Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ ከተሞች ሞጁላር ዳታ ሴንተሮችን ሊገነባ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ የመጀመርያውን የክላውድ ዳታ ሴንተር አገልግሎት በተጠናቀቀው ሳምንት ያስተዋወቀው ኢትዮ ቴሌኮም፣ ሌሎች የሞጁላር ዳታ ሴንተሮችን ከአዲስ አበባ ውጭ ለመገንባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ  አስታወቀ፡፡

ኩባንያው በሳይንስ ሙዚየም ይፋ ያደረገው የክላውድ ዳታ ሴንተር፣ መረጃዎችን ማከማቸት፣ ማስላት፣ ማቀነባበርና ለተጠቃሚዎች በተለይም ለድርጅቶች በፍጥነት ማቅረብ እንደሚያስችል ያስታወቀ ሲሆን፣ መሰል ማዕከላትን በሌሎች የአዲስ አበባ አካባቢዎች እንዲሁም በክልል ከተሞች በመገንባት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ እንዳተናገሩት፣ ኩባንያው የመረጃ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) በመገንባት ለተቋማት ማከራየት መጀመሩን አስታውሰው፣ በተለይም ደርጅቶችን በማስተዳደር ሒደት ውስጥ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል ዳታ ሴንተር መገንባት አንዱ እንደሆነና ይህንን የመረጃ ማዕከል ፍላጎት በተለይም ለተቋማት በአመቺ ሁኔታ ለማቅረብ መብቃቱን አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ይህን ሁሉ ክላውድ አገልግሎት በምን ያህል አቅም ነው እየገነባ የሚገኘው? (አቅም አለው ወይ) የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት፣ ኩባንያው በቅርቡ እየሠራ ካላቸው ማስፋፊያዎች መካከል አንዱ የሞጁላራይዝድ ዳታ ሴንተር ግንባታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ተገንብተው የተጠናቀቁ፣ በሒደት ላይ ያሉ የሞጁላራይዝድ ሴንተሮች እንዳሉ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ በአዲስ አበባ አራት የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በግንባታ ላይ ያሉና የተጠናቀቁ መሰል ማዕከላት ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከባንያው በጠቅላላው 5.2 ሜጋ ዋት አይቲ ሎድ (640 ራክ) አቅም ያለው ሞጁላር ዳታ ሴንተር በተለያዩ አካባቢዎች እየገነባ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ የክልል ከተሞች ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ተናግረዋል፡፡

ኩባንያው ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው የክላውድ ኮምፒውቲንግ አገልግሎት ተቋማት የራሳቸው የመረጃ ማዕከል እንዲሁም ለማዕከሉ አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን መገንባት ሳያስፈልጋቸው ካሉበት ሆነው የቴክኖሎጂና የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢዎች ዓለም የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን መሠረት አድርገው በገነቧቸውና ደኅንነታቸው በተጠበቁ የመረጃ ማዕከላት መረጃዎቻቸውን ማከማቸት፣ መቀመር ብሎም የተለያዩ አገልግሎቶች ማግኘት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡

በአገሪቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የግልና የመንግሥት ተቋማት ከፍተኛ የመረጃ ክምችትና አጠቃቀም እንዲሁም ተዛማች የክላውድ አገልግሎት ፍላጎት መሠረት በማድረግ  የክላውድ ማዕከላትን መሠረተ ልማትና አስፈላጊ ግብዓቶችን ሁሉ በማሟላት ‹‹ቴሌክላውድ›› የተሰኘ አገልግሎት ማቅረቡን ኩባንያው ጨምሮ አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የመረጃ ማዕከሉን ያስገነባው፣ ከቻይናው ሁዋዌ የቴሌኮም ኩባንያ ጋር በመተባበር መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የክላውድ አገልግሎቶቹ በሦስት አማራጭ መቅረባቸው ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች