Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የሰላም ዕድሉ እንዳያመልጥ ስክነት ያስፈልጋል!

  በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር በደቡብ አፍሪካ ተጀምሯል፡፡ ከማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ መጪው እሑድ ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ይከናወናል የተባለው የመጀመሪያው የሰላም ንግግር፣ ወደ ድርድር የመሸጋገር ዕድል ካለው የሚናፈቀው ሰላም ተስፋ ይኖረዋል፡፡ ተስፋ እንዲኖር ግን ከዚህ ቀደም ያስቸገሩ ችግሮች መልክ መያዝ አለባቸው፡፡ እነዚህ ችግሮች የሚመነጩት ጥላቻ ከፈጠረው አለመተማመን፣ ከአገርና ከሕዝብ በፊት ሥልጣንን ከማስቀደም፣ ከራስ ክብርና ዝና በላይ ለሌላው ካለመጨነቅና ከዕብሪት ነው፡፡ የአሁኑ የደቡብ አፍሪካ የሰላም ንግግር የሚደረገው የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል በርካታ ከተሞችን ተቆጣጥሮ የበላይነት በያዘበት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን፣ ዘለቄታዊ ሰላም የሚሰፍነው ግን ሁለቱም ወገኖች ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅም ስምምነት ላይ ለመድረስ መግባባት ሲፈጥሩ ነው፡፡ የአሁኑ የሰላም ንግግር ወደ ድርድር ማምራት ካልቻለ፣ መጪው ጊዜ ከሚታሰበው በላይ ከባድ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ትኩረት ሰቅዞ የያዘው የሰላም ንግግር በሰከነ መንገድ ተካሂዶ አስተማማኝ ሰላም ይስፈን፡፡

  ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሲካሄድ የቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት በአገር ላይ ያስከተለው መዘዝ ቀላል አይደለም፡፡ ከተዋጊዎቹ በተጨማሪ በንፁኃን ላይ የደረሰው ዕልቂት፣ መፈናቀል፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳትና የንብረት ውድመት እንደ ዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በሕጋዊ፣ በፖለቲካዊና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ማግኘት የነበረበት አለመግባባት ያደረሰው ጥፋት አሁንም ትምህርት የተገኘበት አይመስልም፡፡ አስተዋዩና ትሁቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየደረሰበት ያለው ሰቆቃ በፍጥነት እንዲገታ በተለያዩ መንገዶች ፍላጎቱን ሲገልጽ፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ የተጠመዱ ደግሞ መከራው መቋጫ እንዳያገኝ ጥፋት ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የአሁኑ የሰላም ንግግር በደቡብ አፍሪካ እንደሚካሄድ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ፣ በግራና በቀኝ የተሠለፉ አደፍራሾች የሚያስተላልፏቸው አሉታዊ ዘገባዎችም ሆኑ አስተያየቶች ኪሳራ እያደረሱ ነው፡፡ ራሳቸውን ከአገርና ከሕዝብ በላይ በማድረግ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም እንዳይሰፍን በሐሰተኛ ወሬዎች ግራ ያጋባሉ፡፡ የሰላም መታጣት ግን እየጎዳ ያለው በግጭትና በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ያለውን ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የተጋለጠችውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

  ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የሚያፋጅና አገራቸውን የሚያስወድም አስከፊ ጦርነት ውስጥ የከተተው ምክንያት፣ በምንም መመዘኛ ከጠረጴዛ ዙሪያ ክርክርና ድርድር ማለፍ እንደማይችል ለማንም ቢሆን ግልጽ ነው፡፡ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በተደጋጋሚ ወደ ዕልቂትና ወደ ውድመት የሚያመራ ጎዳና ውስጥ እንዳይገባ ብዙዎች ተማፅነዋል፡፡ የአንድ አገር ልጆች ችግራቸውን በሰላማዊ መንገድ መፍታት አቅቷቸው ታሪክ ይቅር የማይለው ስህተት እንዳይፈጸም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ ከአገር ህልውና በፊት የሚቀድም አንዳችም ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ፍላጎት መኖር እንደሌለበት ተወትውቷል፡፡ ከዚህም ታልፎ ኢትዮጵያ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የሚዳርጋት በመሆኑ ጦርነት ፈፅሞ እንዳይታሰብ በዕንባ ጭምር ልመና ቀርቧል፡፡ ይህ ሁሉ ተማፅኖ ወደ ጎን ተገፍቶ በተከፈተው ጦርነት አንድ ትውልድ ከመማገዱም በላይ፣ የደረሰው ጥፋት እንዲሁ እንደ ቀልድ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ አሁንም ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ አስተናግዶ ሰላም ማስፈን ካልተቻለ፣ ኢትዮጵያ የታሪካዊ ጠላቶቿ መቀለጃና መፈንጫ መሆኗ አይቀሬ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አስረዝመው እያስገቡ ያሉ የውጭ ኃይሎች ፍላጎትም የታወቀ ነው፡፡

  በጥላቻና በመገፋፋት ላይ የተመሠረተው ብልሹ የፖለቲካ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ተወግዶ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር የሚቻለው ለሰላም በጋራ ሲሠራ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ስብስቦች፣ ከተራ ብሽሽቅና ከአሉባልታ ወለድ ንትርኮች በመላቀቅ ለአገራቸው ሰላም ጠንክረው ይሥሩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በሴራ ፖለቲካ ምክንያት እየተጠቁ ያሉት እውነት፣ ሰብዓዊ ርኅራኄ፣ እርስ በርስ መተማመን፣ መከባበርና መደጋገፍ ናቸው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ማኅበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ ጭካኔና ግፍ እየተበራከቱ ናቸው፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት በጅምላ ሲጨፈጨፉ ከስማቸው ይልቅ ብዛታቸው ላይ እየተተኮረ፣ ሰብዓዊነት እየነጠፈና ሞት እየተለመደ አሳዛኝ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ በየቦታው በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶችና በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት፣ በገዛ አገር እንደ ልብ ተዘዋውሮ መሥራትም ሆነ መኖር ከብዷል፡፡ ሰላም ጠፍቶ መንቀሳቀስ ሲያስቸግርና ከዛሬ ይልቅ ነገ የበለጠ አስፈሪ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች ነው በማለት የጋራ መፍትሔ መፈለግ የፖለቲከኞችና የልሂቃን ተግባር ቢሆንም የተቻለ አይመስልም፡፡

  በ21ኛው ክፍለ ዘመን በዘመነ መሣፍንት አስተሳሰብ ተቸክሎ ጠመንጃ መወልወልም ሆነ ውረድ እንውረድ ተባብሎ ጦር መስበቅ፣ በየትኛውም መመዘኛ በጣም የሚያስንቅ አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የከንቱዎች ሥራ አንድ ትውልድ በልቶ ጨርሶ ወደ ቀጣዩ ትውልድም ስለሚሸጋገር፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት መወገድ ይኖርበታል፡፡ ጀብደኝነት የጥቂቶችን ፍላጎት ለማስፈጸም የሚያገለግል የኋላቀሮች የከሰረ ፖለቲካ መገለጫ ስለሆነ፣ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ሊፀየፈው ይገባል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከኢትዮጵያ ተርፎ ለአፍሪካ ቀንድ ጭምር ሥጋት መሆኑ በስፋት ሲነገር፣ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ በወጉ መጤን አለበት፡፡ የቀይ ባህር አካባቢ ጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክር የፈርጣማ አገሮች የጦር ሠፈሮች እንዲበራከቱ ማድረጉ እየታወቀ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሰላም እንዲጠፋ የሚያደርግ ጦርነት ውስጥ መክረም በጣም አደገኛ ነው፡፡ የውጭ ኃይሎች የተፅዕኖ አድማሳቸውን እያሰፉ በአገር ጉዳይ ውስጥ ገብተው እየፈተፈቱ መሆናቸው ለማንም ግልጽ ሆኖ ሳለ፣ በፍጥነት ሰላም አስፍኖ የተረጋጋ ከባቢ መፍጠር አለመቻል ዋጋ ያስከፍላል፡፡

  በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው የሰላም ንግግር በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ላይ ተመሥርቶ ለድርድሩ ጥርጊያ ቢያመቻች ይመረጣል፡፡ ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት የቀሩት አውዳሚ ጦርነት በንፁኃን ሕይወት፣ አካል፣ አዕምሮ፣ ንብረትና በአገር ላይ ያደረሰው ውድመት በፍጥነት መቆም አለበት፡፡ ጦርነት ለምንም ነገር መፍትሔ አይሆንም፡፡ የሰላም ንግግሩ በሚፈለገው መንገድ ተጉዞ ድርድሩ በቀና መንገድ እንዲጀመር፣ በሁሉም ጎራ ያሉ ፖለቲከኞችም ሆኑ ልሂቃን ከአፍራሽ ድርጊቶች መታቀብ አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ሰላም ማስፈን ካልተቻለ ጦርነቱ የተለያዩ የውጭ ተዋንያንን ሊጋብዝ እንደሚችል ማሰብ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ አስከፊ ጦርነት ሳቢያ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ሰላምና መረጋጋት በመጥፋቱ ምክንያት የአገር ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጦርነቱም ሆነ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ኢኮኖሚውን እያደቀቁት ነው፡፡ የኢኮኖሚው መድቀቅ የኑሮ ውድነቱን በማባባስ የኢትዮጵያውያንን ሕይወት ገሃነም እያደረገው ነው፡፡ አሁን የተገኘውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ሰላም ማስፈን ይገባል፡፡ ይህ ዕድል እንዳያመልጥ ደግሞ ስክነት አስፈላጊ ነው!    

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አነስተኛ ካፒታል ያላቸው ባንኮች በመዋሃድ አቅም እንዲፈጥሩ ጉምቱው የፋይናንስ ባለሙያ መከሩ

  የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንዳይገቡ የሚከለክለውን ሕግ የማሻሻል...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...

  ነባር ‹‹ላዳ›› ታክሲዎችን መሸጥና መለወጥን ጨምሮ ለሌላ ማስተላለፍ ተከለከለ

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለምዶ ‹‹ላዳ ታክሲ›› ተብለው የሚታወቁትን...

  በሰሜኑ ጦርነት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ አይነሱም ተባለ

  ልማት ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ታማሚ ብድር እንዲነሳለት ጠይቋል የኢትዮጵያ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...