Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የጥቃቅንና አነስተኛ አንደኛው ትሩፋት

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘው አዳማ የስብሰባና የመዝናኛ ከተማነቷን ተከትሎ ‹‹የኮንፍራንስ ቱሪዝም ከተማ›› የሚል ስያሜ አግኝታለች፡፡ በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳዲስ የሆቴል ግንባታዎችም ይታዩበታል፡፡ በመንግሥት ተቋም ውስጥ በግብርና ባለሙያነት ሲያገለግል የነበረው አቶ ዳግም ጥበቡ፣ በ2002 ዓ.ም. በ30 ሺሕ ብር መነሻ ካፒታል በሻይ ክበብ ሥራ ተሰማርቶ፣ በአነስተኛና በጥቃቅንም በመደራጀት ምግብና መጠጥ ለመንግሥት ተቋማት በማቅረብ ሥራውን ጀመረ፡፡ በሒደት ሆቴሎችን በመከራየት በግል ሥራውን እየስፋፋ የመጣው ወጣቱ፣ በ2008 ዓ.ም. ባንክ ባመቻቸለት ብድር አማካይነት ዘመናዊ ሆቴል ለመገንባት ወጠነ፡፡ መንግሥት በተለይ ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ባመቻቸው የጥቃቅንና የአነስተኛ ተቋማት ተደራጅቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስኬትን መጎናፀፍ ከቻሉ ወጣቶች መካከል የሚመደበው አቶ ዳግም፣ 750 ሚሊዮን ብር የፈጀ ሆቴል ገንብቶ ማጠናቀቅ ችሏል፡፡ ስሙንም ‹‹ናፍሌት ሆቴል›› ብሎታል፡፡ የስኬት ጉዞውን በተመለከተ ከዳዊት ቶሎሳ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከመንግሥት የግብርና ባለሙያነት ወደ ግል ሥራ ያመራህበትን አጋጣሚ አስታውሰን?

አቶ ዳግም፡- ከትውልድ አገሬ እንደወጣሁ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመማር በአዳማ ከተማ ዘመድ ቤት ነበር የቆየሁት፡፡ ግን የደሃ ቤተሰብ ልጅ ነበርኩና ወደ ዩኒቨርሲቲ መሰናዶ የሚያስገባ ጥሩ ውጤት ቢኖረኝም ቶሎ ደመወዝተኛ መሆን ነበረብኝ፡፡ ስለዚህ አላጌ የግብርና ኮሌጅ ገባሁ፡፡ እዚያም ሦስት ዓመት ተምሬ ተመርቄ ከወጣሁ በኋላ እዚያው አካባቢ በነበረው የመንግሥት የግብርና ተቋም የ530 ብር ደመወዝተኛ ሆኜ በአንድ የገጠር ቀበሌ የልማት ጣቢያ ሠራተኛ ሆኜ ተመደብኩኝ፡፡ በተማርኩበት ሙያ አርሶ አደሩን የዘመናዊ ግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ በቀን ከ20 እስከ 30 ኪሎ ሜትር መጓዝ ግድ ይለኝ ነበር፡፡ ሆኖም የማገኘው ወርኃዊ ደመወዝ ራሴንም ሆነ ቤተሰቤን ለመርዳት የሚያስችል አልነበረም፡፡ ከሥራው ጎን ለጎን የተሻለ ደመወዝ ፍለጋ ያላንኳኳሁት የመንግሥት ተቋም፣ ያልረገጥኩት የግል መሥሪያ ቤት አልነበረም፡፡ በመጨረሻ የግሌን ቢዝነስ መጀመር የመጨረሻ አማራጭ አደረግሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የግል ሥራ እንቅስቃሴው እንዴት ተጀመረ?

