Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሸገር የተማሪዎች ሰርቪስ አገልግሎት ላይ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል መባሉ ወላጆችን አስቆጣ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ትራንስፖርት ቢሮ በበኩሉ ወላጆች ሳይመክሩበት ይፋ የሚደረግ ውሳኔ አይኖርም ብሏል

የሸገር የተማሪዎች ሰርቪስ አውቶቡስ አገልግሎት ላይ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል መባሉ ወላጆችን አስቆጣ፡፡

የሸገር የብዙኃን ትራንስፖርት የተማሪ ሰርቪስ ተጠቃሚ ወላጆች ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚደረግ፣ ከኅዳር 1 እስከ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በተመዘገቡበት ዴፖ ቀርበው ውል እንዲያድሱ የሚገልጽ  የታሪፍ ዝርዝር እንደተላከላቸው ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም በቃሊቲና ሰሚት ዴፖ ለተመዘገቡ ደንበኞች የተላከው ማስታወሻ እንደሚያሳየው፣ ከዚህ ቀደም እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ለሚደርስ ርቀት በወር 250 ብር የነበረው ታሪፍ 730 ብር እንደሚሆን የሚያሳይ ሲሆን፣ 12 ኪሎ ሜትር ለሚደርስ ጉዞ 350 ብር የነበረው ክፍያ ደግሞ 1,240 ብር ይሆናል የሚል ነው፡፡

ከዚህ ቀደም እስከ 15 ኪሎ ሜትር ለሚሸፍን ርቀት ይጠየቅ የነበረው 400 ብር ወደ 1,550፣ እስከ 21 ኪሎ ሜትር 450 ብር የነበረው ታሪፍ 1,870 ብር እንደሚሆን ለወላጆች የተላከው ማስታወሻ ያሳያል፡፡

እስከ 24 እና 27 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎቶች በቅደም ተከተል 600 እና 650 ብር ክፍያ ይከፍሉ የነበረ ቢሆንም፣ ከታኅሳስ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ 2,800 እና 3,110 ብር ይስተካከላል የሚል ዋጋ ዝርዝር እንደተላከላቸው ወላጆች ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ለተማሪዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ የምግብና የልብስ ዕገዛ በማድረጉ ደስተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት ወላጆች፣ ነገር ግን አነስተኛ አቅም ላላቸው በሚዛናዊነት ይቀርብ የነበረውን የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት ታሪፍ ባልተጠበቀ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ ለማድረግ መታቀዱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

መሀል ከተማ ላይ ያለው የቤት ዋጋ በማንሰራራቱ በከተማዋ ዳርቻ እንደሚኖሩና የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ ሁለት ዓመት እንዳለፋቸው የተናገሩት አቶ ሲሳይ ኃይሉ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቱ ይፋ የተደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ሳይታሰብ የተደረገና ዳግም ሊጤን የሚገባው ነው ብለዋል፡፡

‹‹ጭማሪ አይደረግ ሳይሆን ተጠቃሚዎችን በማወያየት ሊደረግ የሚገባውና  የኑሮ ውድነትን ግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤›› የሚሉት አቶ ሲሳይ፣ የሚመለከታቸው ባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጡት የሚገባው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ፍሰሐ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ ታሪፍ የመወሰን፣ የማውጣት፣ መስመር አውጥቶ አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት የሸገር ትራንስፖርት ሳይሆን ተጠሪ የሆነለት የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ነው ብለዋል፡፡

ለወላጆች የተላከው ወረቀት የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ላይ የተዳረሰ ነው የሚሉት አቶ ሳሙኤል፣ ነገር ግን የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ወላጆች ተጠርተው ውይይት ተደርጎበት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶና ለትራንስፖርት ቢሮ ተልኮ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር እፀገነት አበበ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት ከተጀመረበት ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የታሪፍ ማሻሻያ ሳይደረግበት ቆይቷል፡፡ በወቅቱ የወጣው ታሪፍ የወቅቱን የገበያ ሁኔታና የመለዋወጫ ሌሎች ጉዳዮችንም ታሳቢ ተደርጎ የወጣ መሆኑን ያስረዱት ዳይሬክተሯ፣ ባለፈው የበጀት ዓመት የከተማው ትራንስፖርት ባለሥልጣን ከመፍረሱ በፊት ከዋጋ ማስተካከያ ጋር በተገናኘ ያስጠናው ጥናት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ምክንያት በይደር የቆየው ጥናት ላይ ውይይት ሳይደረግበት በትምህርት ቤቶች መድረሱ ትክክል አለመሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ ጥናቱን በተመለከተ ቅድሚያ መደረግ የሚገባው ውይይት፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ያልተደረገና ውሳኔው ተግባራዊ መሆን አለመጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የታሪፍ ማሻሻያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ከተማሪ ወላጆች ጋር ውይይት እንዲደረግበት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለሸገር ብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት መስከረም 03 ቀን 2015 ዓ.ም. ደብዳቤ መጻፉን ያስታወቁት ወ/ሮ እፀገነት፣ ቢሮው በዚህ ወቅት ወደ ተግባር ይግባ ሳይሆን ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ይደረስበት የሚል አቋም እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ጥናቱን ያጠኑ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ከወላጆች ውይይት ተደርጎ የጋራ ሐሳብ ሳይያዝ ይፋ የሚደረግ የውሳኔ ሐሳብ እንደማይኖር፣ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል፡፡

የተማሪ ሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ 100 አውቶቡሶች በሸገር አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ሥር የሚገኙ ሲሆን፣ እነዚህም ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የሚያገለግሉ 30 አነስተኛ እንዲሁም እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ያሉ ተማሪዎችን የሚያገለግሉ 70 መካከለኛ አውቶቡሶች ናቸው፡፡ አውቶቡሶቹ በየቀኑ በአማካይ ከ4,200 እስከ 4,300 ለሚደርሱ ተማሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች