Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ ችግር ሊፈጥር ይችላል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በፖሊሲ ደረጃ ያሳለፈው ውሳኔ አተገባበር በጥንቃቄ መታየት ያለበት ከመሆኑም በላይ፣ አሁን ካለው የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ፖሊሲው መተግበሩ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ተጠቆመ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከመፈቀዱ ጋር ተያይዞ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ባለሙያዎች ፖሊሲው ከመተግበሩ በፊት ዳግም መፈተሽ ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ፖሊሲውን ለመተግበር የወጡ ረቂቅ መመርያዎችን ተከትሎ በጉዳዩ ላይ በተዘጋጁ የውይይት መድረኮች ላይ የውጭ ባንኮች አገባብ ላይ መንግሥት ጥንቃቄ ያድርግ የሚባለው ግፊት እየጨመረ መምጣቱንም ለመረዳት ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበር ምክር ቤት ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተናጋሪ ከነበሩት የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መካከል ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) እንደገለጹት ከውጭ ባንኮች መግባት ጋር በተያያዘ ሦስት ዋና ዋና ተግዳሮቶች ይገጥማሉ፡፡ ሊገጥሙ የሚችሉት ችግሮች የማክሮ ፋይናንስ መዛባት፣ በባንኮቹ ውስጥ ያለው ችግርና ከብሔራዊ ባንክ አቅም ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁመው፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ የውጭ ባንኮችን ማስገባት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባት ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም የተለያዩ ጥናቶች የሚያመለክቱ ግን የሚባለውን ያህል ጥቅም የሚያመጣ አለመሆኑንና በተለይ የማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ የሚፈቅደውን ፖሊሲ መተግበር ጉዳት ያመጣል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጋር የተያያዙት የዋጋ ንረት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ጦርነት የኢኮኖሚ ውጥኑን ለማስፈጸም ፈታኝ እንደሚሆኑም ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጦርነቱ እንኳን አሁን ቢቆም ተፅዕኖው አንድና ሁለት ዓመት የሚዘልቅ በመሆኑ በዚህ ወቅት የውጭ ባንኮችን ማስገባት ተገቢ ያልሆነ ውሳኔ ነው፤›› ብለው እንደሚያምኑም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ባንኮች እንዲገቡ እንፈቅዳለን መባል ከተጀመረ 15 ዓመታትን ያስቆጠረ በመሆኑ አሁን ካልገቡ መቼ ይገባሉ? የሚለው ጥያቄ ግን አነጋጋሪ ይሆናል ብለዋል፡፡

ስለዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሩ በአንድና ሁለት ዓመት የማይፈታ ስለሆነ በዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ሆኖ ፖሊሲው ባይተገበር የሚመርጡ መሆኑንም ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥት የሆነው ይሁን ውሳኔውን መተግበር አለብኝ ካለ ግን የወለድ ምጣኔው ላይ ገደብ ማድረግ ግድ ይለዋል፤›› ያሉት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ በዚህ ዕሳቤ አሁን ያለው የዋጋ ንረት 35 በመቶ ከሆነ የወለድ ምጣኔውን 40 በመቶ ማድረግ አለበት እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ የባንኮች የማበደሪያ የወለድ መጠን ደግሞ በ50 በመቶ ስለሚወጣ ችግር ሊፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡ በመሆኑም ምናልባት የዋጋ ንረቱ እስከሚወርድ ድረስ የወለድ ምጣኔ መገደብ አንድ አማራጭ ቢሆንም ሌላ ችግር ስለሚያመጣ እሳቸው የሚመርጡት በተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲውን ማስፈጸም የሚበጅ መሆኑን ነው፡፡  

በባንኩ ዘርፍ ውስጥም ችግር ያለ በመሆኑ በተለይ ክሬዲት ሪስክ ማኔጅመንት ላይ ያለውን ችግር ባንኮች ማስተካከል ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

