Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥትና የግል ጡረታ ተቋማት ሠራተኞች አስተዳደር ከሲቪል ሰርቪስ ሊወጣ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጠሪ እንዲሆኑ የተደረጉት የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና አስተዳደርና የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ፈንድ አስተዳደር፣ ሠራተኞቻቸውን የሚያስተዳድሩት በብሔራዊ ባንክ አሠራር መሠረት ሊሆን ነው፡፡

ሁለቱ አስተዳደሮች ከዚህ ቀደም ሠራተኞቻቸውን የሚያስተዳድሩት በሲቪል ሰርቪል ኮሚሽን አዋጅና አሠራር መሠረት የነበረ ሲሆን የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ረዕቡ፣ ጥቅምት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ያጸደቃቸው የሁለቱ አስተዳደሮች ማቋቋሚ ደንቦች ይኼንን አሠራር እንደሚቀይሩት ተገልጿል፡፡

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ዋና ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ወዩማ፣ የደንቡን መጽደቅ ተከትሎ የተቋማቸው ሠራተኞች ቅጥር፣ ዝውውር፣ ስበትና ተያያዥ ጉዳዮች፣ በብሔራዊ ባንክ የሠራተኞች አስተዳደር ደንብ መሠረት እንደሚመራ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ፈንድ አስተዳደር ማቋቋሚያ ደንብም ተመሳሳይ ሐሳብ መያዙን ሪፖርተር ስማቸው እንዳይገለጽ ከጠየቁ የተቋሙ ኃላፊ ተረድቷል፡፡

ሁለቱ ተቋማት የሚመሩበት አዋጅ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃድን ሳይጠብቁ በቦርዳቸው ውሳኔ አዋጭና ትርፋማ የሆኑ ኢንቨስትመንቶች ላይ ገንዘባቸውን እንዲያፈሱ በሚያስችል መልኩ የጸደቀው የካቲት 2014 ዓ.ም. ቢሆንም፣ ተጠሪነታቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ ሥር እንዲሆን የተደረገው ቀድሞ ነበር፡፡ ከምርጫ በኋላ መስከረም 2014 ዓ.ም. መንግሥት ሲመሠረት የጸደቀው የፌደራል አስፈጻሚ ተቋማት መወሰኛ አዋጅ ሁለቱ ተቋማት ተጠሪነታቸው ለብሔራዊ ባንክ እንዲሆን አድርጓል፡፡

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ባንክ እንዲሆን የወሰነው ማኪንሲ ኤንድ ካምፓኒ (McKinsey & Company) በተሰኘው ዓለም አቀፍ አማካሪ የተቋሙን አሠራር ለመለወጥ ያጠነው ጥናት ላይ ተመሥርቶ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው፣ አስተዳደሩን ከተመሳሳይ አቻ የአፍሪካ ተቋማት ጋር በማነጻጸር መዋቅሩ መለወጥ እንዳለበትና አስተዳደሩም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር በመውጣት ራሱን ችሎ ‹‹የባንክ ዓይነት መዋቅር›› እንዲኖረው የሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

ይኼንን ለመቀየርም ለተጠሪነት ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፣ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡ ኩባንያው በጥናቱ ማጠቃለያ ላይ፣ የብሔራዊ ባንክ ባለሙያዎች አስተዳደሩ ለሚያደርጋቸው ኢንቨስትመንቶች ጠቃሚ ድጋፍ ሊያደርጉ የሚችሉ መሆናቸውን እንደ አንድ ምክንያት በመጥቀስ፣ አስተዳደሩ በብሔራዊ ባንክ ሥር እንዲሆን ምክረ ሐሳብ ማስቀመጡን ተናግረዋል፡፡

2001 ዓ.ም. የወጣው የብሔራዊ ባንክ ሠራተኞች አስተዳደር ደንብ፣ በሲቪል ሰርቪስ ሥራ ካሉ የመንግሥት ሠራተኞች የተለየ አሠራር ከዘረጋባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የደመወዝ ጉዳይ ሲሆን፣ የሠራተኞች ደመወዝ የሚወሰነው በቦርድ ውሳኔ ነው፡፡ በብሔራዊ ባንክ ደንብ ላይ የአዲስ ሠራተኞች የሙከራ ጊዜ ስድስት ወር ነው፡፡ ይኼ ሌሎች ሠራተኞች ለሙከራ ጊዜ ከሚቆይበት ሁለት ወር በአራት ወር የሚበልጥ ነው፡፡ የዓመት ዕረፍትን በተመለከተም ዝቅተኛው የዕረፍት ጊዜ 20 ቀን ሲሆን ከአንድ ወር ሳይበልጥ በየዓመቱ ያድጋል፡፡

ደንቡ ተግባራዊ ሲሆን የሚኖረውን የአስተዳደሩን የደመወዝ ስኬል በተመለከተ አቶ ገመቹ፣ ‹‹ቦርዱ እያየ የሚለውጠው›› መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የጡረታ አስተዳደሩ አዋጅ ከጸደቀ ከስድስት ወራት የበለጠ ጊዜ ቢኖረውም አስተዳሩ አስካሁን ከግምጃ ቤት ሰነድና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድ ውጪ ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን አለማከናወኑን የሚገልጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ አሁን ደንቡ በመጽደቁ የኢንቨስትመንት አማራጮችን የመመልከትና ኢንቨስት የማድረግ ሥራ እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች