Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊወደ ጥቅምት 15 የተቀየረው የመከላከያ ሠራዊት ቀን

ወደ ጥቅምት 15 የተቀየረው የመከላከያ ሠራዊት ቀን

ቀን:

ከአሥር ዓመት ወዲህ በየዓመቱ የካቲት 7 ቀን ሲከበር የቆየው የመከላከያ ሠራዊት ቀን ከዘንድሮ አንስቶ ወደ ጥቅምት 15 ቀን መቀየሩን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስቴሩ ለመከላከያ ሠራዊት የወሰነውን አዲስ ቀን በዋዜማው ሰኞ ጥቅምት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. እና በማግሥቱ ባካሄዳቸው የተለያዩ መርሐ ግብሮች አክብሯል፡፡

የመከላከያ ሚኒስቴር ለሠራዊቱ ቀን አዲስ ቀን መቁረጡን ያስታወቀው ዓምና በተመረቀውና ጦር ኃይሎች አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ አካባቢ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ውስጥ ባዘጋጀው የፓነል ውይይት ላይ ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ በነበረው መርሐ ግብር ላይ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ (1881-1906) የሚጀምረውን የመከላከያ ሠራዊት ታሪክ እንዲሁም መከላከያን በሚኒስትርነትና ጦሩን በኤታማዦር ሹምነት የመሩ አመራሮችን የሚያሳይ ዓውደ ርዕይ ተካሂዷል፡፡

በዕለቱ የነበረው ሌላኛው ሁነት የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ታሪክ የቀረበበት የፓነል ውይይት ነው፡፡ በውይይቱ ላይ የቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አበባው አያሌው ከጥንታዊት ኢትዮጵያ ስለሚጀምረው የነገሥታት ሠራዊት በመነሳት ስለመከላከያ ሠራዊት ታሪክ ገለጻ አድርገዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመከላከያ ሠራዊት የምርምር ማዕከል ኃላፊ ተወካይ ኮሎኔል መስፍን ለገሰ ቀጥለው ባቀረቡት ጽሑፍ ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ጥቅምት 15 ሆኖ እንዲከበር ስለመወሰኑና ምክንያቱንም ለታዳሚው አስረድተዋል፡፡

አንድ አገር የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ለመወሰን የተለያዩ መነሻዎችን እንደሚጠቀም በመግለጽ ጽሑፋቸውን ማቅረብ የጀመሩት ኮሎኔል መስፍን፣ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የተመሠረተበትን ቀን፣ የሠራዊቱ አመራር ከቅኝ ገዥ የተላቀቀበት ቀን አልያም የአገሪቱን ነፃነት ለማረጋገጥ የተደረገ ውጊያ ወይም ጦርነት ለቀን መወሰኛ መነሻነት እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

ሠራዊታቸው የተመሠረተበትን ቀን በማሰብ ከሚያከብሩ አገሮች መካከል ቻይና፣ ሩሲያ፣ ፊሊፒንስ፣ ቬትናም፣ ሰሜን ኮርያ፣ አርመን፣ ጃፓን፣ ኢራንና ሜክሲኮ ተጠቅሰዋል፡፡ የሠራዊታቸው አመራር ከቅኝ ግዛት የተላቀቀበትን ቀን መሠረት አድርገው ከሚያከብሩት ውስጥ ደግሞ ህንድና ደቡብ አፍሪካ በምሳሌነት ተነስተዋል፡፡ ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ጣሊያንና ሩማንያ በታሪካቸው ውስጥ የተካሄዱ ጦርነቶችን መሠረት አድርገው የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ከወሰኑ አገሮች መካከል እንደሆኑ ኮሎኔል መስፍን ገለጻ አድርገዋል፡፡

በፓነል ውይይቱ ላይ የቀረበው ጽሑፍ እንደሚያስረዳው፣ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት (1923-1967) በፊት የሠራዊት ቀን ባይኖርም የዓድዋ ድል ወይም የነገሥታት ልደትና የንግሥ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ሠራዊቱ የሠልፍ ትርዒት ያደርግ ነበር፡፡

በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን፣ ከ1948 ዓ.ም. ግንቦት ወር ጀምሮ በምድር ኃይል የተለያዩ ክፍሎች መካከል የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች ይካሄዱ ነበር፡፡ ግንቦት 20 ቀን 1950 ዓ.ም. በተካሄደው ውድድር ላይ የተገኙት አፄ ኃይለ ሥላሴ ውድድሩ በሠራዊቱ መካከል የፈጠረውን መነቃቃት በማየት ዕለቱ የሠራዊቱ ቀን ሆኖ በየሦስት ዓመቱ እንዲከበር ወስነው ሲከበር መቆየቱን ኮሎኔል መስፍን ገልጸዋል፡፡

የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት 1967 ዓ.ም. አነስቶ ደግሞ የሠራዊት ቀን ‹‹እየተቆራረጠ›› ሲከበር መቆየቱን ያስታወሱት ጽሑፍ አቅራቢው፣ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት በአዋጅ የተቋቋመበት የካቲት 7 ቀን 1987 ዓ.ም. ምክንያት በማድረግ ቀኑ ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሲከበር መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት በአዋጅ የተቋቋመበትን መነሻ አድርጎ የሠራዊቱ ቀን የካቲት 7 ቀን ማክበር የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ከዚያ ቀደም የነበረውን ታሪክ ‹‹ዋጋ የሚያሳጣ›› መሆኑን የገለጹት ኮሎኔል መስፍን፣ በዚህም የተነሳ የመከላከያ ሚኒስቴር ለሠራዊቱ በዓል ሌላ ቀን ለመምረጥ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ጽሑፍ አቅራቢው ገለጻ ሚኒስቴሩ ለመከላከያ ሠራዊት አዲስ ቀን ለመምረጥ የተለያዩ ታሪካዊ መነሻዎችን ገምግሟል፡፡

የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ (1847-1860) ዘመናዊ ሠራዊት የማቋቋሙ ሙከራ፣ የዓድዋ ጦርነት ድል፣ የክብር ዘበኛ የተቋቋመበት 1910 ዓ.ም.፣ ኢትዮጵያ ከጣልያን ዳግም ወረራ ነፃ ከሆነች በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ አዲስ አበባ የገቡበት ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም.፣ ሠራዊቱ የራሱን የደንብ ልብስና የሥልጣን ተዋረድ እንዲይዝ የተደረገበት ታኅሣሥ 15 ቀን 1944 ዓ.ም.፣ የሶማሊያ ወረራ የተቀለበሰበት ጥር 26 ቀን 1970 ዓ.ም.፣ የመከላከያ ሠራዊት በአዋጅ የተቋቋመበት የካቲት 7 ቀን 1988 ዓ.ም.  ከተገመገሙ ሁነቶች መካከል መሆናቸው ተነስቷል፡፡

ከእነዚህ ቀናት ውስጥ የተመረጠው ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም. ሲሆን፣ ይህም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመናዊ የመንግሥት አመራር ሥነ ዘዴን ለመከተል በመፈለጋቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሚኒስትሮች የሾሙበት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ሚኒስትር ከተሾሙላቸው ተቋማት ውስጥ አንዱ በአዋጅ የተቋቋመውና በፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ የሚመራው የጦር ሚኒስቴር ነው፡፡ አዋጁ ሚኒስቴሩ የንጉሠ ነገሥቱ ሠራዊት አለቃ መሆኑን ደንግጎ፣ ሠራዊቱ ሁሉ የጦር ትምህርት እንዲማር የሚጠብቅ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

ይህ ቀንም ከዘንድሮ አንስቶ በየዓመቱ የመከላከያ ሠራዊት ቀን ሆኖ እንዲከበር የተመረጠ አዲስ ቀን መሆኑ ተገልጿል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደ አንድ የአገሪቱ ተቋም ሆኖ በሚኒስቴር የተቋቋመበት ጥቅምት 15 ቀን 1900 ዓ.ም. የሠራዊት ቀን ሆኖ ሊመረጥ ችሏል፤›› ሲሉ አዲሱ ቀን የተመረጠበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊት ቀንን ለማክበር እንደ መነሻ የተወሰዱት ቀናት አብዛኛዎቹ ሁነቶች የመከላከያ ሠራዊት ቀን ተብሎ ለመሰየም የሚያስችል በቂ ምክንያት እንደሌላቸው ለታዳሚው ያስረዱት ኮሎኔል መስፍን፣ የድል የተገኘባቸው ቀናት ደግሞ ራሳቸውን ችለው እየተከበሩ ያሉ መሆናቸው አስታውሰዋል፡፡

በዚህም የመከላከያ ሠራዊት ቀን ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ ጥቅምት 15 ቀን እንደሚከበር የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በአዲሱ ቀን የሚከበረው የመጀመርያው የመከላከያ ሠራዊት ቀንም ሰኞ ጥቅምት 14 እና ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን ተከብሯል፡፡ ትናንት በተካሄደው መርሐ ግብር ‹‹የእሳት ቀለበት›› የተሰኘና ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜን ዕዝ በመጠቃቱ የተካሄደውን ‹‹የሕግ ማስከበር ዘመቻ›› አስመልክቶ የተዘጋጀ መጽሐፍ ተመርቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...