Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰላም ንግግሩ በእጅ ጠምዛዦች እንዳይጨናገፍ!

በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ካለው የሰላም ንግግር የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየጠበቀ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ በሰላማዊ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ልዩነቶች ከቁጥጥር ውጪ ወጥተው፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ዕልቂትና ውድመት ያስከተለ ጦርነት ኢትዮጵያውያን በባዕዳን እንዲሸማገሉ አስገድዷል፡፡ መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም አቅቶ ይህ ሁሉ መከራ ከደረሰ በኋላ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የሰላም ንግግር ቢጀመርም፣ በታዛቢነት ስም ንግግሩን የታደሙ አካላት በቀኝም ሆነ በግራ ጫናቸውን ለማሳረፍ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እንደሚታወቀው ምዕራባውያኑም ሆኑ ሌሎች በአፍሪካ ቀንድ ጥቅማቸውን ማስከበር የሚፈልጉ ኃይሎች፣ የሰላም ንግግሩ ወደ ድርድር እንዲሸጋገር የሚደረገውን ጥረት በሚፈልጉት መንገድ ለማስጓዝ እንደሚሹ ከተለያዩ ሚዲያዎች ትንተናዎችና ዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ከተጀመረ ወዲህ በተለይ የአሜሪካና የሸሪኮቿ ድብቅ ፍላጎት በተለያዩ መንገዶች ሲጠቀስ፣ ንግግሩን በባለይነት እየመራ ያለው የአፍሪካ ኅብረት ሚና እዚህ ግባ የሚባል ሥፍራ የተሰጠው አይመስልም፡፡

በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የሚካሄደው የሰላም ንግግር ውሉ ባልታወቀበት ሁኔታ ውስጥ፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማህመት ካናዳ ኦታዋ ከተማ ተገናኝተው መነጋገራቸው ሚስጥራዊ ምክንያቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ ዋነኞቹ የጉዳዩ ባለቤቶች ፕሪቶሪያ ተሰይመው ኦታዋ ውስጥ ስለሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሌላ ንግግር መደረጉ፣ የአጋጣሚ ነገር ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ምን ዓይነት ሴራ እየተጠነሰሰ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የሰላም ንግግሩ ተሳክቶ የድርድር ሒደቱ በአስተማማኝነት እንዲቀጥልና ጦርነቱ እንዲቆም፣ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት ከበስተጀርባ ምንም ዓይነት ድርጊት ማከናወን አይኖርባቸውም፡፡ አሜሪካ በማንኛውም ጉዳይ ጥቅሟን ለማስከበር ስትል የማትፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ቢታወቅም፣ ይህ አደገኛና አውዳሚ ጦርነት በአስተማማኝ ሰላም ሊተካ የሚችለው ከዚህ ቀደም ሌሎች ቦታዎች የሠራችውን ጥፋት እዚህ ላለመድገም ቁርጠኛ ስትሆን ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ከአፍሪካ ኅብረት በላይ ተዋናይ በመሆን የሰላም ንግግሩን ጤና የመንሳት አፍራሽ እንቅስቃሴ መቆም አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሰላም፣ ነፃነትና እኩልነት እንደሆነ ይታወቅ፡፡

በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የተባባሪ አካላት ድጋፍና ትብብር አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከሰላም ጥያቄው በላይ የእነሱ ፍላጎትና ጥቅም ሲቀድም ግን ለምን መባል አለበት፡፡ ሁለቱ ወገኖች ለድርድሩ ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻቸውን የሰላም ንግግር ማድረግ የሚችሉት፣ በአወያይነትም ሆነ በታዛቢነት የታደሙ አካላት በገለልተኝነት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሰብዓዊነትም ሆነ በዴሞክራሲ ስም ጣልቃ ገብነትንም ሆነ ሌላ ፍላጎት ለማራመድ ሲፈልጉ ግን በሕግ መባል አለባቸው፡፡ አውሮፓ ውስጥ በሩሲያና በዩክሬን መሀል እንዲቀሰቀስ የተደረገው አስፈሪ ጦርነት የዓለምን ህልውና አደጋ ውስጥ በከተተበት ጊዜ፣ እዚያ እየታየ ያለው አደገኛ አሠላለፍ እዚህ አይመጣም ብሎ መሞኘት አይገባም፡፡ ዓለምን ለኑክሌር አደጋ ያጋለጡ ኃይሎች ፍልሚያቸውን ወደ አፍሪካ ቀንድ ጎትተው እንደማያመጡት ምንም ማስተማመኛ የለም፡፡ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል የተካሄደው ጦርነትም ሆነ አሁን እየተደረገ ያለው የሰላም ንግግር፣ በውጭ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እንደሚዘወር ማንም አይስተውም፡፡ ዋናው ቁምነገር ግን እነዚህ ኃይሎች የሰላም ንግግሩን እንዳይጠልፉት መጠንቀቅ ነው፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፣ አገራቸው በደቡብ አፍሪካ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር በሚካሄደው የሰላም ንግግር ከፍተኛ ሚና እንዳላት በማስታወቅ፣ ‹‹በሰላም ንግግሩ የሚደረስበትን ውሳኔ በማያከብር ወገን ላይ ተገቢውን ዕርምጃ ትወስዳለች…›› ብለዋል፡፡ አንድን የሰላም ንግግር ሒደት ለመታዘብ የተሰየመ አገር፣ በየትኛው ዓለም አቀፍ ሕግ ዕርምጃ እንዲወስድ እንደተፈቀደለት አይታወቅም፡፡ የሰላም ንግግሩን እንደሚመራ የሚነገርለት የአፍሪካ ኅብረት እንዲህ መሰል ዓይን አውጣ ማስፈራሪያ ሲሰማ በዝምታ ማለፉ፣ ከወዲሁ ኃላፊነቱ እየተሸረሸረ የዳር ተመልካች ለመደረጉ አንድ ትልቅ ማሳያ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ አንድ የውጭ ታዛቢ ኃይል በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ባልተሰጠው ኃላፊነት ማስፈራሪያ ሲያቀርብ፣ የሰላም ንግግሩ እንኳንስ ወደ ድርድር ሊሸጋገር የበለጠ አውዳሚ ጦርነት እንደሚያስከትል ማንም ቢሆን የሚገነዘበው ነው፡፡ ሁለቱ ተነጋጋሪ ወገኖች በጠረጴዛ ዙሪያ በነፃነትና በቀና መንፈስ እንዳይወያዩ የሚያደርግ ጫና በታዛቢነት ከተሰየመ አካል መምጣት ሲጀምር፣ የአፍሪካ ኅብረት ሚናውን ተነጥቆ አፍራሽ አጀንዳ እንደሚተካ መገንዘብ ይገባል፡፡ 