አቶ ዳግም፡- ቤተሰቦቼ በሚኖሩበት አዳማ ከተማ የሚገኝ አንድ የመንግሥት የዱቄት ፋብሪካ የሠራተኛ ማኅበር የሻይ ክበቡን ማከራየት እንደሚፈልግ ሰማሁ፡፡ ከዚያም ቀጥታ ሄጄ የሠራተኛ ማኅበሩን ሊቀመንበር ቢሮው አገኘሁትና ተከራይቼ የመሥራት ፍላጎት እንዳለኝ አስረዳሁት፡፡ እሱም የሻይ ክበቡን የሚከራየው ሰው ለድርጅቱ ሠራተኞች በቅናሽ፣ ለአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ራሱ ባወጣው ዋጋ መሸጥ እንደሚችል ነግሮኝ ከቢሮው ወጣሁ፡፡ ከዚያም የሻይ ክበቡ በወር 500 ብር እንደሚከራይና የስድስት ወር ኪራይ በቅድሚያ መክፈል እንደሚጠበቅብኝ ተነገረኝ፡፡ በወር ከማገኛት 530 ብር የመንግሥት ደመወዝ 500 ብሩን በየወሩ ለኪራይ መክፈል እንደምችል ተገንዝቤ፣ የፍጆታ ዕቃ ግዥ ወጪ ስለሌለብኝ ክበቡን ተከራየሁ፡፡ ሥራውን ለማስጀመር መነሻ ካፒታል እንዲሆነኝ በክበቡ አካባቢ በነበረው የሕግ ማሠልጠኛ ተቋም አቅንቼ ሠራተኞቹ በየወሩ እየከፈሉ የሚመገቡበትን መንገድ ለመፍጠር ዕቅድ አወጣሁ፡፡ በዚህም መሠረት የቢዝነስ ካርድ አሳትሜ ክበቡ እንደ አዲስ ሥራ መጀመሩን ለሠልጣኞቹ አሳወቅሁ፡፡ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ስላልነበረኝ ለሠልጣኞች የዱቤ ሽያጭ ለመስጠት በቅድመ ክፍያ ከፍለው በአገልግሎቱ ለሚጠቀሙ 300 ሰዎች የ100 ብር ካርድ አዘጋጀሁ፡፡ በመጨረሻም በ30 ሺሕ ብር ካፒታል የቢዝነስ ዓለሙን ተቀላቀልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቃቅንና በአነስተኛ ከተደራጁ ወጣቶች መካከል አንዱ ነህ፡፡  የተደራጀህበትን አጋጣሚ ብታብራራልን?

አቶ ዳግም፡- እኔ ወደ ንግድ ዓለም የገባሁበት ጊዜ መንግሥት ወጣቱን በጥቃቅንና በአነስተኛ እንዲደራጁ ከፍተኛ ቅስቀሳ የሚያደርግበት ወቅት ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ በጋራ ከሠሩ፣ በጋራ ማደግ እንደሚቻል አምን ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ መመርያ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ማንኛውም የመንግሥት ተቋም ቅድሚያ የሥራ ዕድል በጥቃቅን ለተደራጁ የሚል ነበር፡፡ መመርያውን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ሥራዬን ማስፋት ነበረብኝ፡፡ ነገር ግን ብቻዬን የትም እንደማልደርስ ስለተረዳሁ፣ እንደ እኔ በአገልግሎት ዘርፍ የተደራጁ ማኅበራትን መፈለግ ጀመርኩ፡፡ ቀጥሎም የመንግሥት የቀበሌ አዳራሾች ላይ እንዲሁም በሥልጠና ማዕከሎች ያሉትን የሻይና የቡና አቅርቦቶች መንግሥት ዕድሉን እንዲሰጠን መጠየቅ አቀድን፡፡ አምስት ማኅበራት ሆነን የጥቃቅንና የአነስተኛ ጽሕፈት ቤት ሄደን ፍላጎታችንን ስንነግራቸው ለመንግሥት ተቋማት ድጋፍ ጻፉልን፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ሻይና ቡናን ለ1,300 ሰዎች አቅርበን የ20,000 ብር ትርፍ አገኘን፡፡

ሪፖርተር፡- ከጥቃቅንና ከአነስተኛ ማኅበር ወደ ሆቴል ሥራ እንዴት ተሸጋገርክ?

አቶ ዳግም፡- በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን ባገኘነው ጠባብ ቦታ ላይ ሥራችንን ጀምረን ወደ መንግሥት ቢሮዎች እያቀናን እንዲሁም በአባ ገዳ የስብሰባ አዳራሽ ምግብና መጠጥ ማቅረብ ቀጠልን፡፡ በሒደት ግን የጥቃቅንና የአነስተኛ ማኅበሮች ቁጥር እየተበራከቱ በመምጣታቸውና የደንበኞች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ ሥራውን ለማስፋፋት በግል ሥራዬን ለማስቀጠል ወሰንኩ፡፡ በ2006 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ጌጤ ሆቴልን በወር 120 ሺሕ ብር ተከራይቼ፣ ወደ መንግሥት ቢሮዎች እያቀናሁ፣ ሆቴሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ማስተዋወቅ ጀመርኩ፡፡ በዚህም ሆቴሉ የስብሰባ አዳራሽ፣ የምግብና የመጠጥ፣ የእንግዳ ማረፊያ እንዲሁም የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት ጀመረ፡፡ ሆቴሉን ከመከራየቴ በፊት እምብዛም እንቅስቃሴ አልነበረውም፡፡ በተከራየሁ ማግሥት በሆቴሉ በቀን ከ300 እስከ 400 ሰው ተገልጋይ ነበረው፡፡ የተለያዩ የመንግሥት ስብሰባዎችንም ያስተናግድ ነበር፡፡ በሆቴሉ ላይ ሦስት ዓመት ከሠራ በኋላ የኪራይ ዋጋ በመጨመሩ በ250 ሺሕ ብር ኮምፈርት ሆቴል ተከራይቼ ቀጠልኩ፡፡ ከሆቴል ሥራው ጎን ለጎን የከብት ማደለቢያ ሥፍራን ተከራይቼ ከብት እያደለብኩ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ ተሰማራሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከፍተኛ ወጪ የተደረገበት ዘመናዊ ሆቴል በአዳማ ከተማ ገንብተሃል፡፡ ግንባታው እንዴት ተጠነሰሰ?

