- እኔ ምልህ ?
- እ… አንቺ ምትይኝ?
- የሚባለው ነገር እውነት ነው?
- ምን ተባለ?
- ሰኞ ይጀመራል የተባለው ድርድር ለአንድ ቀን የዘገየው ተደራዳሪዎቹ በቀጥታ ለሕክምና በመሄዳቸው ነው እየተባለ ነው እኮ?
- የእኛ ተደራዳሪዎች?
- እሱን እንድትነግረኝ እኮ ነው የጠየኩህ?
- አልሰማሁም… ግን በጭራሽ የእኛ ተደራዳሪዎች ሊሆኑ አይችሉም።
- እሱማ የእኔም ጥርጣሬ ሌላ ነው።
- አንቺ ማንን ጠረጠርሽ?
- የታችኞቹን።
- አደራዳሪዎቹ አሉ የተባለውስ እውነት ነው?
- ምን አሉ ተባለ?
- ተቆጧቸው ይባላል።
- ምን ብለው?
- ለድርድር ነው ለሕክምና የመጣችሁት ብለው፡፡
- ይገርማል…!
- ምኑ?
- እኛ ሳንሰማ መረጃው እናንተ ዘንድ ነው ያለው።
- እያፌዝክብኝ ነው?
- ኧረ በጭራሽ …ግን እነሱ ምን አሉ ተባለ?
- በሳንጃው ምክንያት ነው የታመምነው አሉ እየተባለ ነው።
- በሳንጃው?
- በሳንጃው …ወይም …በሲንጁ …እንደዚያ መሰለኝ ያሉት።
- እእእ.. በሲጁ… ገባኝ።
- ምን ማለታቸው ነው?
- ወደ ክልሉ ምንም እንዳይገባ በመደረጉ ጤናችን ታውኳል ለማለት ፈልገው ነው። እየተጠቀሙበት ነው።
- እንደዚያ ነው?
- አዎ። ክስ ለማቅረብ መሞከራቸው ነው።
- ቢከሱም ችግር የለውም።
- እንዴት?
- እናንተ ጥሩ መከላከያ መልስ አታጡም ብዬ ነዋ?
- ታመናል ካሉ ምን ማድረግ እንችላለን?
- ማስረጃ ማቅረብ ነዋ?
- የምን ማስረጃ? ምን ብለን?
- የቅርብ ጊዜ አይደለም ብላችሁ።
- ምኑን ነው የቅርብ ጊዜ አይደለም የምንለው?
- ሕመማቸውን ነዋ። የቅርብ ጊዜ ሕመም አይደለም ማለት ነው?
- አይ አንቺ… እሺ የመቼ ነው ስንባልስ?
- የበፊት ነው ማለት።
- ከምን በፊት?
- ከለውጡ በፊት!
[ክቡር ሚኒስትሩ በቢሯቸው ሆነው ከፖለቲካ አማካሪያቸው ጋር በድርድሩ ምን ሊከሰት እንደሚችል ሐሳብ እየተለዋወጡ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር እንዲያው ይህ ድርድር ይሳካል ብለው ያምናሉ?
- በእኛ በኩል ከድርድሩ ምን እንደምንጠብቅ ስላሳወቅን ብዙም አያሳስበንም።
- እንዴት?
- ድርድሩን የተቀበልነው መከላከያ ኃይላችን አሁን እየፈጠረ ያለውን ሁኔታ በማጽናት ወደ አጠቃላይ ሰላም እንደሚወስደን በማመን ነው።
- የእኔ ሥጋት ድርድሩ ባይሳካስ የሚል ነው?
- እየነገርኩህ እኮ ነው?
- እ…?
- ከድርድሩም ሆነ ከወታደራዊ ዕርምጃችን የምንጠብቀው ግብ እንድ ነው።
- አሃ… ገባኝ
- አዎ። ድርድሩ የምንፈልገውን ውጤት የሚያፈጥን ሰላማዊ መንገድ ነው።
- ድርድሩ ባይሳካም የሚፈለገው ውጤት በወታደራዊ መንገድ ይፈጸማል እያሉኝ ነው አይደል?
- ይፈጸማል ብቻ ሳይሆን እየተፈጸመ ነው!
- ግን እኮ የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎችም ሆኑ ምዕራባዊያኑ ከድርድሩ በፊት አስቸኳይ የግጭት ማቆም ስምምነት እያሉ ነው።
- የአፍሪካ ኅብረት እንኳ ምዕራባዊያኑን ለማስደሰትና ብያለሁ ለማለት ያህል እንጂ … አቋሙ ከእኛ ብዙም የተለየ አይደለም።
- ቢሆንም የምዕራባዊያኑ ጫና ቀላል አይደለም ክቡር ሚኒስትር። ግጭት የማቆም ስምምነት ካልተደረሰ አይለቁንም።
- እኛም ግጭት የማቆም ስምምነት ለመፈጸም ዝግጁ እንደሆንን ደጋግመን ነግረናቸዋል።
- ግጭት የማቆም ስምምነት ለመፈራረም በእኛ በኩል ዝግጁ ነን …ይፈለጋል?
- አሁን የጀመርነውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የማይነካ ከሆነ ችግር የለብንም። ይህንንም በግልጽ አሳውቀናል።
- እንዴት …ፍጹም አልገባኝም?
- በሁሉም ክልሎቻችን እንደምናደርገው የፌዴራል መንግሥት ኤርፖርቶችንና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን እንቆጣጠራለን። ይህንን ለማድረግ የማንም ፈቃድ አያስፈልገንም።
- አሃ …ስለዚህ ግጭት የማቆም ስምምነት ይህንን መብትና ኃላፊነት የሚገድብ ካልሆነ መንግሥት ይቀበለዋል ማለት ነው።
- ትክክል፡፡
- ግን በእነሱ በኩል ይህንን በፍጹም የሚስማሙበት አይመስለኝም። ካልተሰማሙ ደግሞ ድርድሩ ፈረሰ ማለት ነው።
- የምንጠብቀው ውጤት ተመሳሳይ ነው ያልኩህ ለዚህ ነው።
- ከምኑ?
- ከድርድሩም ከወታደራዊ እንቅስቃሴውም!