Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትተግባራዊነታቸው የሚጠበቀው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዳዲስ መመርያዎች ምን ይዘዋል?

ተግባራዊነታቸው የሚጠበቀው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዳዲስ መመርያዎች ምን ይዘዋል?

ቀን:

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በ2014 ዓ.ም. በሐዋሳ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የፀደቁና የተሻሻሉ መመሪያዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ በመድረኩ አቅርቦ የተወያየባቸውን አምስት የተለያዩ ጉዳዮች ተመካክሮና ከባለድርሻ አካላት የተሰጡትን አስተያየቶችን ተቀብሎ ሥራ ላይ ያውለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተወያየባቸው አምስት ጉዳዮች  የባለድርሻ አካላት ድጋፍ አሰጣጥ መመርያ፣ የአሠልጣኞች ደረጃ መስጫ ሰነድ፣ የውጭ ጉዞ ሥርዓት፣ የአትሌት ተወካዮችና የማናጀር ፈቃድ እንዲሁም የአትሌቶች የውጭ ጉዞ መመርያ ሰነድ ናቸው፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ከበላድርሻ አካላት ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል የብሔራዊ አትሌቶችና የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምርጫ ጋር መመርያ ተፈጻሚነት ላይ ክፍተቶች እንዳሉ ተጠቁመዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምርጫን በተመለከተ

አኅጉርና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ሲቃረቡ ከሚያከራክሩት የአትሌቶች ምርጫ ባሻገር የአሠልጣኞች መመረጥ ነበረብኝ የሚል ክስ የተለመደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የብሔራዊ ቡድኑን እንዲሁም የአትሌቶችን ሥነ ልቦና ሲረብሽ ተስተውሏል፡፡ በቅርቡ እንኳን በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ተካተው የነበሩ አትሌቶች  የግል አሠልጣኞቻቸው አብረዋቸው መጓዝ ባለመቻላቸው አንጓዝም መለታቸው ይታወሳል፡፡

የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች ምርጫን በተመለከተ በክፍል ሦስት አንቀጽ ስምንት የተለያዩ ነጥቦች ተዘርዝረዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየወቅቱ በአኅጉር፣ በዓለም አቀፍና በኦሊምፒክ ደረጃ ለሚካሄዱ የአትሌቲክስ ውድድሮች አገርን ወክለው ለሚሳተፉ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ተገቢ አሠልጣኞችን በሙያ ደረጃ፣ በወቅታዊ ብቃት በውጤታማነትና በልምድ ወዘተ ለአትሌቲክስ አሠልጣኞች ደረጃ መስጫ (ስታንዳርድ) መሠረት በማድረግ አወዳድሮ እንደሚመድብ ይጠቅሳል፡፡

በዚህም መሠረት ለብሔራዊ ቡድን አሠልጣኞች መምረጫ መሥፈረት በመቶኛ የተቀመጠ ሲሆን፣ የአሠልጣኙ ደረጃ 30 በመቶ፣ አትሌት አሠልጥኖና አብቅቶ ያስመረጠ 60 በመቶ፣ እንዲሁም የአሠልጣኝነት ልምድ 10 ከመቶ  ማሟላት ይኖርበታል፡፡ ከላይ ለተጠቀሰው ማብራራያ የተቀመጠ ሲሆን የተለያዩ የዓለም አቀፍ አትሌቲክስን የአሠልጣኘነት ሥልጠና የወሰደ ስድስትና ከስድስት በላይ አትሌት ማስመረጥ የቻለ እንደሁም ከአሥር ዓመት በላይ የአሠልጣኝነት ልምድ ያለው በአዲሱ መመርያ መሠረት ተቀባይነት እንደሚኖረው ያስቀምጣል፡፡

ፌዴሬሽኑ ይፋ ያደረገው መመርያ የተወሰኑ ግለሰቦችን ጥቅም ብቻ ከግምት ውስጥ አስገብቶ የወጣ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰነዝሩ አሉ፡፡

‹‹የሚወጡት መመርያዎች የተወሰኑ ወገኖች ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ የወጣው መመርያ በትምህርት እንዲሁም በልምድ ያላቸውን አሠልጣኞች ዕድል የሚሰጥ ቢሆንም ወረቀት ላለው የበለጠ ቦታ ይሰጣል፤›› በማለት አሠልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡

እንደ አሠልጣኙ አስተያየት ከሆነ በመመርያው መሠረት በትምህርት አሠልጣኝ የሆነ እንዲሁም ልምድ ላለው ዕድል የሰጠ ቢሆንም፣ ሁሉም አሠልጣኝ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም ኦሊምፒክ ላይ ባመጡት ውጤት መገምገም ይኖራባቸዋል ይላሉ፡፡

