Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካፒታሉን ወደ 300 ቢሊዮን ብር ሊያሳድግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ካፒታሉን ወደ 300 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የካፒታል ማሻሻያ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ  አቀረበ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ያለውን 100 ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሳደግ ያቀረበው ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ ቀርቦ እየታየ ሲሆን፣ ቦርዱ ተወያይቶ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡

‹‹አሁን ያለንን 100 ቢሊዮን ብር ካፒታል ማሳደግ የፈለግንበት ምክንያት፣ ወሮታችን ከፍ እያለ በመምጣቱ ሲሆን፣ በቅርቡ ያፀድቁልናል ብለን እናስባለን፤›› ሲሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል፡፡

የአየር መንገዱ የካፒታል ማሻሻያ ጥያቄ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ቦርድ ቀርቦ እየታየ እንደሚገኝ ሪፖርተር ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕም አረጋግጧል፡፡

አቶ መስፍን አክለውም የምናንቀሳቅሰው ገንዘብ እያደገ በመምጣቱና የካፒታል ማሻሻያ ከሌለ ትክክለኛ የፋይናንስ አያያዝ ለመፍጠር ስለሚያስቸግር መሆኑን በመግለጽ የካፒታል ማሻሻያ ጥያቄውን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም አሁንም አዳዲስ አውሮፕላኖች እያስመጣን ነው፡፡ በምናስመጣበት ወቅት የዕዳና ካፒታል ምጣኔ መመጣጠን አለበት፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የአውሮፕላን የሚገዛው በብድር ስለሆነ አበዳሪዎቹ ጋ ተቀባይነት እንዲያገኝ ከፍ ያለ የሀብት መጠን መድረስ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

የዕዳና ካፒታል ምጣኔ ተቋሙ ካለው ካፒታል አንፃር ሲታይ ምክንያታዊ ካልሆነ አበዳሪዎቹ ለማመን እንደሚቸገሩ አቶ መስፍን ገልጸዋል፡፡

አየር መንገዱ ከሰኔ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር መተዳደር የጀመረ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥት ልማት ድርጅት ሥር ነበር፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ከገቡት 27 ድርጅቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት ከአምስት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡

በተጨማሪም አየር መንገዱ በ139 አውሮፕላኖች ወደ ተለያዩ ዓለማት በረራ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ ከ66 በላይ የበረራ መዳረሻዎች ላይ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡   

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2012 ዓ.ም. 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

በወቅቱ 110 የመንገደኛና 17 የጭነት በድምሩ 127 መዳረሻዎች ያሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ 91 መዳረሻዎች መዘጋታቸው የወረርሽኙን ተፅዕኖ ያሳያል፣ በዚህም 19 የመንገደኞች መዳረሻዎች ብቻ ቀርተው ነበር።                                                                                                                                                                                        የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ኢንዱስትሪው በኮቪድ-19 ተፅዕኖ ሥር በወደቀበት ወቅት መንገደኞችን በማጓጓዝ ይገኝ የነበረውን ገቢ በጭነት አገልግሎት አካክሶ ነበር፡፡

አየር መንገዱ በፈረንጆቹ 2025 ቀዳሚው የአፍሪካ አየር መንገድ ለመሆን እየሠራ የሚገኝ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ከአንዳንድ የአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በሽርክና በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቶጎው ስካይ፣ የማላዊ፣ የዛምቢያ፣ የኮንጎና የናይጄሪያ አየር መንገዶች ስኬት እንዲያስመዘግቡ በሽርክና ለመሳተፍ ካቀዳቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች