የሮም ፖፕ ፍራንሲስ፣ ባለፈው እሑድ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ካሰሙት ንግግር የተወሰደ። በዕለቱ በነበረው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ላይ ኢትዮጵያን ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ከምዕመናኑ ጋር በኅብረት ባቀረቡት ጸሎት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲወርድ ጠይቀዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በመካሄድ ላይ ካለው የጦርነት አደጋ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ሕፃናትን፣ ሴቶችንና አቅመ ደካሞችን በሙሉ ያስታወሱት ፖፑ በሕዝቡ ላይ የሚደርስ ስቃይ እንዲያበቃ ተማፅነዋል። ግጭት ውስጥ የገቡት ወገኖች በውይይት ሰላምን ለማምጣትና የጋራ ጥቅምን ለማስከበር የሚያደርጉት ጥረት ወደ ተጨባጭ የእርቅ ጎዳና ሊመራቸው እንደሚችል ያላቸውን እምነትም ገልጸዋል። ፖፑ በቲዊተር ገጻቸው ላይ ባስቀመጡት መልዕክትም፣ ‹‹በጦርነት ስቃይ ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚደረግ የጸሎት፣ የአጋርነትና አስፈላጊው የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንደማይቋረጥ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ብለዋል።