‹‹አምስት አትሌቶች የተሰጠው አሠልጣኝ አንዱን ብቻ ውጤታማ አድርጎ ቀሪዎችን ያጠፋ አሠልጣኝ ወረቀት ስላለው ብቻ የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ መሆን አለበት ማለት ተገቢ አይደለም፡፡›› አሠልጣኝ ተሰማ ያክላል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መመርያውን ተግባራዊ በሚያደርግባቸው ጊዜያት በአትሌቲክሱ መስክ የሚከሰቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ለውጦችን አዳዲስ አስተሳሰቦችን ውሳኔዎችን የውድድሮችን ስፋት እንዲሁም ክብደትና የቆይታ ጊዜ፣ የፌደሬሽኑን የፋይናንስ አቅምን ከግንዛቤ በማስገባት የተለያዩ ተጨማሪ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ መሆኑን ያብራራል፡፡

የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች መመልመያና መምረጫ መመርያ

ሌላኛው ሻምፒዮናዎች በተቃረቡ ወቅት አጨቃጫቂ ጉዳይ ሆኖ የዘለቀው የአትሌቶች ምርጫ ነው፡፡ ምንም እንኳን አትሌቶች የተወዳደሩበት ውድድርና ሰዓታቸው በግልጽ ቁልጭ ብሎ ቢቀመጥም ሁሌም ክርክር ሳያስነሳ ቀርቶ አያውቅም፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ሲቀመጡ ቢስተዋልም የክለቦች ጫና ለምርጫው ክርክር መንስዔ መሆናቸው ይነሳል፡፡

አዲስ በወጣው መመርያ መሠረት በምርጫው የሚሳተፉ አትሌቶች በውድድር ዓመቱ እንደ ፊልዱ ባህሪ ተደጋጋሚና ተከታታይነት ያለው የውድድር ብቃት (ከሁለት ያላነሰ) ሊያሳዩ ይገባል፡፡ ይህም ከሌሎች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ያስችላል ይላል፡፡

በምርጫው የሚሳተፉ አትሌቶች ወርልድ አትሌቲክስ (የዓለም አትሌቲክስ) ባወጣው የሚኒማ ነጥብ መሠረት የተሻለ ውጤት ያስመዘገበ በሚለው እንጂ በቀድሞ ዝና እና የክብረወሰን ባለቤትነት የሚመዘን እንደማይሆን ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም በምርጫው በሚሳተፉ አትሌቶች ቀድመው የተመዘገቡ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና ውጤቶችን የዓለም አትሌቲክስ ለውድድሩ በሚደነግገው ወቅታዊ የሚኒማ ሕገ ደንብ መሠረት የሚስተናገዱ ሲሆን፣ በዚህ መመርያ ውስጥ  የአትሌቶች ደረጃ የሚያዘው ከአንደኛ እስከ አሥረኛ (ምርጥ አሥር) ደረጃ ያገኙ አትሌቶች ብቻ የሚካተቱት ናቸው፡፡

በተጨማሪም አንድ አትሌት በውድድር ዓመቱ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና  የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ጨምሮ ሚኒማ ማምጫ ማብቂያ ጊዜ  ለፊልዱ በተቀመጠው መጠንና የጊዜ ልዩነት ብቻ መሮጥ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

የማራቶን እኛ የግማሽ ማራቶን አትሌቶች ምርጫ

የዓለም አትሌቲክስ ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት የፕላቲኒየም ደረጃ ማራቶን ከወርቅ ደረጃ ማራቶን የበለጠ ነጥብ የሚያገኝ ሲሆን፣ የወርቅ ደረጃ ማራቶን ከብር ደረጃ ማራቶን የበለጠ ነጥብ ክብደት ያገኛል፡፡ በዚህም አንድ አትሌት  ከአንድ እስከ አሥር ካሉት በአንዱ መሥፈርት ብቻ ውጤት ያገኛል፡፡ በሁለት ማራቶኖች ድምር ውጤት የተሻለ ደረጃ ያስመዘገበ አትሌት የበለጠ ነጥብ ያገኛል፡፡

ተጨማሪም የማራቶን ውጤት የሚያዘው የዓለም አትሌቲክስ በሚደነግገው የዓለም አትሌትክስ ሻምፒዮና እንዲሁም ኦሊምፒክ በሚካሄድበት ቅድመ የውድድር ዓመት ከነሐሴ እስከ ሚኒማ ማምጫ ማብቂያ ጊዜ ባለው ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ ውጤት ብቻ ይታያል፡፡

በዚህ መመርያ ውስጥ በማንኛውም የማራቶን ውድድር የአትሌቶች ደረጃ የሚያዘው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ (ምርጥ አምስት)  ያገኙ  ብቻ ናቸው፡፡

በሁለት ማራቶኖች ድምር ውጤት ሁለት አትሌቶች እኩል ነጥብ ቢያመጡ በቅርብ በተደረገ ውድድር የተሻለ ደረጃ ያለው አትሌት የተሻለ ደረጃ ያገኛል፡፡ ነገር ግን በዚህም መሥፈርት እኩል ነጥብ ቢያመጡ በድምር ሰዓት አነስተኛ ሰዓት ያመጣ አትሌት የተሻለ ደረጃ እንደሚያገኙ ይገልጻል፡፡

