Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በትግራይ ክልል ባንኮች አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ቅርንጫፎቻቸውን ኦዲት ማድረግ አለባቸው ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች የፌዴራል መንግሥት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል ከተሞች ውስጥ አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት፣ በክልሉ የሚገኙ ቅርንጫፎቻቸውን ኦዲት ማድረግ እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡

ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መጀመር በኋላ ለወራት ቀጥሎ የነበረው የባንክ አገልግሎት፣ የፌዴራል መንግሥት ሰኔ 2013 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ጦርነቱ ዳግም አገርሽቶ የፌዴራል መንግሥት ሽሬ፣ ኮረምና አላማጣ ከተሞችን መቆጣጠሩን ካሳወቀ በኋላ መሠረታዊ አግልግሎቶችን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ መሠረታዊ አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን የባንክ አገልግሎት የመጀመር ጉዳይ በአካባቢው ሰላም መረጋገጥና የባንኮቹ አገልግሎት ለመጀመር የሚያሳልፉት ውሳኔ ላይ እንደሚመሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡ በባንኩ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ፣ ‹‹ሥራ ሲጀመር ጦርነቱ ምን ያህል ውድመት አድርሷል? በቅርንጫፉ ላይ ምን አለን? ምን የለንም? የሚለውን ኦዲት ካደረጉ በኋላ ነው የሚጀምሩት፤›› ሲሉ ባንኮቹ ቀጥታ አገልግሎት ወደ መስጠት እንደማይገቡ አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ገዥው ገለጻ፣ ብሔራዊ ባንክ ተቋማቱ በቶሎ ወደ ክልሉ በመግባት አገልግሎት እንዲሰጡ ፍላጎት ያለው ቢሆንም ተቋማቸው ስለሚገባበት “የአደጋ ሥጋት” ውሳኔ የሚያሳልፉት ባንኮቹ ራሳቸው ናቸው፡፡ ባንኮቹ በአካባቢዎቹ ላይ ሥራ ለመጀመር ያላቸው አቅም፣ የኦዲት ሥራውን ለማከናወን ያላቸው ዝግጅት፣ እንዲሁም የአካባቢዎቹ ደኅንነት አገልግሎት የመጀመር ሁኔታን የሚወስኑ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባንኮቹ አገልግሎት የሚጀምሩት ከተሞች ነፃ በወጡ ቁጥር “ከሥር ከሥር” ነው ወይስ ክልሉ በሙሉ በፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ሥራ ከሆነ በኋላ የሚለውም በባንኮቹ የሚወሰን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ እዚህ ውስጥ ጣልቃ ባይገባ እንመርጣለን፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሥራ ስትጀምሩ ኦዲት ማድረጉን እንዳትረሱ የሚለውን ከማስታወስ በስተቀር ውሳኔው የራሳቸው ነው፣ ኦዲት አድርገው ባመኑበት ጊዜ ሥራ ይጀምራሉ፡፡ ቶሎ ቢጀምሩ እንመርጣለን፤›› ሲሉ የብሔራዊ ባንክን አቋም አብራርተዋል፡፡

ምክትል ገዥው ብሔራዊ ባንክ ከዚህ ቀደም ባንኮች አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ማድረግ ስለሚገቧቸው ቅድመ ሥራዎች ከተቋማቱ ጋር መወያየቱን አስታውሰው፣ ጥንቃቄ ባልተሞላበት ሁኔታ አገልግሎት መጀመር “አደጋ ይኖረዋል” የሚል ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በመስከረም ወር ለሁለት ቀናት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከተለያዩ ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩት የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ተወካይ አኔት ዌበር ስለጉብኝታቸው ለኅብረቱ ባቀረቡት ሪፖርት፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች “በአንድ ጊዜ” እንደማይጀመሩ መረዳታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

‹‹ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ጊዜ የሚያስጀምር አንድ ማብራሪያ የለም፤›› ያሉት ተወካይዋ፣ አገልግሎቶች ሊጀምሩ የሚችሉት በሒደት መሆኑን በሪፖርታቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥት የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትን “ወድያውኑ” ማስጀምር እንደሚችል ገልጸው፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለማስጀምር ግን የቴክኒክ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ለኅብረቱ አስረድተዋል፡፡ የባንክ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት ደግሞ የኦዲት ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ በትግራይ ክልል ባንኮች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉበት ሁኔታ ላይ በማማከር ዕገዛ የሚያቀርብበት መንገድ የሚኖር ከሆነ መመልከት እንደሚገባ፣ ለኅብረቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጠይቀው ነበር፡፡

በክልሉ የባንክ አገልግሎት ማስጀመርን አስመልክቶ ከአውሮፓ ኅብረት የሚቀርብ ዕገዛ ሊኖር ይችል እንደሆን ጥያቄ የቀረበላቸው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹[አገልግሎት መጀመር] ትክክል ከሆነ ራሳቸው ባንኮቹ ይጀምራሉ፣ እንዴት ይጀምራሉ የሚለውም የተነጋገርንበት ነው፣ ከዚህ ቀደም ጀምረው የተቋረጠውን ይቀጥላሉ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ቦታዎች ውስጥ አገልግሎት መጀመርን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ብርሃንና ዳሽን ባንኮች፣ አገልግሎት ለመጀመር ከመንግሥት በኩል የሚመጣ መልዕክት እየጠበቁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዳሽን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ በአካባቢዎቹ ስላለው ሁኔታ ከመንግሥት ገለጻ እስከሚደረግ እየጠበቁ መሆኑን ገልጸው፣ ባንኩ በመንግሥት ገለጻ ሲደረግ በቶሎ ሥራ ለመጀመር ኮሚቴ ማቋቋሙን አስረድተዋል፡፡

ዳሽን ባንክ በትግራይ ክልል ውስጥ 17 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ የተቋቋመው ኮሚቴ አንዱ ኃላፊነት እነዚህ ቅርንጫፎች ኦዲት ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በነበረበት ጊዜ ሕወሓት በተቆጣጠራቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ 238 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች፣ ዘረፋና ውድመት እንደደረሰባቸው ባንኩ አስታውቆ ነበር፡፡ በተጨማሪም ባንኩ በመቀሌና በሽሬ ከተሞች የሚገኙ 120 ቅርንጫፎቹ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ እንደማያውቅ መግለጹ ይታወሳል፡፡

በትግራይ ክልል ውስጥ 112 ቅርንጫፎች ያሉት ወጋገን ባንክም በተመሳሳይ የቅርንጫፎቹን ሁኔታ እንደማያውቅ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች