋ ተበላሽቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ተስፋ ቢስ እንደሆነች ተደርጋ ተስላለች፡፡ ጦርነቱ ኢኮኖሚውን እያደቀቀ የዜጎችን ኑሮ ከማክፋቱና የሚሊዮኖችን ደኅንነት ከማወቃወሱም በላይ፣ በዓለም ላይ የነበራትን መጠነኛ ተቀባይነትና ተደማጭነት አሳጥቷታል፡፡ የዚህ አስከፊ ጦርነት መቋጫ እነዚህን ችግሮች ሁሉ ያገናዘበ ይሁን፡፡

መንግሥት በክልሉ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎችን ሲቆጣጠር ነዋሪዎችን ማረጋጋት፣ የምግብ፣ የመድኃኒትና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶችን ማከናወንና አላስፈላጊ እንቅስቃሴዎችን መግታት ይኖርበታል፡፡ ከማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ውጪ በቆዩ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች ከፍተኛ የሠራዊት እንቅስቃሴ ሲመለከቱ ሊረበሹ ስለሚችሉ፣ ደኅንነታቸው አስተማማኝ እንደሆነ በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ሁኔታዎች አመቺ ከሆኑ ደግሞ ከነዋሪዎች ውስጥም ሆነ ከሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት፣ ሰላም እንዲሰፍን የሚደረገው ጥረት እንዲጠናከር ማድረግ ይገባል፡፡ ከረድዔት ሠራተኞች በተጨማሪ የሕክምና ባለሙያዎችንና ሌሎች ድጋፍ ሰጪዎችን ጭምር በማሰማራት ወገናዊነትን ማሳየት፣ ጦርነቱ በፍጥነት መልክ ይዞ ሰላም እንዲረጋገጥ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ጦርነቱ በሕዝብ መካከል መቃቃር የሚፈጥሩ ፕሮፓጋንዳዎች የተረጩበት ስለሆነ፣ ነባሩን የሕዝብ ለሕዝብ መደጋገፍ አኩሪ እሴት በዚህ ወቅት ማሳየት ለአገር ህልውና ጭምር ይጠቅማል፡፡ ጦርነቱ ከተፋላሚዎቹ ባሻገር የውጭ አካላትን በፕሮፓጋንዳው መስክ ያሳተፈ በመሆኑ፣ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ፈጣንና አስተማማኝ ሥራ ማከናወን ተከትለው ሊመጡ የሚችሉትን አሉታዊ ነገሮች ለማምከንም ይረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲህ ዓይነቱን የተቀደሰ ተግባር ይደግፋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የሚካሄደው የሰላም ንግግር ቀጠሮ እንደተያዘለት ተሰምቷል፡፡ የሰላም ንግግሩ በጥሩ መንፈስ ከተካሄደ ወደ ድርድር በመሸጋገር ዘለቄታዊ ሰላም ለማስፈን እንደሚረዳ ይታመናል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከጦርነቱ ጎን ለጎን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻው በመስፋፋቱ፣ በዚህ ዘመቻ ውስጥ የውጭ ኃይሎች ጭምር በሰፊው ተሳታፊ በመሆናቸው አስቸጋሪ ሁኔታዎች ይታያሉ፡፡ የሰላም ንግግሩ ሊሳካ የሚችለው ውጫዊ ጣልቃ ገብነቱ ሲገታና መተማመን ሲፈጠር ነው፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ሰላም ሰፍኖ ዕፎይታ እንዲገኝ፣ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ አጉል ድርጊቶች መወገድ አለባቸው፡፡ በጦርነቱ ውስጥ የቆዩት የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልሎች ዜጎች አስተማማኝ ሰላም የሚያገኙት ግጭት የሚያነሳሱ ድርጊቶች ሲቆሙ ነው፡፡ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ወገኖች ምግብ፣ መድኃኒት፣ መጠለያ፣ መልሶ መቋቋሚያና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች የሚቀርቡላቸው ሰላም ሲሰፍን ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በጦርነቱ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን፣ ንብረታቸውንና ጤናቸውን ጭምር አጥተዋል፡፡ በእነሱ ስም መነገድም ሆነ መቆመር ተገቢ አይደለም፡፡ ከሕዝብና ከአገር ደኅንነት በላይ የሚቀድም ምንም ነገር ስለሌለ፣ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መረባረብ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከሩሲያና ከዩክሬን ቀጥሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ በመሆኑ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በምዕራባውያን ኃይሎች እየደረሰ ያለው ጫና እየከበደ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም በተደጋጋሚ ድምፃቸውን ቢያሰሙም፣ የውጭ ኃይሎች ፍላጎት የገዛ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የተጠና ስለሆነ ግፊቱ እያየለ ነው፡፡ ይህ አውዳሚ ጦርነት በፍጥነት ተቋጭቶ ሰላም ማስፈን ካልተቻለ ጫናው ዘርፈ ብዙ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ምዕራባውያን ከማዕቀብ ጀምሮ እስከ ወታደራዊ ኃይል መጠቀም ድረስ የሚሄዱበት ታሪክ ስላላቸው፣ ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ጥያቄ ደንታ አይኖራቸውም፡፡ መንግሥት ይህንንና ሌሎች መሰል አሳሳቢ ችግሮችን በመገንዘብ፣ ለአስከፊው ጦርነት መቋጫ የሚረዱ ጉዳዮች ላይ ያተኩር፡፡ ጦርነቱ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተመልሶ እንዳያገረሽና ሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት እንዳያጋጥም፣ በተቻለ መጠን ዕፎይታ የሚፈጥሩ ዘለቄታዊ ተግባራት ይከናወኑ፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን ማሳሰብ የምንፈልገው አስከፊው የጦርነት ምዕራፍ በአስተማማኝ ሰላም እንዲቋጭ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ

ለሲኒመር ትሬዲንግ አ/ማ አባላት በሙሉ የጠቅላላ ጉባኤ የስብሰባ ጥሪ ሲኒመር ትሬዲንግ...

የባህር በር በቀጣናዊ ተዛምዶ ውስጥ

በበቀለ ሹሜ መግቢያ በ2010 ዓ.ም. መጋቢት ማለቂያን ይዞ ዓብይ አህመድ በጠቅላይ...

ሥጋት ያስቀራል ተብሎ የሚታሰበው የጫኝና አውራጅ መመርያ

በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መልኩ በመደራጀት ማኅበረሰቡ ላይ እንግልትና...

ማወቅ ወይስ አለማወቅ – ድፍረት ወይስ ፍርኃት?

በአሰፋ አደፍርስ ወገኖቼ ፈርተንም ደፍረንም የትም አንደርስምና ለአገራችን ሰላምና ክብር...

ከድህነት ወለል በታች ከሆኑት አፍሪካዊያን ውስጥ 36 በመቶው በኢትዮጵያ ናይጄሪያና ኮንጎ እንደሚገኙ ተጠቆመ

‹‹ለሺሕ ዓመት በድህነት ውስጥ የነበረች አገርን በአሥር ዓመት ልንቀይር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...

አስጨናቂውን የኑሮ ውድነት የማርገብ ኃላፊነት የመንግሥት ነው!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ካቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል አንደኛው የኑሮ ውድነትን በተመለከተ ነበር፡፡...