አንድ አትሌት በውድድር ዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኦሊምፒክን  ጨምሮ ከነሐሴ/ኦገስት እስከ ውድድሩ ሚኒማ ማምጫ ማብቂያ ጊዜ ውስጥ ቢበዛ ሁለት ማራቶን ብቻ መሮጥ አለበት፡፡ ከሁለት ማራቶን በላይ የሮጠ አትሌት በምርጫው ውስጥ አይካተትም፡፡

አንድ አትሌት በማንኛውም ማራቶን ውድድር ገብቶ ካቋረጠ እንደተወዳደረ ይቆጠራል፡፡ በተጨማሪም አንድ አትሌት በማንኛውም የግማሽ ማራቶን ውድድር ገብቶ ካቋረጠ እንደተወዳደረ ይቆጠራል፡፡

በተጠባባቂነት የተመረጠ አትሌት ለቡድኑ በተመረጠው አሠልጣኝ፣ በሥልጠና ቦታው የመሠልጠን በተመረጠው ሆቴል አብሮ መኖር አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በፌዴሬሽኑ የሥነ ምግባር መመርያ መሠረት አስፈላጊው ዕርምጃ ይወሰድበታል፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት መሥፈርቶች እንደተጠበቁ ሆኖ ልዩ ሁኔታ ሲከሰት የሦስተኛው አትሌት ምርጫ በቴክኒክ ኮሚቴው ከታየና አዎንታ ካገኘ በኋላ በፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡

አትሌቶች በሥልጠና ሒደት ውስጥ በወቅቱ በቶሎ በማይሻልና ወደ ሙሉ ሥልጠና በማይመልስ ዘላቂ ሕመም ወይም ከፍተኛ ወይም የቆየ አደጋ ወይም በሳይንሳዊ ዘዴዎችና ምዘናዎች በተረጋገጠ ብቃት ማነስ መኖሩ ሲረጋገጥ ከቡድኑ ይቀነሳሉ፡፡

በሌላ በኩል የዓለም አትሌቲክስ ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት የወርቅ ደረጃ የግማሽ ማራቶን ከብር ደረጃ ማራቶን የበለጠ ነጥብ ወይም ክብደት እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ አንድ አትሌት ከመሥፈርት ከአንድ እስከ ዘጠኝ ካሉት በአንዱ መሥፈርት ብቻ ውጤት እንዲያገኝ ይደረጋል። በሁለት የግማሽ ማራቶኖች ድምር ውጤት የተሻለ ደረጃ ያስመዘገበ አትሌት የበለጠ ነጥብ ያገኛል፡፡

የግማሽ ማራቶን ውጤት የሚያዘው የዓለም አትሌቲክስ) በውድድር ዘመኑ በሚደነግገው የሚኒማ ማምጫ ጊዜ ከሚኒማ ማምጫ ጀምሮ እስከ ሚኒማ ማምጫ ማብቂያ ጊዜ ውስጥ የተመዘገበ ውጤት ብቻ ነው፡፡

በዚህ መመርያ ውስጥ በማንኛውም የግማሽ ማራቶን በተደረጉ ውድድሮች የአትሌቶች  ደረጃ የሚያዘው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ያገኙ አትሌቶች ብቻ ነው፡፡

በሁለት የግማሽ ማራቶኖች ድምር ውጤት ሁለት አትሌቶች እኩል ነጥብ ቢያመጡ በቅርብ በተደረገ ውድድር የተሻለ ደረጃ ያለው አትሌት የተሻለ ደረጃ ያገኛል፡፡ ነገር ግን በዚህም መሥፈርት እኩል ነጥብ ቢያመጡ በድምር ሰዓት  አነስተኛ ሰዓት ያመጣ አትሌት የተሻለ ደረጃ ያገኛል፡፡

አንድ አትሌት በውድድር ዓመቱ በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና በተሰጣቸው ውድድሮች ለውድድሩ በተፈቀደው የሚኒማ ማምጫ ጊዜ ውስጥ ቢበዛ ሁለት የግማሽ ማራቶን ብቻ መሮጥ አለበት፡፡ ከሁለት የግማሽ ማራቶን በላይ የሮጠ አትሌት በምርጫው ውስጥ አይካተትም፡፡

በዚህ የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ምልመላና የአሠልጣኞች ምርጫ መመርያ ላይ ትርጉምና ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዩች ሲያጋጥሙ፣ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው ባለሙያ፣ የቴክኒክ ኮሚቴ ወይም የፌዴሬሽኑን የሕግ አማካሪ በማስተርጎምና ማብራሪያዎችንም በማካተት የመተርጎም ሥልጣን አለው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...