ይህ አውዳሚ ጦርነት ከመነሳቱ በፊት የብዙዎች አርቆ አሳቢዎች ማሳሰቢያ፣ ኢትዮጵያ ለውጭ ጣልቃ ገብነት እንዳትጋለጥ ለሰላም ቅድሚያ ይሰጥ የሚል ነበር፡፡ ነገር ግን ኃላፊነት የማይሰማቸው፣ ከሥልጣናቸውና ከሚያግበሰብሱት ጥቅም በላይ የአገር ህልውና የማያሳስባቸው ጦርነቱን ቀስቅሰው እዚህ አሳዛኝ ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ችግር ሲያጋጥም በአገር በቀል የሽምግልና ሥርዓት መፍትሔ ማስገኘት የሚያስችል ዘመን ተሻጋሪ አኩሪ ባህል ያላት አገር፣ ሳትወድ በግድ ጦርነት ውስጥ ገብታ በሌሎች ሸምጋይነት ውጤቱን ለመተንበይ የማይቻል ሁኔታ ውስጥ ገብታለች፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከደረሰው ዕልቂት፣ ውድመትና ምስቅልቅል ውስጥ መውጣት የሚያስችል ዕድል ከተገኘ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን አድፍጠው ያሉት የውጭ ኃይሎች ከዚህ የሰላም ድርድር ጀርባ የሚያሴሩ ከሆነ ግን፣ አሁንም በከፍተኛ ጥንቃቄና ብልኃት ከዚህ ማጥ ውስጥ እንዴት መውጣት እንደሚቻል መመካከሩ አይከፋም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ የሚያስብ ቀና ልቦና ከተገኘ መፍትሔው በጣም ቅርብ ነው፡፡ ነገር ግን ለንፁኃን ዕንባና ደም የማይጨነቁ ራስ ወዳዶች ችግር መፍጠራቸው አይቀሬ ስለሆነ፣ በተቻለ መጠን ከፍተኛ ትዕግሥትና ዘዴ መላበስ ያስፈልጋል፡፡

አሁን ባለው የዓለም ውስብስብ ነባራዊ ሁኔታ ላይ በመመሥረት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር መፍታት አስቸጋሪ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ነገር ግን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ፍላጎቶችን ይዘው ከሚቀርቡ ዓለም አቀፍ አካላት ጋር የሚደረግ ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ መስተጋብር፣ ብርቱ የሆነ ትዕግሥትና ማስተዋልን ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር ይፈልጋል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታለፈባቸው ልምዶች የሚያስገነዝቡት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረገው ፖለቲካዊም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ቀደም ሲል የነበረውን ዓይነት እንዳልሆነ ነው፡፡ በሩሲያና በዩክሬን መሀል የሚካሄደው ጦርነት የወዳጅና የጠላት ጎራ መለያ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ እያንዳንዱ ሐሳብና ተግባር የሚለካውም ከዚያ ጉድኝት አኳያ ነው፡፡ ቀደም ሲል በአገሮች መካከል በሚኖር የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ወይም በባለ ብዙ ወገን ትስስሮች አማካይነት በእኩልነት መርህ የሚስተናገደው ዲፕሎማሲ፣ የአንድን ወገን የበላይነት በማፅናት ሌላውን ተከታይ ማድረግ እየተለመደበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ አውዳሚው ጦርነት ውስጥ ሆና የሰላም ያለህ በሚባልበት ጊዜ፣ የሰላም ሒደቱ ከግራና ከቀኝ እጅ ጥምዘዛዎች እየበዙት ይመስላል፡፡ የሰላም ንግግሩ በእጅ ጠምዛዦች እንዳይጨናገፍ ጥንቃቄ ይደረግ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...