ሌላው ይህንን ፖሊሲ ከማስፈጸም አንፃር ትልቅ ተግዳሮት ተደርጎ የተወሰደው እነዚህ ባንኮች ቢገቡ የብሔራዊ ባንክ የመቆጣጠር አቅም አለው ወይ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)ም ሆኑ ሌሎች በመድረኩ ተናጋሪ የነበሩ የፋይናንስ ባለሙያዎች አሁን ያለው የብሔራዊ ባንክ አቅም የውጭ ባንኮችን ለመቆጣጠር ይችላል ብለው አያምኑም፡፡ እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው ፖሊሲ ወደ 15 የሚሆኑ ጉዳዮችን ሊቆጣጠር የሚፈልግ በመሆኑ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የዘረዘራቸውን ተግባራት የማስፈጸም አቅም ግን ብሔራዊ ባንክ ያለው ባለመሆኑ የውጭ ባንኮች ይግቡ ሲባል ይህም ታሳቢ መደረግ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፖሊሲ ግን በጣም ጥሩ መሆኑን የጠቀሱት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር)፣ ነገር ግን የተዘረዘሩ ተግባራትን ለማስፈጸም አዳጋች በመሆኑ አሁን ባለው አቅምና በአጠቃላይ ከወቅታዊ አገራዊ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት አንፃር ውሳኔውን ማዘግየት ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ አንፃር ይህንን ፖሊሲ ለማስፈጸም ችግር ይሆናል ብለው የጠቀሱት የብሔራዊ ባንክ አፈጣጠር የተቆጣጣሪነት መንፈስ ብቻ ይዞ በመቆየቱ  ጭምር መሆኑንም በመጥቀስ ከዚህ በመውጣት ብሔራዊ ባንክና ከባንኮቹ የጋራ ተቋም በማቋቋም የሚገጥሙ ችግሮችን በጋራ የመፍታት አሠራር መዘርጋትም አንድ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ባለው  የመቆጣጠር አቅም  የተከፈተ ባንክ ግን ችግር የሚፈጥር በመሆኑ በቂ ዝግጅት ማድረጉ ተገቢ እንደሚሆን ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

ለዚህም እንደ ምሳሌ የጠቀሱት ኬንያን ነው፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበትና ተቆጣጣሪው ተቋም ደካማ በሆነበት ሁኔታ ለውጭ ባንኮች ገበያቸውን ከፍተው ከ30 በላይ የሚሆኑ ባንኮቻቸው ከገበያ መውጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡  

በዚህ መድረክ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የአሐዱ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ፣ አሁን ባለው ሁኔታ የውጭ ባንኮች ይግቡ ማለት ብዙ ችግሮች ያስከትላል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በተለይ ለዓመታት የገንዘብ ፖሊሲው ችግር ያለበት ሆኖ ከመቆየቱ አንፃር የውጭ ባንኮችን ማስገባት መፍትሔ እንደማይሆንም ጠቁመዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባት የለባቸውም የሚል እምነት እንደሌላቸው ያመለከቱት አቶ እሸቱ ነገር ግን አሁን እንዲገቡ የሚፈለግበት መንገድ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል ብለዋል፡፡ ይህ ፖሊሲ ወደ 500 ሺሕ የተጠጉ የባንክ የአክሲዮን ባለቤቶችን መብት ሊያስጠብቅ መቻል እንዳለበትም በመጠቆም የውጭ ባንኮች ጥቅም ይሰጣሉ ብቻ ሳይሆን ጉዳት የሚያስከትሉ መሆኑ መታሰብ ስላለበት ፖሊሲውን ለመተግበር ሥጋትን የሚቀንሱ መመርያዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን ነው፡፡  

እንደ አቶ እሸቱ እምነት የሚገቡት ባንኮች ለምሳሌ የኤክስፖርት ሥራ እንዲሠሩ መፈቀድ የለበትም፡፡ ምክንያቱም ባንኮች እየሠሩት ስለሆነ ይኼ ሥራ ከውጭ ባንኮች ከሥራ ዝርዝር ውስጥ መካተት እንደሌለበት አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ እሸቱ ምልከታ የውጭ ባንኮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲከፈቱ አገር ውስጥ ሊያበድሩ የሚችሉትን ሀብት ማምጣት ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡ በአገር ውስጥ ሀብት መጠቀም እንደሌለባቸው አመልክተዋል፡፡ የአገር ውስጥ ሀብትን ሰብስበው የሚያበድሩ ከሆነና በዚህ ሥራቸው በጣም ውጤታማ መሆን ቢችሉ እንኳን እንደ አገር የመጨረሻው ውጤት አገርን መጉዳት ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ባንኮች የራሳችንን ሀብት ለብድር ማቅረብ አግባብ ስለማይሆን ይግቡ ከተባሉ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች ሁሉ መታሰብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡  

