Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአሜሪካ ሴናተሮች የተኩስ አቁም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጻፉ

የአሜሪካ ሴናተሮች የተኩስ አቁም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጻፉ

ቀን:

የሰላም ንግግሩ ለስድስት ቀናት ይቆያል ተብሏል

የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ይጀመራል በተባለበት ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰባት የአሜሪካ ሴናተሮች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በጻፉት ደብዳቤ በአፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ፡፡

ከሪፐብሊካኖችና ከዴሞክራቶች የተውጣጡት እነዚህ ሴናተሮች፣ ‹‹የተጀመረው የሰላም ንግግር በአስቸኳይ በተኩስ አቁም መደገፍ እንዳለበት እናሳስባለን፤›› በማለት ደብዳቤውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የላኩ ሲሆን ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠ መልስ የለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን መሞታቸውንና 2.5 ሚሊዮን ዜጎች መፈናቀላቸውን ሴናተሮቹ የጻፉት ደብዳቤ ያትታል፡፡ ደብዳቤውን ከጻፉት የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል (HR 6600) ስፖንሰር ያደረጉት ሴናተር ክሪስ ኩንስ ይገኙበታል፡፡

በተያያዘ ዜና በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት ያህል የቀጠለው ጦርነት በጥምር ጦሩ አሸናፊነት እየተጠናቀቀ በሚመስልበት አሥራ አንደኛው ሰዓት፣ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሰላም ንግግር ለስድስት ቀናት እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡

ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሰላም ንግግር፣ እስከ እሑድ ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚቀጥል የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ቃል አቀባይ ትናንትና በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ቪንሴንት ማግዌንያ እንደገለጹት፣ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ስሪል ራማፎሳ ድርድሩን ለማስተናገድና ድጋፍ ለማድረግ የተስማሙት የአፍሪካ ኅብረት ጥያቄ ማቅረቡን ተከትሎ ነው፡፡ ‹‹የሰላም ንግግሩን አስተናጋጅ በመሆናችን ፕሬዚዳንቱ ክብር ይሰማቸዋል፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ጥያቄ የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ካለው ሰላማዊ አኅጉር የመፍጠር የውጭ ፖሊሲ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ ይኼ የሰላም ንግግር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንደሚያመጣ ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሃማት በበኩላቸው ማክሰኞ ማምሻውን ባወጡት መግለጫ የሰላም ንግግሩ መጀመሩን በማረጋገጥ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ባለቤትነትና በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚደረገውን የሰላም ንግግር መደገፋችንን እንቀጥላለን፡፡ ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ንግግሩ ያሳዩት ቁርጠኝነት የሚበረታታ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማግኘት መወሰናቸው መደገፍ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ከፌዴራል መንግሥቱና ከሕወሓት ለሰላም ንግግሩ የተመረጡ ተወካዮች ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ቡድን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ጨምሮ ወደ ስድስት የሚጠጉ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ ከሕወሓት በኩልም ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ (ጄኔራል) እና አቶ ጌታቸው ረዳ ተወክለዋል፡፡ የሰላም ንግግሩ የሚመራው በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የአሁኑ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ፣ በድጋፍ ሰጪነትና አወያይነት ደግሞ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ፑምዚሌ ሞላምቦ ናቸው፡፡

የተመድ፣ ኢጋድና የአሜሪካ ተወካዮች በተመልካችነት የተሳተፉ ሲሆን የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ ሌሎች ተመልካቾች መኖራቸውን የሙሳ ፋቂ መግለጫ አልጠቀሰም፡፡

የሰላም ንግግሩ ከሁለት ሳምንታት በፊት ይደረጋል ተብሎ በአፍሪካ ኅብረት ቀን ተቆርጦላት የነበረ ሲሆን፣ በዋናነት በሕወሓት ተወካዮች የሎጂስቲክስ ምክንያት መተላለፉ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ግን የሕወሓት ተወካዮች በአሜሪካ የሎጂስቲክስ ዕርዳታ ደቡብ አፍሪካ መድረስ መቻላቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካና የደቡብ አፍሪካ መንግሥታት ለሕወሓት ተወካዮች ደኅንነት ዋስትና መስጠታቸውንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ከፌዴራል መንግሥት ሕወሓት ትጥቅ መፍታት እንዳለበት፣ እንዲሁም ሕወሓት በበኩሉ ሁሉም ነገር ከጦርነት በፊት (ማለትም ጥቅምት 2013 ዓ.ም.) ወደነበረበት እንዲመለስ መጠየቃቸውንና በተለይ ደግሞ የወልቃይት ጉዳይና የትግራይ ዕጣ ፋንታ የሰላም ንግግሩን ለሳምንት እንዲራዘም ያደረጉ ብርቱ ጉዳዮች ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡

ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ያለው የጦርነቱ ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ፌዴራል መንግሥቱ እያደላ መምጣቱና ሽሬ በጥምር ጦሩ እጅ በገባች በሳምንቱ መቀሌም በከበባ ውስጥ መግባቷ ተነግሯል፡፡ እስከ ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት በነበረው መረጃ በመቀሌ ከተማ ዝርፊያ መኖሩም እየተነገረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በጥምር ጦሩና የሕወሓት ጦር መካከል ከተማዋን በተለይም የአሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያን ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያ መደረጉን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

ምንም እንኳን ‹‹ጦርነቱ እያለቀና የሕወሓት ህልውና እያበቃለት ነው›› የሚሉ ተንታኞች እያመዘኑ ቢመጡም፣ በሌላ በኩል ግን የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ በረሃ ሸሽተው ሌላ ዙር የሽምቅ ውጊያ ሊቀጥል ይችላል የሚሉም ምልከታዎች ይሰጣሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...