አቶ ዳግም፡- በሥራው ሒደት ውስጥ እያለሁ በኪራይ መቀጠል እንደሌለብኝ ተረዳሁ፡፡ የራሴ ነው የምለውን ሆቴል መገንባት አለብኝ ብዬ መንቀሳቀስ ጀመርኩ፡፡ በመጀመሪያ ምዕራፍ በሦስት ሚሊዮን ብር 550 ካሬ ሜትር ቦታን ገዝቼ፣ ሆቴል ለመገንባት እንቅስቃሴ ጀመርኩ፡፡ ግንባታውን ለማስጀመር የተለያዩ የግልና የመንግሥት ባንኮች ደጅ አምርቻለሁ፡፡ ባንኮቹ ግን ብሩን ሊፈቅዱልኝ አልፈለጉም ነበር፡፡ ሐሳቤንና ያነገብኩትን ህልም በመጨረሻ የተረዳኝ ዘመን ባንክ ነበር፡፡ ዘመን ባንክ ግንባታዬን እንድጀምር 82 ሚሊዮን ብር ብድር ፈቀደልኝ፡፡ ብድሩ ከተመቻቸልኝ በኋላ፣ ተጨማሪ 1,500 ካሬ ሜትር መሬት ገዝቼ የሆቴል ግንባታውን አስጀመርኩ፡፡ ለግንባታው ማስፋፊያ ተጨማሪ ገንዘብ በማስፈለጉ ባንኩ ተጨማሪ ብድር 185 ሚሊዮን ብር ፈቅዶልኝ ዘመናዊ ሆቴል ግንባታው በይፋ ተጀመረ፡፡ ሆቴሉ አብዛኛውን የአገር በቀል ግብዓቶችን የተጠቀመ ሲሆን፣ ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ‹‹ናፍሌት ሆቴል›› የሚል ስያሜን ይዟል፡፡ ሰባት ወለሎች (ፎቆች) ያሉት ሲሆን፣ ሕንፃው በ1,600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አርፏል፡፡

ሪፖርተር፡- በጥቃቅንና በአነስተኛ ተደራጅተው ከተሳካላቸው ባሻገር፣ ሳይሳካላቸው የተበተኑ ማኅበራት ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም፡፡ በአንፃሩ ለአንተ ስኬት ምስጢሩ ምንድነው?

አቶ ዳግም ወደ ቢዝነስ ሥራ መቀላቀል ለሚፈልጉ ሰዎች ሦስት የሰዎችን ባህሪያትን ማወቅ አለባቸው ብዬ ስለማምን ባካፍል ደስ ይለኛል፡፡ ሰዎችን በሦስት ከፍዬ ነው የማየው፡፡ እነዚህም ውሳኔ የሚፈሩና የውሳኔ ሰዎች፣ ወይም የዓላማ ሰዎች ናቸው፡፡ ወሳኞች የምላቸው ባላቸው ነገር የሚረኩ፣ ለአዲስ ነገር ብዙም የማይጨነቁ፣ ያለኝ ገቢ በቂ ነው ብለው ስለሚያምኑ የቢዝነሱን ዓለም ቢቀላቀሉ ውጤታማ ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው፡፡ የውሳኔ ፈሪዎች የምላቸው ደግሞ ብዙ ሐሳብ እያላቸው በፍርኃት ምክንያት ሐሳባቸውን ወደ ተግባር የማይቀይሩና የማይወስኑ ናቸው፡፡ መሥሪያ ቤት እንኳን መቀየር እየፈለጉ የማይቀይሩ፣ በትምህርት ራሳቸውን ማሻሻል እየፈለጉ ግን የማያሻሽሉና ቢዝነስ መሥራት እየፈለጉ የማይወስኑ ናቸው፡፡ የውሳኔ ሰዎች ወይም የዓላማ ሰዎች የምላቸው መነሻቸውንና መድረሻቸውን የሚያውቁ፣ መድረስ የሚፈልጉት ቦታ ላይ እስከሚደርሱ የሚገጥማቸውን መሰናክል የሚያልፉ፣ ለመድረሻቸው ጠንክረው የሚሠሩ መሆናቸውን ለራሳቸው የሚነግሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ቢዝነስ ሲገባ የውሳኔ ሰው መሆን ያሻል፡፡ በጊዜው በጥቃቅንና በአነስተኛ የተደራጁ በርካታ ማኅበራት አይሳካም በማለትና እርስ በርስ ያላቸውን መተማመን ማጠንከር ስላልቻሉ ከስኬታቸው የቀሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ ሁሌም የውሳኔ ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...