የባንኮቹ አከፋፈት ምን መሆን እንዳለበት በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ በቅደም ተከተል መተግበር የሚኖርበት መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢገቡ ተቀማጭ ገንዘብ የማይወስዱና የውጭ ምንዛሪ ሥራዎች ላይ እንዲሠሩ የማይፈቀድላቸው መሆን አለበት፡፡ በአብዛኛው የገቢ ምርቶች ላይ የውጭ ምንዛሪ ማምጣታቸው ላይ ያተኮረ የባንክ ሥራ እንዲሠሩ ተደርጎ መመርያዎች መቀረፅ ይኖርባቸዋል የሚል ምክረ ሐሳብም ሰንዝረዋል፡፡

የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ የእነዚህ ባንኮች መግባት ጠቃሚ ጎን ያላቸው መሆኑን አስረድተው ሊያሳርፉ የሚችሉት ተፅዕኖ ግን በጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አሁን የመንግሥት አቋም የሚያሳየው መግባታቸው የማይቀር በመሆኑ ‹‹ይግቡ አይግቡ›› የሚለው ጉዳይ ያበቃለት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳቱን ቀንሶ እንዴት ገብተው መሥራት እንደሚኖርባቸው በመነጋገርና እንዲህ ባሉ መድረኮች ላይ እየቀረቡ ያሉ ሐሳቦችን ብሔራዊ ባንክ በመመርያዎቹ እንዲያካትት መግፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ባንኮች መግባታቸው አይቀርም ብለን ስንዘጋጅ ቆይተናል ያሉት አቶ መላኩ በበኩላቸው ነገር ግን አገባቡ ደረጃ በደረጃ መግባት ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ መላኩ የባንኮቹ አገባብ መጀመርያ በሽርክና (በፓርትነርሺፕ) ቢጀመር ጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸው፣ ከዚህ ልምድ በመነሳት ወደ ሌሎቹ አማራጮች መግባት ይቻላል ብለዋል፡፡ ሁሉንም አማራጮች በአንዴ መጠቀሙ ግን ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

ፖሊሲው አይፈጸም የሚል ፍላጎት እንደሌላቸው የገለጹት አቶ እሸቱ ደግሞ ባለአክሲዮኖቻችን እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ መሆን አለበት ይላሉ፡፡ እንደ ህንድና ሲሪላንካ ያሉ አገሮችም የውጭ ባንኮችን ያስገቡት ደረጃ በደረጃ በመሆኑ በፖሊሲ ስህተት አገርም ባንኮችን የፈጠሩ ባአክሲዮኖችም እንዳይጎዱ የውጭ ባንኮች አገባብ ደረጃ በደረጃ ሊሆን የሚገባ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ይህንን ሐሳብ የዕለቱ ተናጋሪዎች ሁሉም የተጋሩት ነበር፡፡

በዕለቱ ከተናጋሪዎቹም ሆነ ከተሳታፊዎቹ የተሰጡ በርካታ አስተያየቶች የተነሱ መሆናቸውን የገለጹት ዓለማየሁ (ፕሮፌሰር) ይህ የሚያሳየው ፖሊሲው ሲወጣ ከኋላ ባዶ እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡ ስለዚህ የቀረቡትን ሐሳቦች ግብዓት አድርጎ መንግሥት እንዲጠቀምበት ማደረግ ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሕግ ባለሙያው ፈቃዱ ጴጥሮስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደግሞ ከሕግ አንፃር መታየት አለባቸው ያሉዋቸውን ሐሳቦች አቅርበዋል፡፡ በተለይ ለውጭ ባንኮች እስከ 30 በመቶ የአክሲዮን ድርሻ እንዲሰጣቸው በረቂቅ ሕጉ ላይ የተቀመጠው አንቀፅ ለኢትዮጵያውያኖችም ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁን ያለው ሕግ አምስት በመቶ ብቻ የሚፈቅድ በመሆኑ ይህ ሕግ መስተካከል አለበት ብልዋል፡፡ ሌላው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ያሬድ ኃይለ መስቀል ደግሞ የውጭ ባንኮች መግባት ተግዳሮት ያለው ቢሆንም ገብተው እንዲሠሩ መፈቀዱ አግባብ እንደሆነና የኢትዮጵያ ባንኮችም ለዚህ ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች